የሲዳማ ክልል ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ዉዝግብ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 4 2016
የሲዳማ ክልል ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ፣ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ መሪዎች በሥልጣን ይገበኛል ሰበብ ለሁለት መከፈላቸዉን የሚያመለክት መግለጫዎች እያወጡ ነዉ።የፓርቲዉ ሊቀመንበር ከሐገር ወጥተዋል።የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶ እና የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የአደረጃጀት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ደምሴ የሚመሯቸዉ ፖለቲከኞች ግን አንዳቸዉ ሌላቸዉን እየወቀሱ ነዉ።የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ፓርቲው አለኝ የሚለውን የዲሰፕሊን ጉዳይ በጠቅላላ ጉባኤው ሊያይ ይገባል ሲል ጠቁሟል፡፡
የሲፌፓ አመራሮች ውዝግብ
በሲዳማ ክልል ዋነኝ የተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ ኤሌያስ “ ለደህንነቴ ያሠጋኛል “ በሚል ከአገር የወጡት ከወራት በፊት ነበር ፡፡ የሊቀመንበሩን ከአገር መውጣት ተከትሎ ግን በቀሪ የፓርቲው አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት አሁን ላይ እየሰፋ የመጣ ይመስላል ፡፡
አለመግባባቱ የተከሰተው በፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶ እና በምክትል ሊቀመንበርና የአደረጃጀት ጉዳይ ሃላፊው አቶ ደሳለኝ ደምሴ መካከል ነው ፡፡ በፓርቲው ህገ ደንብ ሊቀመንበሩ በሌሉበት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ ሥራውን ተከቶ እንደሚሠራ መደንገጉን የጠቀሱት የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶ “ ነገር ግን አቶ ደሳለኝ ደምሴ በሊቀመንበሩ ይሁንታ ብቻ በውክልና መቀመጣቸው ህጋዊነት የለውም ፡፡ በመሆኑም በህጉ መሠረት ፓርቲውን የመምራት ሃላፊነት የእኔ ነው “ ሲሉ ዛሬ በፓርቲው ጽህፈት ቤት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል ፡፡
የሥነ ምግባር ጥሰት ክስ
በፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የአደረጃጀት ጉዳይ ሃላፊው አቶ ደሳለኝ ደምሴ የሚመራው ቡድን የተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶን አመራርነት አይቀበልም ፡፡ አቶ ጴጥሮስ የፓርቲውን መረጃ ለገዢው ፓርቲ አሳልፈው በመስጠት ፓርቲውን ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸው ጉዳያቸው በዲስፕሊን እየታየ የሚገኙ ናቸው ሲሉም ይከሳሉ ፡፡ የፓርቲውን ጽህፈት ቤት በጉልበት ሰብሮ የገባ ወንጀለኛ እንጂ የፓርቲው ህጋዊ አመራር ሊሆን አይችልም ፡፡ አቶ ጴጥሮስ ይህን ፈጽመዋል በማለት የፓርቲው ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገነነ አሳና ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል ፡፡
የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶ ግን “ ይህ ሥም ማጥፋት ነው “ በማለት ውንጀላውን አጣጥለዋል ፡፡ ከሌላ አካል ተልዕኮ ተሰጥቶት ይንቀሳቀሳል የተባለው ፍፁም መሠረተ ቢስ ነው ያሉት አቶ ጴጥሮስ “ ይህን የሚሉት የእኔን ሥም በማጠልሸት አግባብ ያልሆነ ድጋፍ ለማሰባሰብ ነው ፡፡ፓርቲው መፍረስ ካለበትም ሊያፈርስ የሚችለው ጠቅላላ ጉባዔው ብቻ ነው “ ብለዋል፡፡
አቤቱታ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ
የፓርቲው ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገነነ አሳና በህግ ወጥ መንገድ ፓርቲውን ሊያፈርሱ ነው ያሏቸው የተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶን ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይዳኘን ሲሉ መጠየቃቸውንም ተናግረዋል ፡፡ የተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶ ግን ሥልጣኑን የሠጠኝ ጠቅላላ ጉባዔው እንጂ ምርጫ ቦርድ አይደለም ፤ ምርጫ ቦርድ ታዛቢ ነው ሲሉ ይሞግታሉ ፡፡
ዶቼ ቬለ በሁለቱ የፓርቲው አመራሮች መካካል ሥላለው አለመግባባት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮችን አስተየያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት ሃላፊዎቹን ማግኘት ባለመቻሉ ሊሳካ አልቻለም ፡፡ያምሆኖ ቦርዱ መስከረም 2 ቀን 2016 ዓም በቁጥር 1162 ህዝባር 13 89 ለፓርቲው በጻፈው ድብዳቤ ፓርቲው አለኝ የሚለው የዲሰፕሊን ጉዳይ በጠቅላላ ጉባኤው ሊታይ እንደሚገባው ጠቁሟል፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ