1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«40 ሺ የሚሆኑ ሰዎችን ውሰዱ ተብለናል»

ዓርብ፣ ሰኔ 25 2013

ኢትዮጵያ ካለፈው ቅዳሜ አንስቶ ሳዑዲ አረቢያ የስደተኞች ማቆያ ጣቢያ የነበሩ ዜጎቿን መመለስ ጀምራለች። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስካለፈዉ ዕሮብ ማታ ድረስ 10 ሺ ገደማ ኢትዮጵያውያን  ወደሀገራቸው ተመልሰዋል።

Äthiopien, Addis Abeba | Ambasador Dina Mufti on press Conference
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲምስል Solomon Muchie

«40 ሺ የሚሆኑ ሰዎችን ውሰዱ ተብለናል»

This browser does not support the audio element.

ሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንደገለፁልን ከሆነ በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ ለኢትዮጵያውያን አሁንም በጣም አሳሳቢ ነው። « መኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሳይቀሩ ተይዘው የስደተኛ ማቆያ ጣቢያ የሚገቡበት እና የሚንገላቱበት ሁኔታ አለ።» ይላል የ32 ዓመቱ ወጣት ዐማን መሐመድ። « ነገሩ ፖለቲካ አዘል ነው ብለን ነበር። የገመትነውም ሳይሆን አልቀረም።» የሚለው ዐማን እስካሁን አራት ኢትዮጵያውያን አመልጣለሁ ሲሉ መኪና ገጭቷቸው እና ከፎቅ ወድቀው እንደሞቱ ይናገራል። ዐማን ህጋዊ ፍቃዱ ተቃጥሏል። እሱም ተይዞ ወደሀገሩ እንደሚላክ አይጠራጠርም። 
ሰዓዳ ልክ እንደ ዐማን መካ ውስጥ ነው የምትኖረው። እሷም ህጋዊ አይደለችም። ግን ወደ ኢትዮጲያ የመመለስ እቅድ የላትም። ሳዑዲ ከሄደች ሰባት አመት ሆናት። መጀመሪያ ላይ የሄደችው በህጋዊ መንገድ ነበር።  « ከአሰሪዎቿ ጥሩ ስላልነበሩ ጠፍቼ ነው።» በቤት ሰራተኝነት አረቦች ቤት ተቀጥራ ለምትሰራው ሰዓዳ ከለላ የሰጧት አሰሪዎቿ ናቸው። እነሱ ጋር መቆየት መቻሏ ግን አስተማማኝ አይደለም። «  አረቦች ቤት መግባት ከጀመሩ እነሱም ስለሚፈሩ ሊያስወጡኝ ይችላሉ። እስካሁን ምንም ነገር የለም። ከቤትም ወጥቼ አላውቅም። 
ኢትዮጵያ በሳዑዲ አረቢያ ግፊት ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸው በርካታ ዜጎቿን ስታስወጣ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜዋ አይደለም። ከዚህ በፊትም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያንን ወደ ሀገሯ መልሳለች። ከእነዚህ  ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ ኢትዮጵያውያን መካከል ግን ሁኔታው ጋብ ሲል ተመልሰው ወደ ሳውዲ የተሰደዱ አልጠፉም። ዐማን ከእነዚህ አንዱ ነው። « መጀመሪያ በህገ ወጥ መንገድ መጣሁኝ፤ በሁለተኛ ጊዜ በቪዛ ነበር። ከሰዎቹ ጋር ባለመስማማቴ ግን ተበላሸ » ይላል። ዐማን በአሁኑ ሰዓት ህጋዊ ፍቃድ ቢኖረውም በተለየ ሁኔታ ይታይ እንዳልነበር ይናገራል። በአሁኑ ሰዓት የሚመኘው የኢትዮጵያ መንግሥት እስር ቤት ሳይገባ ከሳውዲ እንዲወጣ መንገዱን እንዲያመቻችለት ነው። ዐማን ፎቅ ላይ በረዳትነት የጉልበት ሰራተኛ ሆኖ እስካሁን ይሰራ እንደነበር ገልፆልናል። አሁን  ግን ስራውን አቁሟል።

እጎአ በ 2013 ዓም ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያንምስል picture-alliance/AP/E. Asmare

ሳዑዲ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደገለፁልን ከሆነ ሰሞኑን ከሳዑዲ ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሱ ያሉት ላለፉት በርካታ ወራት በእስር ቤት የቆዩት ናቸው። ከሁለት ቀን በፊት ወደ ሀገሩ የተመለሰው መሀመድ አንድ ዓመት ከሁለት ወር ያህል በስደተኞች ማቆያ ጣቢያ እንደተንገላታ ይናገራል። ከሳዑዲ አረቢያ እየተያዘ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ይህ ሶስተኛ ጊዜው ነው። በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ግን የነበረው እንግልት በአሁኑ ከባዱ ነበር « ድሮ ችግር የለውም በስምንት እና በ 10 ቀን ነበር ወደ ሀገር የምንገባው። አሁን ግን ከአንድ ዓመት በላይ ወስዶብናል።»ይላል።
መሀመድን በስልክ ስናነጋግረው አብረውት ከሳውዲ የተመለሱ ሌሎች ሰባት ኢትዮጵያን እንዳሉ እና ወደ ክፍለ ሀገር እየተጓዙ እንደሆነ ነግሮናል። ከእነዚህ አንዷ ሀያት ትባላለች።  ባለፈው እሁድ ነው ኢትዮጵያ የገባችው። እንዴት በሳዑዲ ወታደሮች ቁጥጥር ስር እንደዋለች ስትናገር« የምንሰራበት የሆነ እረፍት ቦታ ነበር። እዛ ሰብረው ገብተው ነው የያዙን» ሀያት ለ 16 ቀን ታስራ ነበር። ልጅ ስላላት ቅድሚያ አግኝታ ወደ ሀገራ ተመልሳለች። ከሳዑዲ ስትመለስ የመጀመሪያዋ ጊዜዋ ነው። እንደነገረችን ከሁለት ዓመት በፊት ነው ወደ ሳዑዲ አረቢያ በህገ ወጥ መንገድ የሄደችው። ተመልሳ መሰደድ አትፈልግም። ለሌሎች ወጣቶችም የምትመክረው ይህንን ነው ። « አሁን ላይ ጫና አለ። የሳውዲ መንግሥት አሁን ላይ ኢትዮጵያኖችን አይፈልጉም።ጥንቃቄ ቢያደርጉ እና አሁን ላይ ባይሄዱ ጥሩ ነው። ለሶስተና ጊዜ ወደ ሀገሩ የተመለሰው መሀመድም ስደት በቃኝ ይላል። 

እንደ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴት መግለጫ በቀን ሰባት ወይም ስምንት አይሮፕላኖች ከሳዑዲ ዜጎችን ይዘው ሰሞኑን ኢትዮጵያ እየገቡ ይገኛሉ። «ከአምስት ዓመት በፊትም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ አረቢያ መልሰናል» ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በአሁኑ ወቅት የሳዑዲ ግፊት በተለየ ሁኔታ መጠንከሩንም ሀሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያውያኖች ላይ ከዚህ በፊትም በተለያዩ ምክንያቶች ክስ ይቀርብባቸው እንደነበር እና «የአሁኑ ግን ለየት ያለ መልክ የያዘው ህጋዊ ሰውነት ያላቸውንም ጭምር የመግፋቱ ነገር ከኋላ የሆነ ነገር ይኖራል ብሎ መጠርጠር አግባብነት ያለው ነው» ብለዋል።«40 ሺ የሚሆኑ ሰዎችን ውሰዱ ተብለናል» ያሉት አምባሳደር ዲና  ስደት ዓለም አቀፍ ችግር እንደሆነ እና ምንጩን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW