1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ጦርነት በአፍሪቃዉ ቀንድ የደቀነዉ ስጋት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 11 2015

ግብጻዉያን ከሱዳን መደበኛ ሰራዊት ጋር ልምምድ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ኤርትራ እና ቻድም በሱዳን ላይ ትልቅ የወዳጅነት ፍላጎት አላቸዉ። ፕሬዚዳንት ኢሳያስም በሱዳን የሚሆነዉ ነገር አተኩረዉ እያዩ ናቸዉ። ምክንያቱም ኢሳያስ ከሱዳኑ የሚሊሺያ መሪ ጋር ጥሩ ግንኙነት አላቸዉ። የሱዳን ችግር የሌሎች ሃገሮችን ጣልቃ ገብነት የሚጋብዝ ሊሆን ይችላል።

Kämpfe im Sudan
ምስል Marwan Ali/AP/dpa/picture alliance

«የሱዳንን አየር ኃይል የሚያበሩት ግብጾች ናቸዉ፤ የጦር አዉሮፕላኑ ሳይቀር የግብፅ ነዉ እየተባለ የሚወጣ መረጃ አይተናል። ብዙ ግምትም አለ።»

This browser does not support the audio element.

በሱዳን ጦር ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት መካከል ባለፈዉ ቅዳሜ የጀመረዉ ዉግያ ዛሬም ለአምስተኛ ቀን እንደቀጠለ ነዉ። የግጭቱ ተሳታፊዎች ትናንት በአራተኛ ቀኑ ለ24 ሰዓታት የሚዘልቅ ተኩስ ለማቆም መስማማታቸዉ ቢገልፁም ተግባራዊ አልሆነም። ሁለቱ ተወዛጋቢ አካላት ዛሬም ለሁለተኛ ጊዜ ለ 24 ሰዓታት የተኩስ አቁም ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፤ ተግባራዊነቱ ግን ዛም አጠያያቂ ነዉ። የኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጂቡቲ መሪዎች ለማሸማገል በካርቱም የሚጠበቁት በሱዳን የሚካሄደው ውጊያ በቀጠለበት ወቅት ነው። ጦርነቱ ተጠናክሮ በካርቱም እና አካባቢዋ ሆሲታሎች እና የጤና ተቋማት ወድመዋል። ህዝቡ የመጠጥ ዉኃ የህክምና አገልግሎት ብሎም የኤሌትሪክ አገልግሎት ችግር ገጥሞታል። በተመድ ግምት መሰረት በአምስቱ ቀናት የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በትንሹ 270 ሰዎች ተገድለዋል፤ ከ 2500 በላይ ቆስሏል። ሱዳን ወዴት እያመራች ይሆን?    

ጀነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ምስል Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

የሱዳን ብሔራዊ መከላከያ ጦርና የሐገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሽኩቻ ተባብሶ ነፍጥ አንግበዉ ከተማ ዉስጥ መዋጋታቸዉን ቀጥለዋል። የዛሬ አራት ዓመት ግድም ፕሬዚዳንት ኦማር አልባሽርን ከስልጣን ያስወገዱት ከዝያም ለጥቀዉ የሱዳን የሽግግር መንግሥት ጠ/ሚ ሆነዉ ወደ ስልጣን የመጡትን አብደላ ሃምዶክን ያባረሩት የዛሬዎቹ ሁለት የሱዳን ተቀናቃኝ ወታደራዊ ኃይላት ሱዳንን ወዴት እየወሰድዋት ይሆን? የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራህማን ሰዒድ እንደሚሉት የሱዳን ችግር እየተባባሰ የሌሎች ሃገራትን ጣልቃ ገብነትን እየጋበዘ ነዉ።

«ሱዳን በአሁን ወቅት ከባድ ደረጃ ላይ ነዉ የምትገኘዉ። ከሁለቱ ተዛጋቢ ወገኖች መካከል አንዱ አሸንፎ ከወጣ ሱዳን በአንባገነን እጅ ስር ትወድቃለች። ካልተሸናነፉ ደግሞ ሱዳን ሶማልያ፤ ሊቢያ፤ ኢራቅ የመሳሰሉት ሃገራት የሚገኙበት አይነት እጣ ፈንታ አይነት ይገጥማታል። በተለይ አሁን እየተካሄደ በሚገኘዉ ጦርነት ላይ ግብጾች ምናልባት ከተሳታፊነት ሩቅ አይሆኑም፤ ምክንያቱም ግብጾች ከአልቡህራን ማለትም ከመደበኛዉ ሠራዊት ጋር ተሰልፈዉ መዋጋት ይፈልጉ ይሆናል። ሱዳን ለግብጽ በጣም አስፈላጊ ስልታዊ ቦታ ናት። እስካሁን ግብጻዉያን ከሱዳን መደበኛ ሰራዊት ጋር ልምምድ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በሌላ በኩል የኤርትራ የቻድ ኃይላት በሱዳን ላይ ትልቅ የወዳጅነት ፍላጎት አላቸዉ። ምስራቃዊ ሱዳን ከኤርትራ ጋር በጎሳም ሆነ በሌላ በጣም የተግባባ ነዉ። ፕሬዚዳንት ኢሳያስም በሱዳን የሚሆነዉን ነገር አተኩረዉ እየተከታተሉ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ኢሳያስ ከሱዳኑ የሚሊሺያ መሪ ጋር ጥሩ ግንኙነት አላቸዉ። የሱዳን ችግር እየተባባሰ ሲሄድ የሌሎች ሃገሮች ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝ ሊሆን ይችላል»      

ጀነራል አብደል ፋታህ ኧል ቡራን ምስል Marwan Ali/AP/dpa/picture alliance

ሱዳን በደም ጨቅይታለች። ዛሬ ለአምስተኛ ቀን በቀጠለዉ የእርስ በርስ ጦርነት እንደተባበሩት መንግሥታት ግምት እስካሁን ወደ 270 ሰዎች ተግድለዋል። ወደ 2500 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። በሱዳኑ ግጭት እየተዋጉ ያሉት ሁለቱ የጦር ጀነራሎች ለ24 ሰዓታት የሚዘልቅ ተኩስ የማቆም ስምምነት ደርሰናል ቢሉም ስምምነቱ ገቢራዊ አልሆነም። ጦርነቱ በቀጠለበት ያደራድራሉ ተብለዉ በካርቱም የሚጠበቁት የኬንያው ዊሊያም ሩቶ፣ የደቡብ ሱዳኑ ሳልቫ ኪር እንዲሁም የጂቡቲው ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናሉ? አጠያያቂ ነው።

የሱዳንን ህዝብ አጣብቂኝ ዉስጥ የከተተዉ የሱዳን ቀዉስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአካባቢዉ ሃገራት ምን አይነት ተግዳሮት ይኖረዋል? በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዉስጣዊ የፖለቲካ መረጋጋት በማይታይባቸዉ ሃገራት?  

«ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋራ የድንበር እና የህዳሴ ግድብ ችግር አለባት። ይህ ጉዳይ ሁለቱ ሃገሮች ሳይስማሙ ብዙ የቆዩበት ጉዳይ ነዉ። ግብጽ ይህን ክፍተት ተጠቅማ ግድቡ ላይ ጥቃት ለመፈፀም ትሞክር ይሆን የሚለዉ ጉዳይ ኢትዮጵያን ሊያሰጋት ይችላል። ከኤርትራም ጋር ቢሆን እንዲሁ ችግር አለ። ኤርትራ ከሱዳን ጋር በጎሳም ሆነ በሌሎች ብዙ ነገሮች በቀጥታ የተሳሰሩ ሃገሮች ናቸዉ። ቻድም በዳርፉር በኩል፤ በምዕራብ ሱዳን በኩል የተሳሰሩ ሃገራት ናቸዉ። በዚህም አለ በዝያ የሱዳን ጦርነት ግብጽን ከሌሎቹ ሃገራት በላይ ሊያሰጋ እና ሊያሳትፍ ይችላል። በአሁኑ ወቅት የሱዳንን አየር ኃይል የሚያበሩት ግብጾች ናቸዉ፤ የጦር አዉሮፕላኑ ሳይቀር የግብፅ ነዉ እየተባለ የሚወጣ መረጃ አይተናል።  እየተወራም ነዉ፤ ብዙ ግምትም አለ። ስለዚህ የግብፅ በሱዳን ጦርነት መሳተፍ ኢትዮጵያንም ሊያሰጋት ይችላል።»     

የሱዳን ጦርነት እንዲቆም በርሊን ጀርመን ዉስጥ የተካሄደ ጥሪ ምስል Michael Kuenne/Zumapress/picture alliance

የሱዳን ህዝብ በጦር ጀነራሎች አንመራም፤ በወታደር መመራት ትርፉ  በጦር መዋጋት ነዉ ሲል ለዓመታት በዘለቀ በሰልፍ የሲቪል መንግሥት እንዲመሰረት በሰልፍ ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረዉ የሱዳን ህዝብ ዛሬ በሁለት ዝሆኖች ጠብ ሆነና፤ ሁለቱ ጀነራሎች መዲና ካrtumeን ጨምሮ በተለያዩ የሱዳን ከተሞች ከተከታዮቻቸዉ ጋር ቃታ ስበዉ ህዝቡ መከራ ዉስጥ ዘፍቀዉታል።  

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW