የስምጥ ሸለቆ ሀይቆችን ህልውና ለመታደግ የመከረው መድረክ
ሐሙስ፣ መስከረም 22 2018
የስምጥ ሸለቆ ሀይቆችን ህልውና ለመታደግ የመከረው መድረክ
በኢትዮጵያ በታላቁ የስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ ሀይቆች ሥነ ህይወታዊ ህልውናቸው በአሳሳቢ ደረጃ ላይ መውደቁን የዘርፉ ተመራማሪዎች ገለጹ ፡፡ በሀዋሳ እየተካሄደ በሚገኘው 22ኛው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባዔ ላይ የተጋበዙ ተመራማሪዎች እንዳሉት ሀይቆቹ በሰው ልጅ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት የተነሳ የውሃ መጠናቸው እየቀነሰ ፣ ነጥረ ነገራዊ ይዘታቸውም እየተዛባ ይገኛል ፡፡ በኮንፈርንሱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ኮንፍረንሱ የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታትና በጥናት ላይ የተመሠረቱ ምክንያታዊ ውይይቶችን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል ፡፡
የስምጥ ሸለቆ ሀይቆችን ህልውና እንዴት እንታደግ ?
ከሶሪያ ተነስቶ እስከ ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ሞዛቢክ የሚደርሰው ታላቁ የስምጥ ሸለቆ ኢትዮጵያን ለሁለት ከፍሎ ነው የሚያልፈው ፡፡ ሳይንስ ከ18 ሚሊዩን ዓመታት በፊት በመሬት እንቅሰቃሴ ተፈጥሯል የሚለው ይሄው ሸለቆ ኢትዮጵያን የበርካታ ሀይቆች ባለቤት ማድረጉ ግን እውነት ነው ፡፡ የመተሃራ ፣ የዝዋይ ፣ የላንጋኖ ፣ የሀዋሳ እንዲሁም የአባያ እና የጫሞ ሀይቆች ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው ፡፡ ዓሳን ጨምሮ ለተለያዩ የብዝሃ ህይወት መኖሪያነት ፣ ለመጓጓዣና ለጎብኚዎች መዝናኛነትን እየዋሉ የሚገኙት የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች አሁን ላይ ሥነ ህይወታዊ ህልውናቸው በአሳሳቢ ደረጃ ላይ መውደቁ እየተነገረ ይገኛል ፡፡
የሐይቆቹ ሥነ ሕይወታዊ ጤንነት
በሀዋሳ እየተካሄደ በሚገኘው 22ኛው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባዔ ላይ የንጹህ ውሃ ሥነ ምህዳር ተመራማሪው ፕሮፌሰር ዝናቡ ገ/ማሪያም የምርምር ሥራቸውን አቅርበዋል ፡፡ በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ላይ አለ ያሉትን ሥነ ህይወታዊ ሥጋት በማብራራት ገለጻቸውን ያደረጉት ፕሮፌሰሩ ሀይቆቹ ከባድ በሆነ የሥነ ሕይወታዊ ጤንነት ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል ፡፡
በሀይቆቹ ዙሪያ ገብ መሬት የሚደረጉ የመስኖ እርሻ ሥራዎች ፣ የመኖሪያ መንደሮች መስፋፋት ፣ ልቅ የሆነ የዓሳ ማስገር ለሐይቆች ህልውና ቀጣይነት ፈተና መሆናቸውን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ዝናቡ “ በተለይም ሀይቆቹን የሚመግቡ ወንዞች ለመስኖ ሥራ በመዋላቸው የሀይቆቹ የውሃ መጠን እንዲቀንስ እያደረጉ ነው ፡፡ ለምሳሌ የዝዋይ ሀይቅን ብቻ ብናነሳ ወደ ሀይቁ የሚገቡ የመቂ ፣ ከተር እና የቡልቡላ ወንዞች ባለፉት ሠላሳ እና አርባ ዓመታት የመስኖ ሥራ በመጨመሩ ወደ ሐይቁ የሚገባው የውሃ ፍሰት መጠን እንዲቀንስ አድርጎታል ፡፡ የውሃ መጠን መቀነስ ዓሳን የመሳሰሉ የውሃ ውስጥ አካላት መራቢያ የሆኑ ካባቢዎችን በመረበሽ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡
መፍትሄ ጠቋሚ አማራጮች
የንጽህ ውሃ ሥነ ምህዳር ተማራማሪውበሀይቆቹ ላይ ለተፈጠረው ሥጋት መፍትሄ ያሉትን አማራጭ ሀሳብ ጠቅሰዋል ፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ዘላቂነት ያለው ዝርዝር የውሃ ሀብት ዕቅድ ማዘጋጀትና መፈጸም እንደሚገባ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ዝናቡ “ በዋናነት ቀደም ሲል የወጡ የውሃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደርን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ የተፈጥሮ ሀብትና የአካባቢ ጥበቃ አዋጆችን ተግባራዊ ማድረግ ያሥፈልጋል ፡፡ በተለይም የሀይቆች መጋቢ የሆኑ ወንዞችን በአግባቡ በማስተዳደር ወደ ሀይቁ ክልል የሚገባው የውሃ መጠን እንዳይቀንስ ለማድረግ የሚያሥችል ስራ መሠራት ይኖርበታል ፡፡ ይሁንና ዛሬ ላይ እነኝህ ምክረ ሀሳቦች ተቀባይነት ካላገኙ ችግሩ የሚቀጥል ነው የሚሆነው “ ብለዋል ፡፡
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባዔ
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባዔ ከተመሰረተ 60 ዓመታት አስቆጥሯል ፡፡ በየሦስት ዓመቱ በአገር ውስጥ እና በተለያዩ የውጭ ሀገራት ሲካሄድ መቆየቱም ይታወቃል ፡፡ በኮንፈርንሱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ኮንፍረንሱ የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታትና በጥናት ላይ የተመሠረቱ ምክንያታዊ ውይይቶችን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል ፡፡
በኮንፍረንሱ ላይ በተለያዩ አገራት ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት የተውጣጡ ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ሲሆን በተለያዩ ዘርፎች ላይ የጥናት እና ምርምር ውጤታቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃ ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ