የሲቪሎች ግድያ መቀጠል፤ ለ«ጦርነት ይቁም» ጥሪ የተጠራው ሰልፍ፤ የብር አቅም
ዓርብ፣ ኅዳር 28 2016የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ ባወጣው መግለጫ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በኦሮሚያ ክልሎች፣ በኅዳር ወር ውስጥ ብቻ በሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ 56 ሰዎች፣ በዐማራ ክልል ደግሞ በርካቶች መገደላቸውን አመልክቷል። መረጃውን ከተከታተሉት ሰሎሞን ካሣ፤ «የሲቪሎችን ስቃይ መስማት በጣም ያሳዝናል።» ሲሉ፤ እዩኤል ንጉሤ በበኩላቸው፤ «ኢትዮጵያ ማለት ባጠቃላይ የመከራ ሀገር ማለት ነው ቢባል ይቀላል፣ እሮሮ ሳይሰማ ውሎ ሚያድረበት ጊዜ የለም።» ማለት ይኽን በመሰለው ዘገባ መታከታቸውን ጠቁመዋል። ምናለ ይበልጣልም እንዲሁ፤ «አሁን እኛ የፈልግነው መፍትሄ ነው፤ ሁልግዜ የዜጎችን ሞት መስማት» ሲሉ ነው እንዲህ ያለው ዜና መደጋገሙን በማመልከት መፍትሄ የጠየቁት።
ኢድሪስ መሀመድ ደግሞ፤ «የጥቃቱ አቀናባሪ ስርአቱ ውስጥ ያሉ የአካባቢው አመራሮች መሆናቸው ከቸልተኝነታቸው ሲታይ ግልፅ ነው። ሸኔ የሚለው ዜማ የተነቃበት ቀልድ አንድ ቀን ለሁሉም ይገለጣል» ነው የሚሉት። ጎበና በሻህ ሹሮሞም፤ «መንግሥት ተብዬው ይሄው አምስት ዓመት የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ አልቻለም ወይም ሆን ብለው ነው።» የሚል ተቀራራቢ አስተያየታቸውን በማኅበራዊ መገናኛው አጋርተዋል። ጆም ጆ ጀምስም እንዲሁ፤ «ይኽ መንግሥት ከመጣ ጀምሮ 1,2 ሚሊየን ሲቪሎች ተገድለዋል፤ ወይም ሕይወታቸውን ከጥቃት ለመከላከል አልቻለም።» ብለዋል። እማይ ዜና በበኩላቸው፤ «ኦሮሚያ የሚባል ቦታ የንጹሃን መታረጃ ከሆነ ሰነባብቷል። በሰላማዊ ሰልፍ ሰላም ለማግኘት የተደረጉ ጥረቶች በአገዛዙ እብሪት አልተሳኩም። ይባስ ብሎ በድሮንና በመድፍ ንጹሃንን እየጨፈጨፈ ነው።» በማለት ሰፋ ያለ አስተያየታቸውን አጋርተዋል። አበበ ታምሩ፤ «በሀገራችን ላይ የመጣው መከራ በታሪክ ላይ የለም» ይላሉ። ትዕዛዙ ደጉ ግን፤ «ኢትዮጵያ ወደ አምላክሽ ጩኺ ህዝብሽ በርሀብና በጦርነት አለቀ ደቀቀ» በማለት ለችግሩ ምድራዊ መፍትሄ ይገኛል የሚል ተስፋቸው መሟጠጡን አመላክተዋል።
ለፊታችን እሑድኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. «ጦርነት ይቁም ሰላም ይሰፈን» በሚል መሪ ሃሳብ አዲስ አበባ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ የጠሩት ወገኖች ከመንግሥት ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው ይፋ አድርገዋል። ሰልፉን የሚያስተባብሩት ፖለቲከኞች፣ ሲቪል ተቋማት እና በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች መሆናቸውን የሰልፉ አዘጋጆች ገልጸዋል። የሰልፉን መካሄድ የደገፉም፤ መደረግ የለበትም ያሉም አሉ። ከእነዚህ መካከል ታደሰ ኃይሌ ቀና ሰው፤ «ሁሉም እሚደግፈው ሀሳብ ነው፡ ጦርነት ይቁም፡ አንድም እቤት ሚቀር የለም፡ ጦርነት ይብቃን አገሽግሾናል።» ነው የሚሉት፤ መስፍን ሰሎሞን ደግሞ፤ «የኑሮ ዉድነት ጉዳይስ? የሙስናና መልካም አስተዳደር እጦት» በማለት አሉ ያሏቸውን ችግሮች አብረው እንዲነሱ አክለዋል። ናስር ጀማል በበኩላቸው፤ «ሰልፉማ ግድ እና ግድ ነው፣ ሲቀጥል ማንም የመከልከል ስልጣን የተሠጠው አካል የለም፣ ማሳወቅ ብቻ ነው ግዴታው።» ይላሉ።
ባይሳ ዳዲ፤ «ጦርነቱ እየተካሄደ ያለው በባሕርዳር ስለሆነ ሰላማዊ ሰልፉም እዚያው ይደረግ!» ባይ ናቸው። ሙሳ ኤልያስም የሃሳባቸው ደጋፊ ናቸው፤ «ሄደው እዚያ ጦርነት በለባት ቦታ ሰልፍ ያድርጉ 4 ነጥብ» በማለት። ባሻ የዤሎይ በበኩላቸው፤ «የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6 2015 6.4 ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፈቃድ ውጪ ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለ ነው።» በማለት ሕግ ይጠቅሳሉ። ቢም ቦኬ ዎን የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛው ተጠቃሚ የሰልፉን አለመፈቀድ በማስመልከት፤ «ከወያኔ የባሰ ብልፅግና ፈሪ ሆኑዋል» ነው የሚሉት፤ ሲሳይ ተሰማ ደግሞ፤ «እኔ አልገባኝም መንግሥት ጦርነት ይፈልጋል ማለት ነው ወይስ ሌላ?» በማለት ይጠይቃሉ። አማኑኤል ጌታሁን ዘላለም አስተያየት ደግሞ ይለያል፤ «ባክህ አትጃጃሉ መንግሥት ነው ሰልፉን የጠራው ድራማ ሲራ ነው ያለ አብይ ፍቃድ ሰልፍ ማድረግ እንደማይቻል ይታወቃል፤» ሄኖክ ካሰኝም ይህን ይጋራሉ፤ «ብልፅግና እራሱ በጠራው ሰልፍ እራሱ ከለከለ ያመቱ ምርጥ ቀልድ» ነው ያሉት። አብዲ እንዳለው ግን፤ «ኢትዮጵያ ውስጥ ሰልፍ ለስኳር እና ለዘይት ብቻ ነው የሚፈቀደው፤ አታስቡ።» ብለዋል። ማራኪ ማራኪ በበኩላቸው፤ «ፋኖ ትትቅ ይፍታ ይሚል ከሆነ ይሰለፉ።» ባይ ናቸው።
አማራ ደመላሽ ደግሞ፤ «አዲስ አበባ ላይ ኅዳር 30 "ሰላም ይሰፈን ጦርነት ይቁም" ብለው ሰልፍ ይወጣሉ ተብለው የተጠረጠሩ ወጣቶች በጅምላ እየተሰሩ ነው።» በማለት መረጃ አጋርተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መገበያያ ገንዘብ፤ ብር ከዕለት ወደ ዕለት የመግዛት አቅሙ መቀነሱ ሸማቾችን እያሳቀቀ ባለበት በዚህ ወቅት የውጭ ሃገራት ገንዘብ የብር ምንዛሪን በተመለከተ ሰሞኑን ወጡ መረጃዎች በማኅበራዊ መገናኛው የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምንም እንኳን ባለፈው ሳምንት ለምክር ቤት ባቀረበው የእቅድ አፈጻጸም ዘገባው የምንዛሪ ለውጥ ስለማድረግ የገለጸው ነገር አለመኖሩን ባወጣው መግለጫ ቢያሳስብም ጉዳዩ ግን ትኩረት ስቧል። ነገሩ ካሳሰባቸው መካከል መክሊት ጌታቸው፤ «የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እባክህ ምንም እንኳን የውጪ ገንዘብ እጥረትም ሆነ ከዓለም ባንክም ሆነ ከዓለም የገንዘብ ተቋም IMF ጫና ቢኖርም የብርን ዋጋ በዚህ ወቅት ዝቅ አታድርግ። በዚህ የፋይናንስ ኪሳራ ወቅት ገንዘብም አታትም፤ ከዚህ ይልቅ የኤኮኖሚ ግሽበት መቆጣጠሪያ ስልት ተጠቀም። እርግጥ ነው የመንግሥት ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እንዲህ ባለ ጊዜ እንደሚኖር አውቃለሁ፤ ነገር ግን ኃላፊነታችሁን በሚቻላችሁ በአግባቡ ተወጡ።» በማለት መክረዋል። አበበ ታምሩ በበኩላቸው፤ «እውቀቱ እያላቸው ስለሚፈሩ ብቻ አይሆንም ማለት አቅቷቸው ወገናቸው ላይ የተዛባ ተግባር የሚፈፅሙትን ስታይ ታዝናለህ፣» ይላሉ። ተካልኝ በለጠም፤ «በዚህ ሰዓት ይህ ቢደረግ የእብድ ውሳኔ ነው የሚሆነው።» ነው የሚሉት።
በልክ ኤ በልክ፤ «መደረጉን ይደረጋል ያው ወሬው ቀድሞ ስለተሰራጨ በገበያው ላይ መናጋትና ህዝባዊ ቁጣ ይቀሰቅሳል በሚል የጭንቅ ማስተባበይ ነው!» በማለት የተባለው ቢዘገይም መደረጉ አይቀርም የሚል አስተያየት ነው ያጋሩት። ዝይን ኑር ካሣ ግን፤ «ችግሩ ባንክም ምንዘሪ ሲጨምር ብላክ ማርኬቱም አንደዛው የጫምረል» ባይ ናቸው። በላይነሽ ጋሻውም እንዲህ ነው የሚሉት፤ «እስኪ ለአንድ ቀን 100አስገቡትና በኢትዮጵያ ምድር ስንት ዶላር እንዳለ እዩት።» አበቃ ዘመኑ በበኩላቸው፤ «ለውጥ ቢደረግ ኑሮ ህዝብ ይከብድና እራስ በእራሳችን እንባላለን የሚሆን ይሄ ነበር።አሁን እንኳን በአዲስ አበባ በቀን አንዴ የማይበላ ብዙ ነውና።» በማለት ስጋታቸውን አጋርተዋል። የእናት ውለታም፤ «የኢትዮጵያ ህዝብ የኑሮው ውድነት በራሱ 3ኛ የዓለም ጦርነት ሆኖበታል!!» ሲሉ ነው ችግሩን የገለጹት፤ በዚሁ የዕለቱን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት እናብቃ።