1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሳዴክ ጉባኤ

ዓርብ፣ ጥር 3 2005

ስለ ጦር ስምሪቱ በግልጽ የሚታዬ ተግዳራቶች ቢኖሩም የደቡባዊ አፍሪቃ መንግስታት የልማት ማህበርሰብ ዋና ፀሐፊ ቶማስ ሳላማዖ እንደሚሉት ግን ሳዴክ ወታደሮቹን ያለ ምንም ዓለም አቀፍ እርዳታ ለማዝመት አቅዷል።«የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እርዳታ መጠበቅ የለብንም። በራሳችን አቅም መጀመር እንችላለን። የያዝነውን እንቀጥልበታለን።»

Tanzania's President Jakaya Kikwete speaks during a press availability with Secretary of State Hillary Rodham Clinton at the State House in Dar es Salaam, Tanzania, Monday, June 13, 2011. (Foto:Susan Walsh, POOL/AP/dapd)
የጉባኤዉ አስተናጋጅ ኪክዌቴምስል dapd

የደቡባዊ አፍሪቃ መንግስታት የልማት ማህበርሰብ በምህጻሩ ሳዴክ አባል ሀገራት ትናንት በታንዛኒያ ማካሄድ በጀመሩት ስብሰባ በምስራቅ ዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ በማዳካስካር እየታዬ ስላለው የፖሊቲካ ቀውስና ስለዚምባቢዌ ሁኔታ መክረዋል። በዚህም መሠረት በዲሞክራሲያዊ ኮንጎ የሳዴክን የተጠንቀቅ ጦር የማዝመት ሂደት መጀመሩ ተገልጿል። ነገር ግን ካለኮንጎ መንግስትና ከM23 አማጺያን ተሳታፊነት ውጭ የተደረገው የሳዴክ ምክክር ያማሬ ውጤት ማምጣቱ አጠራጥሯል። ገመቹ በቀለ ዝርዝር ዘገባ አለው።

በዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ ስለሚታየው ግጭት እንዲሁም በማዳካስካሪና ዚምባቡዌ እየታየ ስላለው የፖሊቲካ ቀውስ የደቡባዊ አፍሪቃ መንግስታት የልማት ማህበርሰብ ሳዴክ ትናንት በጀመረው ጉባዔ ላይ የአስተናጋጇ ሀገር የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጃካያ ኪክዌ፣ የደቡብ አፍሪቃ አቻቸውናን የናሚቢያ አቻዎቻቸው ጄኮብ ዙማና ሂፊኬፑኜ ፓሃምባ እንዲሁም የሞዛምቢክ ፕሬዚደንት አርማንዶ ኤሚልዮ ገቡዛም ተገኝተዋል።

ሳዴክ ከወር በፊት በታንዛኒያ ባደረገው ስብሰባ በምስራቅ ዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ የተሰማራውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይልን ለማጠናከር የራሱን የጦር ኃይል ለመላክ መወሰኑ ይታወሳል። ትናንት በተጀመረው ስብሰባም አንዱ ዓላማ ከዚህ ውሳኔ ወዲህ ምን እንደተሰራ ለመገምገም እንደሆነ ተነግሯል። ባለፈው ታህሳስ በተደረገው የሳዴክ ስብሰባ አባል ሀገራቱ 4000 ወታደሮችን ወደ ምስራቅ ዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ ለመላክ ቃል ቢገቡም፣ የጦር ኃይሉን ወደ ሥፍራው የማዝመቱ ሥራ አስቸጋሪ እንደሚሆን ያካባቢው የፖሊቲካ ተንታኙ ጀነራሊ ኡሊምዌንጉ ይናገራሉ

«ጦር ማዝመትን በተመለከት በርግጠኝነት ፈተናዎ ች ይኖራሉ። ስለጉዳዩ በቂ መረጃ እውቀት ያላቸው አይመስለኝም። እንዴት አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚቻል የተቀመጠ ግልጽ ነገር የለም። በዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ ብዙ የማይታወቁ ጉዳዮች አሉ። ይህ ደግሞ ጦር ስምሪቱ ግልጽ የሆነ ያልሆነ አካሄድ እንዲኖረው ያደርጋል። ብዙ ችግሮችና መሰናክሎች አሉት።»

ስለ ጦር ስምሪቱ በግልጽ የሚታዬ ተግዳራቶች ቢኖሩም የደቡባዊ አፍሪቃ መንግስታት የልማት ማህበርሰብ ዋና ፀሐፊ ቶማስ ሳላማዖ እንደሚሉት ግን ሳዴክ ወታደሮቹን ያለ ምንም ዓለም አቀፍ እርዳታ ለማዝመት አቅዷል።

«የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እርዳታ መጠበቅ የለብንም። በራሳችን አቅም መጀመር እንችላለን። የያዝነውን እንቀጥልበታለን።»

የታላላቆቹ ኃይቆች አከባቢ ዓለም አቀፍ ጉባዔ በምስራቅ ዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ ለዘብተኛ የጦር ኃይል እንዲቋቋም ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ ሙከራ ሲያደርግ ቆይቷል። ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎም የዚው ጉባኤ አባል ናት። አንዳንድ የአከባቢው ሀገራት የሳዴክ አባል ሀገራት ቢሆኑም በሳዴክና በታላላቆቹ ኃይቆች አከባቢ ዓለም አቀፍ ጉባዔ መካከል ዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክን በተመለከተ ግልጽና ተደጋጋፊ መዋቀራዊ አሰራር የለም።

ይህ የታንዛኒያ ስብሰባ እየተካሄደ ባለበት ባሁኑ ጊዜ በዩጋንዳ መዲና ካምፓላም የኮንጎ ፕሬዚደንት ካቢላን መንግስትና የM23 አማጺያንን ለማስታረቅ የሰላም ድርድር እየተካሄደ ነው። እንዲህ የሆነ የተናጠል አሰራር ችግር አለው የፖሊቲካ ተንታኙ ጀነራሊ ኡሊምዌንጉን ይላሉ፤

«ቅንጅት የለም። በሁለቱም ሂደቶች መካከል የመረጃ ፍሰት የለም። ማለትም፣ በምስራቅ ኮንጎ የቀጠለውን ውዝግብ በተመለከተ በካቢላ መንግስትና በM23 አማጺያን መካከል በሚካሄደው ድርድር ላይ ነው ጥረቱ ማትኮር ያለበት። የዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ ችግር የሚያሳስበን ከሆነ ከነዚህ ሁለቱ ጋር ነው ሌሎች አንድ ላይ መስራት ያለባቸው። ሁለቱ ቡድኖች አሁን ካምፓላ ውስጥ እያደረጉ ያሉትን ድርድር ያላገናዘበ ማንኛውም መፍትሔ አፈላላጊ የሚመስል ሂደት ሊኖር አይገባም።»

በሳዴክና በታላላቆቹ ኃይቆች አከባቢ ሀገራት መካከል ያለው የመረጃ ፍሰት ቢጠብም ሳዴክ ባለፈው ታህሳስ በወሰነው ውሳኔ መሰረት የተጠንቀቅ ጦርን ለመላክ እየተዘጋጀ ነው። በዚህ ጉዳይም ላይ በሁለቱ ቡድናት መካከል ንግግር ይካሄዳል ይላሉ የሳዳክ ዋና ፀኃፊ ቶማስ ሳላማዖ፣

«ይህ በሂደት የሚሰራ ጉዳይ ነው። በታላላቁ ኃይቆች አከባቢ ከሚኖሩ ወዳጆቻችን ጋር አንድ ላይ መነጋገር አለብን። አፍሪቃ ህብረትንም ማጠቃለል አለብን። ወደ ፊት እንራመዳለን።»

በዚህ በታንዛኒያ እየተካሄድ ባለው የደቡባዊ አፍሪቃ ሀገራት ጉባኤ ላይ ሶስት ዓመት የሆነውን የማዳካስካር የፖለቲካ ውዝግብ ስለሚያበቃበት እና ስለዚምባቡዌየፖሊቲካ ጉዳይም ተነስቷል። በሁለቱ ሀገራት ሊካሄዱ የታቀዱ ብሔራዊ ምርጫዎች ዋናው የውይይቱ ጉዳይ መሆኑ ታውቋል።

የማዳጋስካሩ መሪ-ራጆሊናምስል picture-alliance/dpa
የኮንጎ አማፂያን M23ምስል Phil Moore/AFP/Getty Images

ገመቹ በቀለ

አርያም

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW