የሲፒጄ መግለጫ እና የባለሙያዎች አስተያየት
ረቡዕ፣ ሐምሌ 27 2014
"ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከኤርትራ ጋር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች በከፋ ደረጃ ጋዜጠኞችን የምታስር ሀገር ናት"
ሲል የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ ( CPJ ) ትናንት ባወጣው ዘገባ አመልክቷል።
ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ የተቀሰቀሰው ጦርነት በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ላይ ጥላ እንዲያጠላ ማድረጉንም ሲፒጄ አትቷል።
"በሁሉም ደረጃ የሚሠሩ ባለሥልጣናት ጋዜጠኞችን በሥራቸው ምክንያት ማሰር ማቆም አለባቸው ያለው ሲፒጄ ይህም ባለሙያዎች በሥራቸው ምክንያት የሚፈጠረባቸውን የፍርሀት ዳመና ለመግፈፍ ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብሏል። ዶይቼ ቬለ ( DW ) ያነጋገራቸው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ እና ጋዜጠኛ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ "ወገንተኛነት" የሚንፀባረቅበት ጋዜጠኝነት መኖሩን እና በጋዜጦች እና በማሕበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች የመንግሥት ወይም የሕዝብ ከሚባሉት መደበኛ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በተለየ ለእሥር እና እንግልት እንደሚዳረጉ ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሳንሱር ከሚደረግባቸው አገሮች አንዷ ነበረች" ያለው ሲፒጄ የኢንተርኔት አገልግሎት መዘጋት እና ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረው የጸረ ሽብር ሕግ የጋዜጠኞችን መብት በተመለከተ ለዚህ ድምዳሜው ምክንያት መሆናቸውን አስታውሷል። የሰሜን ኢትዮጵያን የጦርነት ትርክት ለመቆጣጠር የሚደረገው ትግል በብዙኃን መገናኛ ላይ እየጨመረ ነው ላለው ጥላቻ ዋና ምክንያት መሆኑንም ዘርዝሯል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ጋዜጠኞች ታስረዋል?
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከህዳር 4 ቀን 2020 ጀምሮ ቢያንስ 63 ጋዜጠኞች እናየመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች መታሰራቸውን ሲፒጄ ዘግቧል። ከነዚህም ውስጥ ስምንቱ እስከ ትናንት ነሐሴ 1 ቀን ድረስ በእሥር ላይ መሆናቸውን እና እሥሩ ከመዲናዋ አዲስ አበባ እስከ ኦሮሚያ ክልል ፣ ከአማራ እስከ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች ድረስ የዘለቀ መሆኑን እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በትግራይ ክልል መስተዋሉን ጠቅሷል።አብዛኛዎቹ ታሳሪ ጋዜጠኞች ተመሳሳይ ክስተት እንደሚገጥማቸው የገለፀው ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም ሲፒጄ የመንግሥትባለስልጣናት ጋዜጠኛችን ወይም የመገናኛብዙኃንሠራተኛን ከያዙበኋላ ፍርድ ቤት አቅርበው ለምርመራ ብዙ ጊዜ
እንደሚወስዱባቸው ፍርድ ቤቶች የዋስትና መብት ሲሰጡ፣ ፖሊሶች የጋዜጠኞቹን መፈታት የሚያዘገዩ ይግባኞችን በተደጋጋሚ እንደሚያነሱ መታዘቡን ገልጿል። በሌላ በኩል አንዳንድ ጋዜጠኞች ቤተሰብም ሆነ የሕግ አማካሪ በማያገኙበት ሁኔታ ይታሰራሉ ሲል አብነቶችን ጠቅሶ አስረድቷል።
አስፍሯል።በአዲስ አበባ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል አስተማሪ የሆኑት ዶክተር ተሻገር ሽፈራው ኢትዮጵያ ውስጥ " ማጠቃለል እንኳን ባይቻልም ሁሉም ወገንተኛ ጋዜጠኝነትን ነው እያራመደ ያለው" በማለት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን የሥራቸውን ደረጃ ያሳያሉ።
"ውስን ጋዜጦች እና ራዲዮ ጣቢያዎች በዚህ ረገድ ቢጠቀሱም ጉልበታምና በሥፋት የሚሰራጩት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሥራ ላይ አቋም የመያዝና የወገንተኝነት ችግር ይታይባቸዋል" ይላሉ
ሲፒጄ"ከእስር የተፈቱ ጋዜጠኞች በባንክ ሂሳባቸው እና እንቅስቃሴ ላይ እገዳ እንደተጣለባቸው ፣ ከእሥር ከተለቀቁ በኋላ በጋዜጠኝነት ሙያ የማይሠሩ መኖራቸውን እና በፍርሃት ውስጥ ሆነው የሚሰሩ መኖራቸውን የገለፁለት እንዳሉም ገልጿል።
በጋዜጠኞች ላይ የደረሱ እርምጃዎች ምንድን ናቸው ?
ሲፒጄ ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች "አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል" በማለት በስም እየጠቀሰ ዘርዝሯል።
አክሎም የተገደሉ ፣ ፍቃዳቸውን የተነጠቁ ጋዜጠኛችንም በዘገባው አስፍሯል።
አሻም ቴሌቪዥን ላይ የሚሠራው ጋዜጠኛ ዮሃንስ አሰፋ " አሁን የታሰሩትን አብዛኞቹን ጋዛጠኞች በምናይበት ሰዓት አብዛኞቹ በሕትመት ላይ የተሰማሩ ወይም በማሕበራዊ መገናኛዎች በተለይም በዩቲዩብ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ናቸው" በማለት መንግሥት ላይ ትችት የሚሰነዝሩት ከሌሎች የሕዝብ መገናኛ ብዘኃን በላቀ ለእሥር እንደሚጋለጡ አስረድቷል።
በአገር ውስጥ የሚገኙ ውስን የሙያ ማሕበራት ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት ተደጋግሞ ለእሥር እና እንግልት መዳረጋቸው እንዳሳሰባቸው በመግለጽ እንዲህ ያለው አዝማሚያ ዘርፉን ከማቀጨጭ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም በማለት እርምት ሲጠይቁ ይስተዋላል። ዶክተር ተሻገር ሽፈራው መገናኛ ብዙኃንና ባለሙያዎቻቸው ትልቁን አገራዊ ድርሻቸውን እየተወጡ ስላለመሆኑ ይጠቅሳሉ።
የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ እንዲሻሻል ምን ይደረግ ?
ሲፒጄ በዘገባው እንዳለው በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ባለስልጣናት ጋዜጠኞችን በሥራቸው ምክንያት ማሰር ማቆም አለባቸው። ይህ የባለሙያዎችን "የፍርሀት ዳመና ለመግፈፍ" ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል" ብሏል። የመንግስት አካላት በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን ኢ- ፍትሐዊነት ማስወገድ አለባቸውም ብሏል።
የአጥፊዎች አለመክሰስ በጋዜጠኞች ላይ ጥቃትን እንደሚያስከትል ገልጾ ባለሥልጣናቱ በጋዜጠኞች ላይ ጥፋት በሚያደርሱት ላይ ተዓማኒነት እና ግልጽነት ያለው ምርመራ በማድረግ አጥፊዎቹ በሕግ እንዲጠየቁ የበለጠ ጥረት ማድረግ አለባቸው ብለሏል።
ጋዜጠኞ ዮሃንስ አሰፋም ይህንኑ ሀሳብ ይደግፋል። የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት መምህሩ ዶክተር ተሻገር ሽፈራው "ያጠፉ ጋዜጠኞች መከሰስ ፣ በሕጋዊ መንገድ ለፍርድ ቤት መቅረብ ይገባቸዋል። ግን ጠፍተው የቆዩና በኋላም ክስ ያልተመሰረተባቸውን ስታይ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ደስ የማይል እንደሆነ ትረዳለህ" በማለት እርምት መደረግ እንዳለበት ጠቅሰዋል።
የመንግሥት ምላሽ ምን ይመስላል ?
መንግሥት ሲፒጄ ባወጣው የጋዜጠኞችን የመብት ጥሰት እና አያያዝ የተመለከተውን ወቀሳ የታከለበት ዝርዝር ዘገባ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጥበት ጥረት አድርጌያለሁ። ለጊዜው ግን አልተሳካም።
ከሳምንታት በፊት የጋዜጠኞች ያልተገባ እሥር መኖሩ ተጠቅሶ ጥያቄ የቀረበላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢለኔ ስዩም "ጋዜጠኛ ማን ነው" ? በማለት በእሥሩ ሂደት ውስጥ ጋዜጠኝነትን በትክክል የሚተገብሩ እና በሙያው ሥም የሚንቀሳቀሱ ያሏቸውን መለየት እንደሚገባ ተናግረው ነበር።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ኋሩት መለሰ