አንድ - ለ - አንድ፤ ከሊቀ ትጉሃን ቄሲስ ታጋይ ታደለ ጋር
ዓርብ፣ መስከረም 2 2018
የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች በተስፋፉበት በዚህ ወቅት የተጠቃሚው ቁጥር በዚያው ልክ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ታዲያ በዚህ የዲጂታል ዘመን ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ የሚጠቀሙ እንዳሉ ሁሉ አሉታዊ ሃሳቦች የሚያንሸራሽሩ ፤ የጥላቻ ንግግሮችን የሚያሰራጩ ብሎም በተለይ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ የመከባበር እና የመቻቻል ማሳያ የነበሩየኃይማኖት ተቋማት በጥርጣሬ እንዲተያዩ የሚያደርጉ ይዘቶችን የሚያሰራጩ ግለሰቦች እየተበራከቱ መጥተዋል።
የኢትዮጵያዉያንን ጥብቅ ማህበራዊ መስተጋብር የሚሸረሽሩ መሰል እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ በርካቶች ድምጻቸውን ሲያሰሙ ይደመጣል።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ፤ ራሳቸው የእምነት ተቋማት ፣ ብሎም ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው የመንግስት ተቋማት ስለጉዳዩ ምን እየሰሩ ነው የሚል ጥያቄ ይነሳል።
በሳምንቱ በአንድ ለአንድ ዝግጅታችን ላይ ተጋባዥ እንግዳ የነበሩት የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ትጉሃን ቄሲስ ታጋይ ታደለ ተቋማቸው እያከናወነ ያለውን ጨምሮ ባለድርሻ ናቸው ያሏቸው መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሚናን አንስተዋል።
ከማሕበራዊ ሚዳያ ተጽዕኖ ሳንወጣ ለልጆች አስተዳደግ ጠንቅ የሆኑ እና ምናልባትም ለቀጣዩ ትውልድ ስነምግባር አሳሳቢ የሆኑ ጉዳዮች ይታያሉ፣ በንግግር ፤ በድርጊት እና የማህበረሰቡን ባህል ፤ ወግ እና እሴት የማይመጥኑ ይዘቶች በማህበራዊ ሚዲያው በስፋት እየተሰራጨ መሆኑ ይታያል።
ይህ ትውልድን በስነ ምግባር አንጾ ከማሳደግ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ረገድ እየተፈጠረ ያለውን ማህበራዊ ቀውስ እንደምን መግታት ይገባል የሚለው ሃሳብ አሳሳቢ እየሆነ ነው። በዚህ ረገድ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት ነው ጠቅላይ ጸሐፊው ያሳሰቡት ።
በሀገሪቱ እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶች መቋጫ አላገኙም ። ወደፊት ተጨማሪ ግጭትቶች ሊቀሰቀሱ እንደሚችሉም ምልክቶች እየታዩ ነው ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ለማስፈን ተስፋ ጠፍቶ ይሆን ለሚለው ስጋት ቄሲስ ታጋይ መፍትሄ ያሉትን ሃሳብ አቅርበዋል። በመነጋገር እና በመያየት ችግሮችን ለመፍታት ዕድል መስጠት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ታምራት ዲንሳ