የሱዳን ውጊያ ምን ያክል ብርቱ ነው? የአፍሪቃ ቀንድን ምን ያክል ያሰጋል?
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 10 2015በሱዳን ጦር እና እጅግ ኃይለኛ በሚባለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ቅዳሜ ሚያዝያ 7 ቀን 2015 በተቀሰቀሰው ውጊያ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 200 ገደማ ደርሷል። በውጊያው ኻርቱምን ጨምሮ በተለያዩ የሱዳን ግዛቶች ከ2000 ሺሕ በላይ ሰዎች ቆስለዋል።
የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብዱል ፋታኅ አል ቡርኻን እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የሚመሩት ብርጋዴየር ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በጋራ መፈንቅለ መንግሥት አሲረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክን ከሥልጣን ያስወገዱ አጋሮች ነበሩ። ሁለቱ ወታደራዊ አዛዦች ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በተናጠል በስልክ ካደረጉት ውይይት በኋላ ለ24 ሰዓታት ተኩስ ለማቆም ተስማምተዋል። ሙሉ በሙሉ ውጊያውን ማቆም እናሸማግላለን ላለው ኢጋድ፣ ሙሳ ፋቂ ማኅማትን ወደ ኻርቱም ለመላክ ለወሰነው ለአፍሪቃ ኅብረትም ይሁን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምን ያክል ፈታኝ ነው?
ለአንድ ዓመት በላይ ከዘለቀ የኃይል ትንቅንቅ በኋላ ወደ ውጊያ አዘቅት የተዘፈቀችው ሱዳን የተለያየ የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውስ ያለባቸውን ሊቢያ፣ ቻድ፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ እና ደቡብ ሱዳንን ታዋስናለች። ከሁለት ዓመት ብርቱ ጦርነት ለማገገም የምትንፏቀቀው የኢትዮጵያ ጎረቤት ናት። ይኸ ወትሮም በቅጡ መርጋት የተሳነውን የአፍሪቃ ቀንድ አስግቷል። ይኸ ውጊያ ለአፍሪካ ቀንድ ምን ያክል ያሰጋል? በቻታም ሐውስ ተባባሪ ተመራማሪው አቤል አባተ ለዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከአቶ አቤል አባተ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።
እሸቴ በቀለ