የሳይበር ጥቃት እና የዘንድሮው የአሜሪካ ምርጫ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 27 2017
በጎርጎሪያኑ 2016 ዓ/ም እንደታየው በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሳይበር ጥቃት ትልቅ ስጋት ሆኗል። ትናንት በጎርጎሪያኑ ህዳር 5 ቀን 2024 ዓ/ም የተጠናቀቀው እና ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ያሸነፉበትን የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመረበሽ ሩሲያ ፣ቻይና እና ኢራን የሳይበር ጥቃት መሰንዘራቸውን የአሜሪካ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ደህንነት ተቋማት ገልፀዋል።
ኒውዮርክ ታይምስ እና ዎል ስትሪት ጆርናል ያለፈው ሳምንት እንደዘገቡት የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ እጩ የነበሩትን ዶናልድ ትራምፕን፣ ተመራጩን ጄዲ ቫንስን እና የምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስን የምርጫ ዘመቻ አባላትን የተንቀሳቃሽ ስልክ ሰብሮ ለመግባት ተደጋጋሚ ሙከራ ተደርጓል ።
ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎችን በመጥቀስ ኒውዮርክ ታይምስ የትራምፕ እና የቫንስ ተንቀሳቃሽ ስልኮች በጠለፋ ቡድኑ የተመረጡ መሆናቸውን እና የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች የተፈጠረውን ነገር ለማወቅ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክቷል።
ይህ ዘገባ በቀረበ በጥቂት ሰአታት ውስጥ ዎል ስትሪት ጆርናል ጠላፊዎቹ ከዲሞክራቲክ እጩ ካማላ ሃሪስ ዘመቻ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች ስልኮቻቸው ኢላማ መደረጉን ዘግቧል።
ይህንን ችግር ለመቀልበስም የአሜሪካ መንግስት የሳይበር ደህንነት ተቋማት ስራ በዝቶባቸው ነው የሰነበተው።
ጋዜጠኛ እና የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ የሆነው አበበ ፈለቀ እንደሚለው የሳይበር ጥቃት በአሜሪካ ሰሞኑን ምርጫን አስታኮ ይከሰት እንጅ የሳይበር ወንጀለኞች ሁልጊዜም በተለያዩ መንገዶች በሀገሪቱ ጥቃት ያደርሳሉ ።
በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት
የአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት ሰኞ ዕለት በምርጫው ዋዜማ ባወጡት መግለጫም በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
የአሜሪካ የብሄራዊ መረጃ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር (ODNI)፣የአሚሪካ የፌዴራል የምርመራ ቢሮ (FBI) እና የሳይበር ደህንነት እና የመሠረተ ልማት ደህንነት ኤጀንሲዎች/CISA/ እንደገለፁት የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እምነት እንዲያጣ የውጭ ኃይሎች ሙከራ እያደረጉ ነው ሲሉ ኮንነዋል።
ባለስልጣናቱ በተለይ ሩስያ የአሜሪካንን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ታአማኒነት ለማሳጣት እና መራጮችን ለመከፋፈል እየሰራች ነዉ ሲሉ ጣታቸዉን ወደ ሞስኮ ቀስረዋል።
የሳይበር ጥቃት ስጋቶች በምርጫ ዋዜማ
ቀደም ሲል በምርጫው ቀን የምርጫ ዘመቻ ማካሄጃ ቢሮዎችን፣ የድምፅ መስጫ እና የቆጠራ ጣቢያዎችን ኢላማ ያደረገ የሳይበር ጥቃት ስጋቶች መኖራቸውን ሲገልፁ የቆዩት የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት፤በትናንትናው ዕለትም በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአሜሪካውያን ፕሬዚዳንታቸውን ለመምረጥ ወደ ምርጫ ጣቢያ ከማቅናታቸው ከጥቂት ሰአታት በፊት ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
መግለጫው ፤መራጮች በአሜሪካ የምርጫ ሂደት ላይ ያላቸውን እምነት ለማዳዳከም እና አሜሪካውያን እርስበርስ ለሚከፋፈል ከሚሰራጭ የመረጃ ማዕበል ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስጠንቅቋል።
በተለይም የፕሬዚዳንታዊ ፉክክሩን ውጤት ሊወስኑ በሚችሉ ግዛቶች ቁጣን ለመቀስቀስ እና ውጥረቶችን ለማቀጣጠል የታቀዱ የውሸት ቪዲዮዎች እና መጣጥፎች በፍጥነት መሰራጨታቸው ተገልጿል።
ማስጠንቀቂያው ከትናንቱ ምርጫ በፊት ባሉት ሳምንታት እና ወራት ውስጥ የአሜሪካ የስለላ ባለስልጣናት ያወጧቸውን ተከታታይ ግምገማዎችን ተከትሎ ነው።
ሶስተኛው ዓለም ጦርነት በሳይበር ጥቃት ይሆን?
ከመረጃ መመንተፍ እና ከስልክ መጥለፍ ባሻገር የሳይበር ወንጄለኞች የተለያዩ ተቋማትን መረጃዎች እንደመያዣ በመጠቀም ገንዘብ መጠየቅም ሌላው የሳይበሩ ዓለም ችግር መሆኑን የሚገልፀው አበበ፤«ምናልባትም ሶስተኛው ዓለም ጦርነት የሚጀመር ከሆነ ያ ጦርነት የሚካሄደው በመደበኛ ጦርሜዳ ሳይሆን በአብዛኛው በሳይበር ጥቃት ሊሆን ይችላል።የሚል ግምት ነው ያለው።»ይላል።ምክንያቱም ይላል አበበ። የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ ነው።ጥቃቱ የአንድን ሀገር የውሃ፣ የኤለክትሪክ አገልግሎት እስከ ኒዩክሌር ኮዶች ማስተጓጎል ሊደርስ ይችላል።
በዚህ ሁኔታ እነዚህ ሀገሮች የሚያደርሱት ጥቃት በተለይ ከጎርጎሪያኑ 2016 ዓ/ም ምርጫ ማለትም ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ተባብሶ መቀጠሉንም አመልክቷል።ይህ ሙከራቸውም በአሜሪካ ዲሞክራሲ ላይ ጥርጣሬ በመፍጠር ፣ህብረተሰቡን ግራ በማጋባት፣ ሀገራቱ ለእነርሱ የውጭ ፖሊሲ ተስማሚ የሆነ ፕሬዚዳንት እንዲመረጥ በማድረግ፣ በሀሰተኛ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ምርጫ እንዲካሄድ በማድረግ እና የማይፈልጓቸውን የምርጫ ዘመቻዎች በማወክ ተሳክቶላቸዋል ሲል ጋዜጠኛ እና የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያው አበበ ፈለቀ ገልጿል።
ጥቃቱ ዲሞክራሲን ዋጋ እንዲያጣ ያደርጋል
ለመሆኑ ይህ ሁኔታ በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ይኖር ይሆን?
«በአሜሪካ ባለፉት አስር አመታት ምርጫ በመጣ ቁጥር የሳይበር ጥቃት እጅግ የተለመደ ሆኗል።» ካለ በኋላ «በ2016 የሄላሪ ክሊንተንን ኢሜል የጠለፉ ጊዜ የተጠለፉ በርካታ ኢሜሎች ዊክሊክስ ላይ ጭነው ያሳዩበት ሁኔታ ነበር።» ሲል አስታውሷል።አሁንም በአሜሪካ በኩል እነኝሁ ሶስት አገሮች ናቸው ስራ ይሰራሉ ተብሎ የሚጠበቀው ቻይና ሩሲያ እና ኢራን።»ብሏል።«ስለዚህ በአንድ ሆነ በሌላ መንገድ በምርጫው ጫና ለማሳደር፤የአሜሪካ ምርጫ ውጤትንም ለመቀየር አንዳንድ ጊዜ ምክንያቱም እነዚህ ሀገራት አሜሪካ ከሁለት በአንዳቸው ብትመራ በአለማቀፍ ግንኙነታቸውም ይሁን በሌላ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የተሻለ አማራጭ እንዳላቸው ሲያስቡ አንደኛውን እጩ የመደገፍ ነገርም አለ።»በማለት አብራርቷል።
በዚህም እነዚህ ሀገራትየዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫ የሆነውን ምርጫን በማጣጣል ዲሞክራሲን ዋጋ እንዲያጣ ያደርጋሉ።
የሳይበር ደህንነት ስጋት በመሠረተ ልማቶች ላይ
የአሜሪካ ባለስልጣናት በምርጫው ውጤት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር በውጭ ሀገራት ከሚሰራጩት የሀሰት መረጃ ስርጭት ጎን ለጎን ወሳኝ በሆኑ መሠረተ ልማቶች ላይ የሳይበር ደህንነት ስጋት እንደሚፈጠር በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።
የመረጃ መንታፊዎቹ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የመንግስት ኤጀንሲዎችን እና ሌሎች ትልልቅ ድርጅቶችንም ኢላማ አድርገው ነበር ሲል ወልስትሪት በዘገባው አመልክቷል።
ባለፈው ወርም የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ ሶስት የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ አባላት በትራምፕ እና በሃሪስ ዘመቻዎች ላይ በነሀሴ ወር ላይ በፈጸሙት የጠለፋ ጥቃት ክስ መሰርቶባቸዋል።
እንደ ወል ስትሪት ዘገባ ባለፈው ወርም፣ ኤፍቢአይ ካሜራዎች፣ የቪዲዮ መቅረጫዎች እና የዋይፋይ ራውተሮችን ጨምሮ ከ200,000 በሚበልጡ የሸማቾች መሳሪያዎች ላይ በቻይና የተጫኑ ተንኮል አዘል ሶፍትዌሮችን አቋርጧል።
በዚህ ሁኔታ፤ ቻይና ሩሲያ እና ኢራን አደረጉት የተባለው የሳይበር ጥቃት በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተፅዕኖው በውል ባይገለጽም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለሁለተኛ ጊዜ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ