1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሱዳን የናይል ወንዝ የጎርፍ ሥጋት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ

ሰለሞን ሙጬ
ማክሰኞ፣ መስከረም 20 2018

ሱዳን ዐባይ ወንዝ አቅራቢያ በሚገኙ አምስት ግዛቶቿ ሊደርስ ስለሚችል የጎርፍ አደጋ የተጋላጭነት ማስጠንቀቂያ አወጣች። የሱዳን የመስኖ ሚኒስቴር ባወጣው ማሳሰቢያ የናይል ወንዝ የውኃ መጠን መጨመሩን ተከትሎ ብርቱ የጎርፍ አደጋ በእርሻ መሬቶች እና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል የሀገሪቱ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ
ሚኒስትሩ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት የህዳሴ ግድብ ለሁለቱም ሀገራት "ትልቅ በረከት ይዞ መጥቷል።ምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

ሱዳን የጎርፍ ስጋት ገብቶኛል ስትል ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ተከላከለች

This browser does not support the audio element.

የሱዳን የናይል ወንዝ የጎርፍ ሥጋት እና የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም

ሱዳን ዐባይ ወንዝ አቅራቢያ በሚገኙ አምስት ግዛቶቿ ሊደርስ ስለሚችል የጎርፍ አደጋ የተጋላጭነት ማስጠንቀቂያ አወጣች።

የሱዳን የመስኖ ሚኒስቴር ባወጣው ማሳሰቢያ የናይል ወንዝ የውኃ መጠን መጨመሩን ተከትሎ ብርቱ የጎርፍ አደጋ በእርሻ መሬቶች እና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል የሀገሪቱ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ሰሞኑን ከዶቼ ቬለ ጋር አድርገውት በነበረ ቃለ ምልልስ "ሱዳን ውስጥ ብዙ ሥራ የሚሠራው ለመስኖ መሆኑን" ጠቅሰው "ሕዳሴ [ግድብ] በመኖሩ ተጨማሪ ውኃ እንዲያገኙ ማስቻሉን ተናግረዋል።

ሱዳን ውስጥ በጎርፍ ምክንያት "ክረምት ላይ በየዓመቱ ብዙ ሃብት የሚወድምበት እና ብዙ ሕይወት የሚጎዳበት ጉዳይ ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት አልነበረም" ሲሉም ግድቡ "በቀጣይም ምንም አደጋ አያመጣባቸውም"፣ ይልቁንም ከአደጋ መታደግ ችለናል የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። በጉዳዩ ላይ ዛሬ ለተጨማሪ ማብራሪያ ልናገኛቸው ብንሞክርም ስብሰባ ውስጥ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የሱዳን የጎርፍ ማስጠንቀቂያ ምን ያህል አሳሳቢ ነው?

የጎረቤት ሀገር ሱዳን መንግሥት የመስኖ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በጥቁር እና ነጭ ዐባይ ያለው የውኃ መጠን እየጨመረ መሆኑን በመጥቀስ በኻርቱም፣ በሪቨር ናይል፣ በነጭ ዓባይ፣ በሰናር እና በብሉ ናይል ግዛቶች የሚኖሩ ነዋሪዎች የጎርፍ አደጋ በእርሻ መሬቶች እና ቤቶች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ጠቅሶ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

በሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች የጎርፍ መጥለቅለቅ በመከሰቱ በናይል ወንዝ አካባቢ የሚኖሩ አንዳንድ ገበሬዎች "የሽንኩርት ምርታቸውን በፍጥነት ለመሸጥ መገደዳቸውንም" ሰሞነኛ ዘገባዎች አመልክተዋል።

የሱዳን የመስኖ ሚኒስቴር እሑድ ዕለት ባወጣው መግለጫ በአካባቢው ያሉ ግድቦች መጠኑ የበዛ ውኃ በመልቀቃቸው ለተከታታይ አራት ቀናት የውኃ ፍሰቱ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሶ ጥንቃቄ እንዲደረግ አስጠንቅቋል።

በሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች የጎርፍ መጥለቅለቅ በመከሰቱ በናይል ወንዝ አካባቢ የሚኖሩ አንዳንድ ገበሬዎች "የሽንኩርት ምርታቸውን በፍጥነት ለመሸጥ መገደዳቸውንም" ሰሞነኛ ዘገባዎች አመልክተዋል።ምስል፦ Hohlfeld/IMAGO

ኢትዮጵያ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ. ም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስመርቃለች። ግድቡ ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር በቅርበት በሚያዋስነው ጉባ መገንባቱ ሱዳንን ማሥጋቱ አልቀረም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ላይ ያለው አቋም

አሶሺየትድ ፕሬስ የኢትዮጵያ የውኃ እና ኢነርጂ ሚንስትር ኢንጂኒየር ሃብታሙ ኢተፋ ጠቅሶ ትናንት እንደዘገበው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሱዳንን ከአስከፊ የጎርፍ አደጋ ተከላክሏል። ዶቼ ቬለ ሚኒስትሩን ዛሬ ሊያገኛቸው ቢሞክርም ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። ከሳምንት በፊት ለዶቼ በሰጡት ማብራሪያ ግን ለዚሁ ጉዳይ ምላሽ ሰጥተውበታል።

"ህዳሴን ስንገነባ በነበርንበት ሰዓት ምንም ነገር አልጎዳናቸውም። ይልቅ ትርፍ ነው ያገኙት [ሱዳን እና ግብጽ]። ሱዳን ውስጥ ብታይ ብዙ ሥራ የሚሠራው ለመስኖ ነው። ለዚያ ነበር መሬታቸው የሚያመቸው። ክረምት ላይ በየ ዓመቱ በጣም ብዙ ሃብት የሚወድምበት፣ ብዙ ሕይወት የሚጎዳበት፣ ብዙ አደጋ ይደርስበት የነበረው ጉዳይ ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት አልሰማንም። ምን አድርገናል ማለት ነው? ከአደጋ መታደግ ችለናል።"

የናይል የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግብፅም ሆነች ሱዳን የወንዙ የውኃ መጠን ይቀንሳል በሚል ለዓመታት የህዳሴን ግድብ ግንባታ ሲቃወሙ ቆይተዋል። በተለይ ግብጽ የውኃ ክፍፍል አሳሪ ስምምነት እንዱኖር መፈለጓ አሁንም ግድቡ ተጠናቆ እንኳን ጉዳዩን ለመንግሥታቱ ድርጅት አቤት እንድትል አድርጓታል። የኢትዮጵያ ውኃና ኡነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ እንደሚሉት ግን ግድቡ ወደፊትም ቢሆን ሀገራቱን ይጠቅማል እንጂ የሚጎዳ አይደለም።

"ይህ ውኃ የትም አይሄድም። ከሱዳን አልፎ ወደ ግብጽ ነው የሚሄደው። ሥጋታቸውን ውኃው ምንም ሳይጎዳቸው እስካሁን ህዳሴን ካጠናቀቅን በቀጣይም ምንም አደጋ አያመጣባቸውም። ሥጋት ሊገባቸው አይገባም።"

ሚኒስትሩ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት የህዳሴ ግድብ ለሁለቱም ሀገራት "ትልቅ በረከት ይዞ መጥቷል።" ባለፉት ዓመታት የውኃውን የፍሰት መጠን እየለካን ነበር ሲሉም "ክረምት ላይ ሲያስቸግር የነበረን ጎርፍ በትልቁ ነው የቀነሰው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW