1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሱዳኖች ዉጊያ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 9 2015

ሁለቱ ጄኔራሎች የሚያዙዋቸዉ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦርና መከላከያ ጦር ባልደረቦች ናቸዉ።ሁለቱ ጄኔራሎች የአልበሽር ታዛዥ ሆነዉ ዳቦና ፉል ጥየቃ አደባባይ የወጣዉን ደሐ አስገደሉ፣የወታደራዊ ሁንታ መሪዎች ሆነዉ የተቃወማቸዉን ሰላማዊ ሰዉ አስገደሉ።ከቅዳሜ እስከ ዛሬ ደግሞ በትንሽ ግምት መቶ ሰላማዊ ሰዎችን አስገደሉ።

Sudan | Militärübung im sudanesischen Maaqil-Gebiet
ምስል፦ Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

ሱዳን፣ «ሁለት አዉራ ዶሮዎች አንድ ቆጥ---»

This browser does not support the audio element.


የተቀራራቢ ዘመን፣ የአንድ ሐገር ግን የሩቅ ለሩቅ አካባቢ ዉልዶች ናቸዉ።የአስተዳደግ፣ ሙያ፣ ዕዉቀት ተቃራኒዎች ግን የአንድ አለቃ ምንዝሮች፣ ያንድ ጦር ሜዳ ተዋጊ-አዋጊ ጓዶች ነበሩ።ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ቀደም ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሕምዲቲ) ከተል ብለዉ የጄኔራልነት ማዕረግ የለጠፉላቸዉን አለቃቸዉን ከዱ። ካስልጣን አስወገዷቸዉም።ሚያዚያ 11 2019 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።የአንድ አለቃቸዉን ስልጣን እንደ ዋናና ምክትል የተጋሩት ጄኔራሎች እንዳጀማመራቸዉ አልቀጠሉም።«አንድ ቆጥ ላይ ሁለት አዉራ ዶሮ አይስፍርም» እንዲል ሐበሽ-ሆኖ በ4ኛ ዓመታቸዉ ዘንድሮ ዉጊያ ገጠሙ።ኻርቱምን የሚያነደዉ ዉጊያ መነሻ፣ የሁለቱ ጄኔራሎች የፍቅር-ጠብ አጫር ወግ ማጣቃሻ የዉጪዉ ዓለም ጥሪ-ተማፅኖ መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
                              
2018።ሱዳኖች ነዳጅ አጡ።የሞፎና የፉል ዋጋም ሲበዛ አሻቀበ።መልክ፣ባሕሪ፣ ሰበብ- ምክንያት አካባቢዉን የሚቀያይረዉ ጦርነት፣የምዕራባዉያን ማዕቀብና ጫና ግራ ቀኝ የሚያላጋዉ፣ በብሉሹ አሰራርና ሙስና እስከ አናቱ የተዘፈቀዉ የፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አልበሽር መንግስትን ከዚሕ በላይ ሊታገሱት አልፈቀዱም።
ቀዳሚዎቹ የሰሜን ሱዳናዊቱ ከተማ የአትባራ ነዋሪዎች በጣሙን ወጣቶች ነበሩ።ታሕሳስ 17 2018።
የገዢዉ የብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የአትባራ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት መኪኖች በእሳት ጋዩ።የፅሕፈት ቤቱ ግርግዳ፣አጥርና ንብረት ተሰባበረ።በሳልስቱ ተቃዉሞዉ ካርቱምን እንዱሩማንን፣ ከሰላን፣ ሰናርን እያለ-----ብዙ ከተሞችን አጥለቀለቀ።
ሰልፈኛዉን ለመበተን የዘመተዉ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር የመጀመሪያዉን ሰላማዊ ሰልፈኛ ገደለ።የ60 ዓመት አዛዉንት ነበሩ።
ሕዝባዊዉ አመፅ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተገደለ፣አካሉ የጎደለ፣የተደፈረዉን ሰላማዊ ሰዉ ትክክለኛ ቁጥር በዉል አይታወቅም።ሱዳን ሞት አይፈራም።በጥይት እየተገደለ፣ በቆመጥ እየተቀጠቀጠ፣ በአስለቃሽ ጢስ እየታጠነ የአደባባይ ተቃዉሞዉን ቀጠለ።
የሱዳን ሐኪሞች የተሰኘዉ ስብስብ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ማሕበራት እንደሚሉት ከታሕሳስ 2018 እስከ ታሕሳስ 2022 በነበረዉ አራት ዓመት  ከ378 እስከ አምስት መቶ የሚደርስ ሰላማዊ ሰልፈኛ ተገድሏል።ከ3 ሺሕ በላይ ቆስሏል።
ከ90 በመቶ የሚበልጠዉን ሰልፈኛ የገደሉ፣ ያቆሰሉና ሴቶችን የደፈሩት አንድም የሱዳን ፖሊስ፣ ሁለትም ሁለቱ ጄኔራሎች የሚያዙዋቸዉ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦርና መከላከያ ጦር ባልደረቦች ናቸዉ።ሁለቱ ጄኔራሎች የአልበሽር ታዛዥ ሆነዉ ዳቦና ፉል ጥየቃ አደባባይ የወጣዉን ደሐ አስገደሉ፣የወታደራዊ ሁንታ መሪዎች ሆነዉ የተቃወማቸዉን ሰላማዊ ሰዉ አስገደሉ።ከቅዳሜ እስከ ዛሬ ደግሞ  በትንሽ ግምት መቶ ሰላማዊ ሰዎችን አስገደሉ።
                                             
የቀድሞዉ የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ ትናንት በሰጡት መግለጫ የሱዳን ሕዝብ ሚዚያ 2019 አምባገነኖችን ለመጨረሻ ጊዜ አሰናብቷል ይላሉ።«ዛሬ ምንም ነገር ቢሆን፣ ከሚያዚያ 2019ኙ ለዉጥ በኋላ ሱዳን ዉስጥ የበሩት ነገሮች እንደነበሩት አይቀጥሉም።አምባገነንን ተሰናብተናል።አንዳዴ መንገራገጭ፣ ወደ ኋላ መመለስና ማደናቀፍ ሊኖር ይችላል ግን በጭራሽ አንሸነፍም።» 

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦርምስል፦ Hussein Malla/AP/picture alliance
ኻርቱምምስል፦ Marwan Ali/AP/picture alliance

አምባገነን ቦርማ ነዉ ወይስ ፈንዝማ። የአልቡርሐን-ሐምዲቲ አገዛዝ  የመንገራገጭ፣መደነቃቀፉ ምልክት ይሆን? ወይስ ሐምዶክን ራሳቸዉን ጥቅምት 2021 ከስልጣን ያስወገዱት አል-ቡርሐን አምገነን አይደሉ ይሆን?
ከቅዳሜ ጀምሮ የሱዳን ከተሞችን የሚያጋየዉ ዉጊያ የአምባገነኖች የስልጣን ሽሚያ ዉጤት መሆኑ ምንም አላጠራጠራም።የሱዳን ሕዝብ አምባገነን ገዢዎቹን አስወግዶ አዳዲስ አምባገነኖችን ለማንገስ የስንት ወገኖቹን ሕይወት፣ደም አጥንት መገበር አለበት? ደግሞስ እስከ መቼ? እናዉቅም።የምናዉቀዉ ኻርቱሞች የነገ ከነግወዲያ መኖር አለመኖራቸዉን አለማወቃቸዉን ነዉ።እሳቸዉ፣ የዛሬ ንግግራቸዉ በፍንዳታ ድምፅ ይቆራረጣል።
«እስካሁን ደሕናነን።መብራት ግን ተቋርጧል።እንትን ነዉ----ኧረ ምን እደሆነም አላዉቅም።በመሐሉ ሰላማዊ ሰዎች የሚያልቁበት ዉጊያ ነዉ።እኛ  ጠቡን ምንም አናዉቅም።ይሕ ትክክል አይደለም።ላጭር ጊዜም ቢሆን የስኳር መድሐኒቴን ሳጣ በጣም ተጨንቄ ነበር።አሁን አገኘሁት አልሐም ዱሊላሕ»
ታላቅዩዉ በእስልምና ኃይማኖቱ ጠንከር፣በዘመናይ ትምሕርቱ ጠለቅ፣ በሐብቱ ደልደል ካለ ከሱፊ ቤተሰብ በ1960 ሰሜን ሱዳን ተወለደ።ወላጆቹ «አብዱል ፈታሕ» አሉት ስሙን።የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርቱን አጠናቅቆ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን ለቀጠል ከትዉልድ ቀበሌዉ ሼንዴይ ወደተባለችዉ ከተማ እንደሄደ ታናሽዬዉ ተወለደ።
የትዉልድ ቀን፣ወር ዓመቱ በዉል አይታወቅም።ለሱዳን ምናልባት ለኢትዮጵያም የትዉልድ ጊዜ አይደለም የጎሳ ማንነት እንጂ ተፈላጊዉ።1973፣በ1974 ወይም በ1975፣ ብቻ በሆነ ቀን፣ ባንዱ ዓመት፣ ካንዱ የዳርፉር ቀበሌ ግን ሪዚጋርት ከተሰኘዉ ከትልቁ የዳርፉር ጎሳ ተወለደ።«መሐመድ » ተባለም።
አጎቱ የጎሳ መሪ ነበሩ።መደበኛዉን ትምሕርት ሶስተኛ ክፍል ላይ አቁሞ እንደ-አባት አያት ቅድመ አያቶቹ ግመል ጥበቃ ሲጀምር አብዱል ፈታሕ ከካርቱሙ የጦር ኮሌጅ በመኮንነት ተመረቀ።
አብዱል ፈታሕ እንደ ወጣት የጦር መኮንን ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ሲዋጋ፣ሲያዋጋ አማን-ዮርዳኖስ፣ካይሮ-ግብፅ እየተጓዘ በወታደራዊ እዉቀት እየበሰለ፣ ማዕረግ እደራረበ ከጦር ኃይሉ አናት ሲንጠላጠል፣ መሐመድ ግመል እያረባ፣የግመል ወተት እየጠጣ፣ ግመል እየጋለበ፣ ግመል ላይ ሆኖ ተኩስ እየተለማመደ፣ ግመል እየነገደ የሱዳንና የቻድን ድንበር ይመላለስበት ያዘ።
በ2003 የዳርፉ አማፂያን በሱዳን ማዕከላዊ መንግስት ጦር ላይ ዉጊያ ሲከፍቱ አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን የሚያዙት ጦር አማፂያኑን ለመደምሰስ ዳርፉር ዘመተ።ወጣቱ መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ደግሞ እንዳደገ፣እንደኖረበት ጃንጃዊድ (ወይም ግመል ጋላቢ) ተዋጊዎች አለቃ ሆነ።አሚር።
በአብዛኛዉ የጃንጃዊድ ሚሊሺያዎችን የያዘዉ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር በ2013 ሲመሰረት ሐሚቲ የጦሩ አዛዥ፣አልቡርሐል አሰልጠኝና የበላይ ጠባቂ አይነት ሆነዉ ተመደቡ።ተዋወቁም።
አብዱል ፈታሕ ካርቱም ተመልሰዉ የሱዳን ምድር ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በነበሩበት በ2015  ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር የመንን ወረረ።የሳዑዲ አረቢያ መራሹን ጦር እንዲያግዝ ከሱዳን የሚዘምተዉን ተዋጊ ኃይል ለመመልመል፣ማስታጠቅ፣ ማዝመቱ ኃላፊነት ፕሬዝደንት አል በሽር ከሁለቱ ታዛዦቻቸዉ ሌላ ታማኝ ሰዉ አላገኙም ነበር።የሁለቱ ትብብርና ትዉዉቅም ተጠናከረ።
አልቡርሐን ፣የምድር ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምነትን፣ የጦሩ ጠቅላይ አዛዥነትን፤ የሱዳን ጦር ሠራዊት ዋና ተቆጣጣሪነትን ስልጣንን ተራበተራ እየተዉጣጡ ከብርጌድየር ጄኔራልነት ወደ ሉትናንት ጄኔራልነት ሲመነጉ፣ ሐምዲቱ ባጭር ጊዜ ሜጄር ጄኔራል ሆነዉ አረፉት።
ሁለቱ ጄኔራሎች ከ2018 ማብሪያ ጀምሮ በየከተማዉ የተደረገዉ ያደባባይ ሰልፍና ሕዝባዊ አመፅ የአልበሽርን የስልጣን ክር ቀስበቀስ እየበጣጠሰ የ30 ዓመቱን አገዛዝ ከፍፃሜ ማድረሱን በየፊናቸዉ ሲያዉቁ አልበሽርን ትተዉ ከአመፀኛዉ ጎራ ቆሙ።
አልበሽርን ያስወገዱት የያኔዉ መከላከያ ሚንስትር አዋድ ኢብን አዉፍ የአንድ ቀን ስልጣናቸዉን ሲለቅቁ የተሰየመዉ ወታደራዊ ምክር ቤት መሪዎች ሆኑ።ሚዚያ 12።2019።አል ቡርሐን።
«የሲቢል መንግስት ይመሰረታል።ሁሉም ወገኖች ተስማምተዉበታል።የጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደሩ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ በመመስረት የሲቢል መንግስቱን ይመሰርታል።የሽግግር ወቅቱ ቢበዛ ከ2 ዓመት መብለጥ የለበትም።በዚሕ ጊዜ ዉስጥ ወይም በስተመጨረሻዉ ሕጥቡ ለሚመሰርተዉ የሲቢል መንግስት፣ ጦር ኃይሉ ስልጣኑን ያስረክባል።»
ቃል ግን በነነ።የኢትዮጵያ፣የሳዑዲ አረቢያ፣ የግብፅ፣የአሜሪካ የኖርዌ፣ የብሪታንያ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣የአፍሪቃ ሕብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  ዲፕሎማቶች ለተከታታይ ወራት ለፍተዉ የተመሰረተዉ የሲቢል-ጦር ኃይል ቅይጥ አስተዳደርም ጥቅምት 2021 አል-ቡርሐን በመሩትመፈንቅለ መንግስት ተወገደ።
ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክን ከስልጣን ያስወገደዉን መፈንቅለ መንግስት ሐምዲቲ ባለፈዉ የካቲት «ስሕተት» አሉት።የሐምዲቲ መልዕክት በአል-ቡርሐን ላይ የማገንገናቸዉ ምልክት መሆኑን የተረዱት ጥቂቶች ናቸዉ።
ለነገሩ፣ የኻርቱም የጦርም ሆነ፣የሲቢል ልሒቃን ሐምዲቲን ያልተማረ፣ ገጠሬ፣ዘላን የፖለቲካ ጥበብ የማይገባዉ---እያሉ ያሟቻዋል።ይንቋቸዋልም ።በርግጥም ከ3ኛ ክፍል ሌላ የሚመዙት ሰርቲፊኬት የላቸዉም።
ከዳርፉር በረሐ የወርቅ ጉርጓድ እስከ ኻርቱም ባንኮች፣ ከእንዱሩማን መደብሮች እስከ ዱባይ ሕንፃዎች የተዘረጋዉ ኩባንያቸዉ ግን ከጥቂት የሱዳን ቱጃሮች አንዱ ያደርጋቸዋል።የሚያዙት ፈጥኖ ደራሽ ጦርም ከመቶ ሺሕ ይበልጣል።
ከአልቡርሐን ጋር የተጣሉበት ዋናዉ ምክንያትም ታማኝ፣ ታዛዥ ጦራቸዉ በሁለት ዓመት ዉስጥ ይበተን የሚለዉ ዕቅድ ነዉ።ሐምዲቲ ጦሩ የሚበተንበት ጊዜ ቢያንስ 10 ዓመት እንዲሆን ይሻሉ።
ልዩነቱ እየከረረ ሲሄድ የድሮዉ ግመል ጋላቢ የሱዳንን ፕሬዝደንታዊ ፅሕፈት ቤት፣ ቴሌቪዥን ጣቢያዉን፣ አዉሮፕላን ማረፊያዉን ጨምሮ የኻርቱምና የሌሎች ትላልቅ ከተሞችን ስልታዊ ተቋማት አስከበቡ።
የመጀመሪያዉን ጥይት የተኮሰዉ ወገን ማንነት ግን በዉል አይታወቅም። ቅዳሜ ማለዳ ላይ ግን የሱዳን ከተሞች በመድፍ አዳፍኔ፣ በጄት-ሞርታር ቦምብ አረር  ያርሩ ገቡ።ዛሬም አልበረደም።የአረብ ሊግ፣የአፍሪቃ ሕብረት፣የአዉሮጳ ሕብረት፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያ፣ ግብፅ ሌሎችም መንግስታት ሁለቱ ወገኖች ዉጊያዉን እንዲያቆሙ እየጠየቁ ነዉ።
የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነመንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ሁለቱን ጄኔራሎች እንዲያነጋግሩ የሶስት ሐገራት መሪዎችን ወደ ኻርቱም ልኳል።የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ኑር መሐመድ ሼኽ እንዳሉት የሶስቱ መሪዎቹ ተልዕኮ ሁለቱ ጄኔራሎች ባስቸኳይ ተኩስ አቁመዉ እንዲደራደሩ መጠየቅ ነዉ
«ርዕሳነ ብሔራቱ ጄኔራል ቡርሐንና ጄኔራል ሐምዲቲን ያነጋግራሉ።ሶስት ፕሬዝደንቶችን የያዘ ኮሚቴ ነዉ።እነሱም የደቡብ ሱዳኑ ሳልቫ ኪር፣ የጅቡቲዉ ፕሬዝደንት ዑስማኤል ዑመር ጌሌ እና የኬንያዉ ዊልያም  ሩቶ ናቸዉ።»
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ምምሻዉን ይሰበሰባል።ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ዛሬ በሰጡት መግለጫ «ዕብደት» ያሉትን የአል ቡርሐንን ርምጃን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያስቆም ጠይቀዋል።ጄኔራል አል ቡርሐን ግን ከፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዦች ጋር ንግግር ብሎ ነገር አይኖርም ይላሉ።

የቀድሞዉ የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክምስል፦ Amr Alfiky/REUTERS
ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሕምዲቲ) ምስል፦ Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance
ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን (እጃቸዉን ያነሱት)ምስል፦ Sudan Sovereignty Council Press Office/AA/picture alliance
ከግራ ወደ ቀኝ ሐምዲቲ፣አል ቡርሀንና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችምስል፦ Cem Ozdel/AA/picture alliance

በዉጊያዉ አዉድ ሁለቱም ወገኖች ድል መቀዳጀታቸዉን፣ በተለይ ኻርቱም የሚገኙ የጦር ኃይል ምሽጎችን፣ አዉሮፕላን ማረፊያዎችና የመንግስት መስሪያ ቤቶችን መቆጣጠራቸዉን በየፊናቸዉ ያዉጃሉ።ዕዉነቱ አይታወቅም።ኻርቱም ግን በርግጥ የሕንፃ ፍርስራሽ፣ ቀለሕ፣ትቢያ ተከምሮባት ጢስ-ጠለስ አስደንጋጭ ድምፅ ታገሳለች።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW