የሴትነትን ክብር የሚጻረረው ፊስቱላ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 17 2013
በወሊድ ወቅት የምጥ መራዘምን ተከትሎ ከሚመጡ የጤና ችግሮች አንዱ በሆነው ፊስቱላ ጤናቸውና ኑሯቸው ለተናጋ ወገኖቻችን ኢትዮጵያ ውስጥ መፍትሄውን ለማምጣት ለበርካታ ዓመታት የደከሙት ዶክተር ካትሪን ሃምሊን ካረፉ ዓመት ሆነ። እኚህ ብዙዎች እናትና የህክምና ባለሙያ ወደ ኢትዮጵያ ከባለቤታቸው ጋር በመምጣት የአዋላጅ ሃኪሞች ማሠልጠኛ ለማቋቋም በሚሠሩበት አጋጣሚ ይኽን ችግር በማስተዋላቸው ዛሬ የብዙዎች ሕይወት የተቀየረበትን የፊስቱላ ማዕከል በመመሥረታቸው ስማቸው በበጎ ከሚነሳ ወገኖች አንዷ ለመሆን በቅተዋል። የሃምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል በኢትዮጵያ ከተመሠረት ከ60 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥም ከ60 ሺህ በላይ ሴቶች ጤናቸው ተመልሶ ወደ ማኅበረሰባቸው በመመለስ የቀደመ ክብራቸውና ኑሯቸውን አግኝተው ሕይወታቸውን በደስታ እየገፉ መሆኑን የሀምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ማሞ ነግረውናል። ዶክተር ካትሪን ሃምሊን በትውልድ ሀገራቸው አውስትራሊያ ይኽ የጤና ችግር ከሴቶች ላይ ከተወገደ ረዥም ዓመት በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ለፊስቱላ ችግር ብዙ ሴቶች ተጋልጠው በማየታቸው አዲስ የህክምና ዘዴ መጀመራቸውን አቶ ተስፋዬ ያስታውሳሉ። በዚያን ጊዜም ዶክተር ሃምሊን ከሚያውቋቸውና ከቤተሰቦቻቸው የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ የአዲስ አበባን የፊስቱላ ሆስፒታል በማቋቋሙ ሥራው መስፋፋቱንም ገልጸዋል። በሂደቱም ብዙዎችን ወደሙያው በማምጣት ስልጠና እንዲያገኙም አመቻችተዋል ነው ያሉት። ከወሊድ ጋር በተገናኘ የሚከሰተው ፊስቱላ የጤና ችግር በተለይ ለህክምና ሩቅ በሆኑት የሀገሪቱ ክፍሎች በብዛት የሚያጋጥም በመሆኑም አዲስ አበባ ላይ የተጀመረው የህክምና ርዳታ መስጫ ማዕከል ወደሌሎች አካባቢዎች መስፋፋት ችሏል።
በምጥ መራዘም ለፊስቱላ የተጋለጠች እናት በተለያየ መልኩ እንደምትጎዳ እና በሚያስከትልባት መገለል የስነልቡና ጉዳትም እንደሚያጋጥማት ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት። እንዲህ ባለ ስቃይ ውስጥ የቆዩት የፊስቱላ ታማሚዎች ሕይወታቸውን ወደሚያስተካክሉበት የሀምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ሲመጡ በነጻ የሚያገኙዋቸው ርዳታዎች በርካታ ናቸው።
እንዲህ አካላዊና ስነልቡናዊ ጉዳት ከደረሰባቸው የፊስቱላ ታማሚዎች አንዳንዶቹ ጤናቸው ተመልሶ ዳግም ፀንሰው ልጅ የሚወልዱበት አጋጣሚ እንዳለ ያነጋገርኳቸው ሁለቱም በዚህ የጤና ችግር ላይ የሚሰሩት ባለሙያዎች ጠቅሰዋል። ለዚህም የሃምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል የተለየ ክፍል እንዳለውም አስረድተዋል።
በሃምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል እስካሁን እጅግ በርካቶች ታክመው ወደቀደመ ክብርና ሕይወታቸው የተመለሱ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም በመላ ሀገሪቱ ባሉት ማዕከላት በየዓመቱ ከሁለት ሺህ እስከ ሦስት ሺህ ታካሚዎችን በቀዶ ህክምና እንደሚረዱ ገልጸውልናል። በከተሞችን ጭምር ችግሩ ስለሚያጋጥምም በተመላላሽ ደረጃ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትን እንደሚረዱም ለመረዳት ችለናል። በኢትዮጵያ የሀምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ምንም እንኳን ዋና ትኩረቱ ሀገሬው ላይ ቢሆንም ከጎረቤት ኤርትራ እንዲሁም ከሱዳን ለመጡ የዚህ የጤና ችግር ሰለባዎች ተመሳሳይ የህክምና ርዳታ እንደሚሰጥም ለመረዳት ችለናል።
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ