ወደ አውሮጳም የተዛመተው የሴት ልጅ ግርዛት
ማክሰኞ፣ ጥር 28 2016
በዛሬው ዕለት በሴት ልጆች ላይ የሚፈጸመውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት በመላው ዓለም ይታሰባል። ለዓመታት በተደረገው የማስተማርና የማንቃት እንቅስቃሴ በአንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት ለውጥ እየታየ መሆኑ ቢነገርም ድርጊቱ ወትሮ ባልነበረባቸው የአውሮጳ ሃገራት እየተፈጸመ መሆኑ ትኩረትን ስቧል።
በየዓመቱ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ትኩረት አግኝቶ እንቅስቃሴው በመላው ዓለም መታሰብ ከጀመረ ዘንድሮ 13ኛ ዓመቱን ያዘ። ከዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የተረፉ ሴቶች ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት እንዲያገኝ ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውተዋል ዛሬም ይህንኑ ቀጥለዋል። ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሕይወታቸው ላይ ጫና ያስከተለባቸው በርካቶች ያለውን አካላዊና ስነልቡናዊ ጉዳት በይፋ እያስተማሩና በየመድረኩ እየተናገሩ የብዙ አዳጊ ሴቶችን የስነተዋልዶ ጤና ለማስጠበቅ የበኩላቸውን ማድረጋቸውን እንደ የተመ የሕጻናት መርጃ ድርጅት UNICEFን የመሳሰሉ ተቋማት በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። በእነሱ ጥረት የተገኘው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ድርጊቱ ጭራሽ እንዲቆምም በሚፈለገው ሁሉ ድጋፎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ያሳስባሉ።
እንደ UNICEF መረጃ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2024 4,4 ሚሊየን አዳጊ ሴት ልጆች ለግርዛት ተጋልጠዋል። በየዕለቱም ከ12 ሺህ በላይ አዳጊ ሴት ልጆች በመላው ዓለም የዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉም አመላክቷል። ምንም እንኳን እስከ ዛሬ በየሀገሩ የተከናወኑ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን መዘዞች በማስተማርና መተዳደሪያቸው ያደረጉትን ወገኖችም እያረሙ በሌላ ሥራ ገቢ እንዲያገኙ በማድረጉ በኩል የተከናወኑት ተግባራት ትርጉም ያለው ውጤት ማስገኘታቸው ቢታወቅም፤ አሁንም ግን በብዙ ሃገራት ድርጊቱ እየተፈጸመ መሆኑ አሳሳቢነቱ ለመቀጠሉ ማመላከቻ እንደሆነም UNICEF አሳስቧል።
በሴት ልጆች ላይ የሚፈጸመው ግርዛት ከአሰቃቂነቱ በተጨማሪ ሕይወት እስከማጣት የሚያደርስ እንደሆነ ለማሳያነት የከፋው ግርዘት የሚፈጸምባቸውን አካባቢዎች እየጠቀሱ ጥናት ያካሄዱ ወገኖች መረጃዎች ይፋ ያደርጋሉ። ከዚህ በመነሳትም የተመድ ድርጊቱን ከባድ የአዳጊና አዋቂ ሴቶችን ሰብአዊ መብት መጣስ ነው ብሎ በጎርጎሪዮሳዊው 2012 ዓም ደንግጓል።
የሴት ልጅ ግርዛትና የአፍሪቃ ሃገራት
በተለይም አፍሪቃ ውስጥ በሚሊየን የሚቆጠሩ አዳጊ ሴት ልጆች ለግርዛት መጋለጣቸውንም የተመድ አመልክቷል። በበርካታ አፍሪቃ ሃገራት ይህን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቆም በቂ ሕግ የለም ነው የሚባለው። እንዲያም ሆኖ ዩጋንዳ እና ኬንያ የሴት ልጅን ግርዛት ለማስቆም የደነገጉት ሕግ ትርጉም ያለው ውጤት እያመጣ መሆኑ ተነግሯል። ባለፉት ዓመታት ሁለቱ የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን ለማስቆም የወሰዱት እርምጃ ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ነው የተገለጸው።
አፍሪቃ ውስጥ በጥቅሉ 20 ሃገራት የሴት ልጅ ግርዛትን በይፋ አግደዋል። ሆኖም ያሏቸው በቂ እንዳልሆኑ፤ ተግባራዊነታቸውም የላላ መሆኑ የሚፈለገው ለውጥ እንዳይመጣ እንቅፋት ሆኗል በሚል ይተቻል። እንዲህ ካሉት እና በከፍተኛ ስጋት ከሚታዩት ሃገራት መካከልም ቻድ፣ ላይቤሪያ፤ ማሊ፤ ሴራሊዮን፣ ሶማሊያ እና ሱዳን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ወደ 16 ሚሊየን ለሚሆኑ አዳጊ ሴት ልጆች መኖሪያ ናቸው የሚባሉት ሃገራት እስካሁን የሴት ልጅ ግርዛትን ወንጀል አድርጎ የሚያግድ ሕግ የላቸውም። ድርጊቱንም በይፋ እየተፈጸመ ነው። ብዙዎች ግን ሕጉ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ በመጠቆም፤ ባህላዊ ድርጊቶችንና ደንቦችን ለመለወጥ ብዙ መሥራት እንደሚገባም ያሳስባሉ።
የኢትዮጵያ ሁኔታ
ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎችጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን ለማስቆም የተደረጉ ጥረቶች ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደቻሉ ነው የሚነገረው። ምንም እንኳን ዛሬም የሴት ልጅ ግርዛት በከተሞች ሳይቀር እንደሚፈጸም ቢነገርም ከዋና ከተማዋ ራቅ ባሉ አካባቢዎች መጠነኛ ለውጥ መኖሩን ለመረዳት ችለናል።
የሀላባ ዞን ዌራ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ወይዘሮ ከዲጃ ሁሴን በሚኖሩበት አካባቢ በከተሞች የሴት ልጅ ግርዛት እንደበፊቱ ባይሆንም ዛሬም እየተፈጸመ መሆኑን ነው የገለጹልን። በገጠሩ ዛሬም ድርጊቱ ቀጥሏል ያሉት ወይዘሮ ብርቅነሽ በከተሞችም ቢሆን በፊት ይደረግ የነበረው የአገራረዝ ስልት ለውጥ እየታየበት ነው ይላሉ።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ቢበረክቱም ድርጊቱ በባህላቸው የሌለ የኅብረተሰብ ክፍሎችም አሉ። የአማሮ ልዩ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ብርቅነሽ ዑዊዝራ እንዲህ ያለው ልማድ በሌለበት አካባቢ የሚኖሩ ናቸው።
የሴቶች ግርዛት በአውሮጳም መስፋፋቱ
እስከዛሬ ዓለም የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም የሚሟገተው በአብዛኛው አፍሪቃ ውስጥ ነበር። አሁን ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አውሮጳም ውስጥ መስፋፋቱ እያነጋገረ ነው። በቅርቡ ቴር ደ ፋም የተባለው የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅት ይፋ ባደረገው መረጃ በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ውስጥ ብቻ የተገረዙ ከ100 ሺህ በላይ ልጃገረዶች ይገኛሉ። ሌሎች ከ17 ሺህ በላይ እንደሆኑ የሚገመቱ ልጃገረዶች ደግሞ ለግርዛት የተጋለጡ ናቸው። በመላ ጀርመን የግርዛት ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦች ድጋፍ የሚያደርጉ በርካታ የምክር አገልግሎት መስጫዎች ቢኖሩም ለህክምና ባለሞያዎች ለአዋላጆች፣ ለሕጻናት ሐኪሞችና ለማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞች ግንዛቤ ማስጨበጥ ጠቃሚ ነውም ተብሏል። በተመሳሳይ ስዊድን፤ ኖርዌይ፣ ኔዘርላንድ እና ሌሎችም ሃገራት በተለይ ከአፍሪቃ የመጡ ቤተሰቦችና ልጆችን በዓይነ ቁራኛ እየተከታተሉ ነው። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ በፍልሰተኞች ምክንያት ከዚህ በፊት ወደማይታወቅባቸው ሌሎች የመዛመቱ ጉዳይ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
በየዓመቱ በዚህ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታሰበው የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም የሚደረገው ጥረት የዘንድሮው መሪ ቃል «ተግባራዊ እርምጃ» የሚል ነው። አሁንም በየሀገሩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን የሚያስቆም ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ሁሉም ድምፁን ሊያሰማ ይገባል እንላለን።
ሸዋዬ ለገሠ