1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲቪል ማሕበራት እና አመራሮቻቸው እየገጠማቸው ያለው ችግር

ረቡዕ፣ ኅዳር 18 2017

የሲቪል ማሕበራትና አመራሮቻቸው በፀጥታ አካላት «በአካልና በስልክ ተደጋጋሚ ወከባና ማስፈራሪያ» እየደረሰባቸው መሆኑን እንደገለፁለት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል አመለከተ። ይህን «ዛቻና ማስፈራሪያ በመሸሽ ከአገር ለመሰደድ የተገደዱ» መኖራቸውንም አስታውቋል።

አርማ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል አርማ ፎቶ ከማኅደር ምስል EHRDC

የሲቪል ማሕበራት እና አመራሮቻቸው እየገጠማቸው ያለው ችግር

This browser does not support the audio element.

 

የሲቪል ማሕበራት እና አመራሮቻቸው በፀጥታ አካላት «በአካልና በስልክ ተደጋጋሚ ወከባና ማስፈራሪያ» እየደረሰባቸው መሆኑን እንደገለፁለት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል አመለከተ። ይህን «ዛቻና ማስፈራሪያ በመሸሽ ከአገር ለመሰደድ የተገደዱ» መኖራቸውን ያስታወቀው ድርጅቱ አሁንም በሥጋት ላይ የሚገኙ እንዳሉ ጠቅሶ ሰሞኑን ከዓላማቸው ውጭ ተንቀሳቅሰዋል በሚል የታገዱት የሦስት ሲቪል ድርጅቶች ጉዳይ የሲቪል ምህዳሩን እንዳያጠብ ሥጋቱን ገልጿል። በጉዳዩ ላይ መግለጫ ያወጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለድርጅቶቹ መታገድ የቀረቡት ምክንያቶች ግልጽ ያልሆኑ እና ያልተረጋገጡ ክሶች መሆናቸውን በማመልከት እርምጃውን አውግዟል። መሰል ምክንያቶች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ለማፈን በመሳሪያነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን በመግለጫው ያመለከተው ዓለም አቀፉ የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግሥት እገዳዎችን በአስቸኳይ ሊቀለበስ ይገባል ብሏል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ያወጣው መግለጫ እና ሥጋቱ

«ሐሳብን የመግለጽ እና ሌሎች መሠረታዊ የዜጎች ነጻነቶችና መብቶች ያለአግባብ በሚገደቡበትና በሚጠቡበት ዐውድ የዜጎች ተሳትፎ እንዲኮስስ ከማድረግም ባለፈ ለግጭቶች መበራከት፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ መጓደል፣ ለድህነት መንሰራፋት፣ ለተጠያቂነት መጥፋት» ይዳርጋል ያለው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል፤ የሲቪክ ምህዳሩን ሊያጠቡና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ምልክቶችን እያየን በመሆኑ መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ሲል አሳስቧል። የሲቪክ ድርጅቱ ትናንት ያወጣውን መግለጫ በተመለከተ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም እንዲህ ያሉት ሕጋዊ ሂደቶችን ያልተከተሉ እግዶች ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መበራከት እና ለዴሞክራሲ መቀጨጭ በር ይከፍታሉ ብለዋል።

«በሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችላይ እንደ ድርጅት እና በሠራተኞቻቸው ላይ፣ በግል የሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የመብት ተሟጋቾች ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ጥቃቶች፣ እርምጃዎች የሲቪክ ምህዳሩን ክፉኛ እየጎዳው እና እያጠበበው መሆኑ እና ይህ ነገር በጊዜ የማይገታ ከሆነ ተነቃቅቶ የነበረው የሲቪክ ምህዳር እንደገና ሌላ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ለማሳሳብ ነው» ይህን መግለጫ ያወጣነው ብለዋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መለያ አርማፎቶ ከማኅደር ምስል Pond5 Images/IMAGO

በጉዳዩ ላይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ምን አለ?

ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ «ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን ሲገባቸው፣ ከዓላማቸው ውጭ በመንቀሳቀስ የአገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት ላይ ተሠማርተዋል» በሚል ምክንያት የታገዱት የሲቪክ ድርጅቶች በሚመለከት መግለጫ ያወጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናል እግዶቹ «ግልጽ ያልሆኑ እና ያልተረጋገጡ ክሶችን ተመስርተው» የተወሰዱ፣ ውንጀላዎችም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ለማፈን በመሳሪያነት ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑን ጠቅሶ እገዳዎቹ በአስቸኳይ ሊቀለበሱ ይገባል ብሏል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን አካሄድ በአስቸኳይ በድጋሚ በመከለስ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች የትጥቅ ግጭቶችን ተከትሎ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት፣ ለመመዝገብ እና ማስረጃዎችን የማቆየት ዘዴን ለመዘርጋት እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበትም በመግለጫው ጠቅሷል። 

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋን ጨምሮ ሌሎች የሲቪክ ድርጅት መሪዎች ከሀገር መሰደዳቸውንም ገልፀዋል። «በርካታ የሚሆኑ የሲቪክ ድርጅት መሪዎች፣ ሠራተኞቻቸው በተለያየ መንገድ በፀጥታ አካላት ወከባ፣ ክትትል፣ ማሳደድ፣ ማስፈራራት ይደርስባቸው እንደነበር ለጽሕፈት ቤታቸን ቀርበው በጽሑፍም በቃልም አቤቱታ አቅርበው ነበር።» ብለዋል።

መሰል እርምጃዎች የሲቪክ ምህዳሩን እንዳያጠቡ ሥጋት ፈጥራል

ማዕከሉ የሚደርሱ ጫናዎችና እገዳዎች «የሲቪል ማኅበረሰቡን ምህዳር የሚያጠቡ፣ በቀሩት የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ዘንድ ፍራቻን የሚፍጠሩ እና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚያደርጓቸውን ንቁ ተሳትፎዎችንም እጅግ የሚያኮስሱ ናቸው» ብሎ እንደሚያም አስታውቋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች ከመንግሥት ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ለሰብአዊ መብቶች ቅድሚያ መስጠት እንደሚኖርናቸው በመግለጫው ጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስለ ሲቪክ ድርጅቶች 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ «ለውጡና የለውጡ ፍሬዎች» ሲሉ ትናንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጾቻቸው ባሰራጩት ዘለግ ያለ ጽሑፍ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት ላይ የነበረውን «የተንሸዋረረ» ያሉት አመለካከት ተስተካክሎ «የታሠሩበት ቀፍዳጅ ሕግ በለውጡ ተሻሽሏል» በማለት የድርጅቶቹ ቁጥር መጨመሩንም አመልክተዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW