የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የብሔራዊ ጦሩን ይዞታዎች እና ሲቪል መሰረተ ልማቶች በድሮን አጠቃ
እሑድ፣ መስከረም 4 2018
የመሐመድ ሐምዳን ደጋሎ የሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የሚገኙ ቁልፍ የብሔራዊው ጦር ይዞታዎች እና የህዝብ መገልገያ የመሰረተ ልማቶችን በድሮን እንዳጠቃ አንድ ከፍተኛ የጦር መኮንን ተናገሩ።
ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ጥቃት መፈጸሙ የተሰማው አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ሰብአዊ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጥሪ ባቀረቡ በሁለተኛው ቀን ነው።
በጥቃቱ የሱዳን ብሔራዊ ጦር 18ኛ ክፍለ ጦር ዋና ማዘዣ እና በዋይት ናይል ግዛት ከኮስቲ ከተማ አቅራቢያ የሚገኙ የነዳጅ ማከማቻዎች ዒላማ መደረጋቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በተጨማሪም ከኮስቲ ከተማ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኝ የከናን የአየር ማረፊያ እና ኤርፖርት ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ከከተማዋ በስተ ምሥራቅ የሚገኘው የኡም ዳባኪር የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በድሮን መመታቱን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ወታደራዊ መኮንን ጠቅሶ የዜና ምንጩ ዘግቧል።
ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በስተደቡብ 320 ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው ኮስቲ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጾች ሲሰሙ እንደነበር የአይን ምስክሮች ተናግረዋል። ለጥቃቱ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም።
የሱዳን ብሔራዊ ጦር የድሮን ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጦ ነገር ግን ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥቧል። የፈጥኖ ደራሹ ኃይል የድሮን ጥቃት በአንድ ሳምንት ውስጥ ሲፈጸም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ተብሏል።
የሱዳን ብሔራዊ ጦር ቃል አቀባይ ትላንት ቅዳሜ ጠዋት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሰሜን ኮርዶፋን ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ኢል -ኦቤይድ ላይ በድሮኖች ጥቃት መፈጸሙን ተናግረው ነበር።
ዩናይትድ ስቴትስ፣የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ፣ ግብጽ እና ሳኡዲ አረቢያ በሱዳን ከሁለት ዓመታት በላይ የተዋጉ ኃይሎች ሰብአዊ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል። አራቱ ሀገራት ለሰብአዊነት ሲባል የሚደረገው የተኩስ አቁም ቋሚ እንዲሆን እና ሱዳን ወደ ሲቪል የፖለቲካ ሥርዓት እንድትሸጋገር ጭምር በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
ይሁንና ወደፊት በሲቪል ፖለቲከኞች ሊቋቋም በሚችል መንግሥት ውስጥ ተፋላሚ ኃይሎች መሳተፍ አይኖርባቸውም የሚል አቋም አላቸው።
ጦርነቱን ለማቆም የሚደረገውን ጥረት በበጎ እንደሚመለከት የገለጸው የሱዳን ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ግን "በሱዳን መንግሥት ሉዓላዊነት፣ በሕጋዊ ተቋማት እና ሕዝቡን እና መሬቱን የመጠብቅ መብቷን የማያከብሩ ጣልቃ ገብነቶችን እንደማይቀበል" አስታውቋል።
አርታዒ እሸቴ በቀለ