የሱዳን ጦርነትና የኧል ቡህራን የእንኳን አደረሳችሁ መልክት
ዓርብ፣ ሚያዝያ 13 2015በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ባለፈዉ ቅዳሜ የጀመረዉ ዉግያ ዛሬም ለሰባተኛ ቀን እንደቀጠለ ነዉ። የሱዳን ተቀናቃኝ ጀነራሎች ለሦስተኛ ጊዜ የተኩስ አቁም ለማድረግ ቃል ቢገቡም በሱዳን በተለይ መዲና ካርቱም ላይ እየተካሄደ ያለዉ ጦርነት ቀጥሏል። የእርስ በርሱን ጦርነት በመሸሽ በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናዉያን ሃገራቸዉን እየለቀቁ ቻድ እየገቡ ነዉ። ሌሎች ሱዳናዉያን በምግብ እና በመጠጥ ዉኃ ችግር እቤታቸዉ ዉስጥ እየተሰቃዩ ነዉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጦርነቱ ከጀመረ ለመጀመርያ ጊዜ የታዩት የሱዳን ከፍተኛ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡህራን ሃገራቸዉ ሱዳን በሲቪል ለሚመራ መንግሥት ቁርጠኝነቷን ገልፀዋል። ጀነራሉ ኢድን አስመልክተዉ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልክት ሃገራቸዉ ሱዳን ዲሞክራስያዊ ሽግግር እንደምታደርግ ተስፋቸዉን በመግለፅ በጦርነቱ ለወደቁ ሰማእታት ነፍስ እንፀልያለን ብለዋል። ጀነራሉ ይህን ንግግር ያድርጉ እንጂ በተለይ ካርቱም ከተማ ዛሬም በከባድ መሳርያ ስትናጥ ነዉ የዋለችዉ
«ውድ ሀገራችን ዒድ አልፈጥርን የተቀበለችዉ የሞቱና የቆሰሉ ሰዎች ወድቀው፣ ቤተሰቦች ተፈናቅለዉ፣ ህንፃዎችና ቤቶች ወድመዉ፣ ደስታ በሚገባት በሃገራችን የጥይት ድምፅ እየተሰማ ነዉ። ነገሮች በዚህ ሁኔታ በመምጣታቸው በጣም እናዝናለን። ነገር ግን ሁልጊዜ ይህን መከራ ከተወደደው ሕዝባችን ጋር እንደምናልፍ እና በይበልጥ በአንድነት እና በጠንካሬ፣ ሁሉም ለአንድ ሠራዊት፣ እንደሚጮኹ ተስፋ አለን። ይህንን መከራ በጥበብ እና በጥንካሬያችን እንደምናሸንፈው፣ የመንግሥትን ደህንነት እና አንድነት እንደምንጠብቅ፣ ወደ ሲቪል አገዛዝ አስተማማኝ ሽግግር ለመስጠት እንደሚያስችለን እርግጠኞች ነን። የተከበራችሁ ዜጎቻችን ለሀገራችን ሰማዕታት ሁሉ ነፍስ እንፀልያለን፤ ለተጎዱት ሰዎች ምኞታችንን እንገልፃለን። በዚህ ኢድ እለት ደህንነትና ሰላም እንዲያመጣ ወደ ፈጣሪ እንጸልያለን።»
በሱዳን ጦር ሠራዊት ይህን ይበሉ እንጂ በሱዳን መዲና ካርቱም ላይ አንድ የመኖርያ ቤት ህንጻን በከፍተኛ ፍንዳታ ወድሟል ከቀትር በፊት ከፍተኛ ፍንዳታ እና የከባድ መሳርያ ተኩስ ሲሰማ ነበር። ይህ የመኖርያ ቤት ፍንዳታ ከተሰማ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ለስልጣን እየተዋጉ ያሉት ሁለት ጀነራሎት "ቢያንስ የሦስት ቀናት" የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። የጀርመንዋ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌላ ቤርቦክም በሱዳን የሲቪሉ ማህበረሰብ ደህንነቱ ወደተረጋገጠ ቦታ እንዲዛወር እና የርዳታ ድርጅቶች ሰብዓዊ ርዳታን እንዲያደርሱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል። የሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል የኢድ በዓአልን በማስመልከት የሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ ዛሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ለ 72 ሰዓት የሚዘልቅ የተኩስ አቁም ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታዉቀዋል። በሱዳኑ ጦርነት እስካሁን ወደ 413 ሰዎች መገደላቸዉ ተነግሯል።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ