1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፓርቲዎች ነቀፌታ በሕገ መንግሥት ጥናት ዙሪያ

ዓርብ፣ ግንቦት 25 2015

የሲዳማ እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ፓርቲዎች ባወጡት መግለጫ የጥናቱን ውጤት ከእውነታው ጋር የሚጋጭ እና የአንድ ጎራ አስተሳሰብ ሰለባ ሲሉ ነቀፈውታል።፡ ጥናቱ ሁሉም ሀሳቦች በእኩል የተስተናገዱበት መሆኑን የሚናገሩት የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ተቋም አጥኚ ቡድን አባላት በበኩላቸው የፓርቲዎቹ ውንጀላ አግባብነት የሌለው ነው ብለዋል ፡፡

Äthiopien | Sidama Partei
ምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ተቋም  ላለፉት 30 ዓመታት ገደማ ሲያገለግል በቆየው ኢፌድሪ ህግ መንግስት ዙሪያ  ያካሄደው የዳሰሳ ጥናት ነቀፌታ እየቀረበበት ይገኛል ፡፡ ተቋሙ ጥናቱን ያካሄደው ለብሄሮች የመገንጠል መብትን የሚፈቀደውን አንቀጽ 39ን ጨምሮ  አንዳንድ የህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሻሻያ ያስፈልጋቸዋል ወይስ አያስፈልጋቸውም በሚሉ መጠይቆች ላይ ነው፡፡

ተቋሙ  በአሃዛዊ መረጃዎች በማስደገፍ ያካሄደውን የጥናት ውጤት  ሰሞኑን ይፋ ካደረገ በኋላ  በተለይ በሲዳማ እና በኦሮሞ ፌዴራሊስት ፓርቲዎች ተቃውሞ ገጥሟታል ፡፡ ፓርቲዎች በየበኩላቸው ባወጡት መግለጫ በተቋሙ ተጠንቶ ይፋ የተደረገው የጥናት ውጤት የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ያላስገባና የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ አካላትን ያላሳተፈ ነው ብለዋል ፡፡

በተለይም የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ትናንት ባወጣውና በፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ በአቶ ፃዲቁ ሙሴ በተነበበው መግለጫ ጥናቱ አሁን በአገሪቱ ለሚታዩት ችግሮች በሙሉ ህገ መንግሥቱን ብቻ ተጠያቂ ያደረገና የአንድ ወገን የፖለቲካ ትርክት ሰለባ የሆነ ነው ሲል ነቅፏል፡፡ በህገ መንግሥቱ ከተቀመጡት መብቶች መካከል ሦስት አራተኛው የግለሰብና የቡድን መብቶች መሆናቸውን የጠቀሱት የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ ኤሊያስ በበኩላቸው ነገር ግን በጥናቱ መንካት የተፈለገው ሌላ ነገር ነው ብለዋል፡፡

ምስል Solomon Muchie/DW

በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ባካሄደው ጥናት  የአጥኝው ቡድኑ አባላት ከሆኑት አንዱ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ደሳለኝ  ሃምሳሉ በጥናቱ ሁሉም ሀሳቦች በእኩል የተስተናገዱበት ነው ይላሉ  ፡፡የፓርቲዎቹ ውንጀላ አግባብነት የሌለው ነው ሲሉ የጠቀሱት  ዶክተር ደሳለኝ “ ጥናቱ ወደ አንድ ወገን ያደላ አይደለም ፡፡ በጥናቱ በዋናነት የተነሱት ሦስት አማራጮች ናቸው ፡፡ የህገ መንግሥት ድንጋጌዎቹ ምንም ሳይሻሻሉ እንዳለ ይቀጥሉ ፣ ለመወሰን አስቸጋሪ በመሆኑ ተጨማሪ መረጃዎች እንዲቀርቡ ሀሳብ የሠጡና እንዲሁም ማሻሻያ ያሥፈላጋቸዋል የሚል ናቸው ፡፡ ይህም ወደአንድ ወገን ብቻ ያደላ መሆኑን አያሳይም “ ብለዋል ፡፡

በተቋሙ የተካሄደው ጥናት የብሄሮች መብት ለመገደብና ህገ መንግሥቱን ለማሻሻል ተደርጎ በተለያዩ አካላት የሚቀርበው ትችት ከእውነታው የራቀ መሆኑን የጠቀሱት  ዶክተር ደሳለኝ  “ ጥናቱ ምንም አይነት የፖለቲካ አጀንዳ የሌለውና በተቋሙ ተነሳሻነት ብቻ የተካሄደ ነው ፡፡ የጥናቱ መነሻውም ሆነ ውጤቱ የአገሪቱ ችግሮች ምክንያት ህገ መንግሥቱ የሚል  ድምዳሜ የያዘ አይደለም “ ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ፖለቲከኞች እና ሊህቃን ህገ መንግሥትን ፤ ሠንደቅ ዓላማንና ታሪክን ጨምሮ መሠረታዊ በሚባሉ በበርካት አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ሥምምነት እንደሌላቸው ይታወቃል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW