የስዊድን ዕስረኞች መለቀቅና የእስር ቤት ቆይታቸው
ዓርብ፣ ግንቦት 17 1999እስረኞቹ ደረሰባቸው ስለተባለው ስቃይ ዶይቼቬለ ራድዮ የአማርኛው ክፍል የጠየቃቸው አንድ የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣን መስሪያ ቤታቸው የጠበቃውን መረጃ ለማግኘት እየጠበቀ መሆኑን አስታውቀዋል ። ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰሩት ሶስቱ ስዊድናውያን ተለቀው ወደ ሀገራቸው ስዊድን መመለሳቸው እንደተሰማ የስዊድን መንግስት በዕርምጃው መደሰቱን ነበር የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የገለፀው ። የስዊድናውያኑ ጠበቃ ብዮርን ሁርቲክም የዕስረኞቹን መለቀቅ ያልተጠበቀ ግን ዕጹብድንቅ ብለውት ነበር ። እኝሁ ጠበቃ ትናንት ለአንድ የስዊድን ህዝብ ራድዮ ጣቢያ እንዳስታወቁት ደግሞ ስዊድናውያኑ በኢትዮጵያ ዕስርቤት ተሰቃይተዋል ፤ ተንገላተዋል ። የታሰሩት ከማንም በማይገናኙበት አንድ ሜትር ተኩል ካሬ ስፋት በነበረው ጠባብ ቦታ ውስጥ ነበር ። አብዛኛውን ጊዜም እጅና እግራቸው በካቴና እንደተጠፈረ ነው የቆዩት ። ሲተኙ እንክዋን የታሰረው እጃቸው አይፈታም ። ከዚህ በተጨማሪም በምርመራ ወቅት አካላዊና ስነልቦናዊ ስቃይ ደርሶባቸዋል ብለዋል ጠበቃ ቦይርን ሆርቲክ ። ጠበቃው ስዊድናውያኑ ደረሰባቸው ስላሉት ዕንግልት ባልደረባችን ሉድገር ሻዶምስኪ የጠየቃቸው የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤት ቃል አቀባይ ኒና ኤርስማን እስካሁን ስለሰዎቹ አያያዝ ምንም ዓይነት ነፃ ዘገባ የለንም ነው ያሉት ። አክለውም የጠበቃውን መረጃ ለማግኘት እየጠበቅን ነው ብለዋል ። የኢትዮጵያ መንግስት ሶስቱ ስዊድናውያን ከሶማሊያ ተዋጊዎች ጋር ገጥመው ወግተውናል ነው የሚለው ። የስዊድን መንግስት በበኩሉ ለዚህ ምንም ማረጋገጫ የለንም ነው መልሱ ። ቃል አቀባይ ኒና አርስማን እንደሚሉት ዜጎቻቸው የታሰሩበት ምክንያት ግን እስካሁን በይፋ አልተገለፀላቸውም
“እንዲያውም ፤ የታሰሩበትን ትክክለኛውን ምክንያት በፍፁም አልነገሩንም ። ምንም ዓይነት ክስና ትክክለኛ ህጋዊ አካሄድ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የተያዙት ግለሰቦች በተቻለ ፍጥነት እንዲለቀቁ ጠይቀናል ። ይህም እነርሱን ወደ ስዊድን ለማምጣት ቅድሚያ የሰጠነው ጉዳይ ነበር ። “
ስዊድናውያኑ ከአምስት ወራት በፊት ሶማሊያ ውስጥ በኢትዮጵያ መንግስትና በሶማሊያ ፍርድ ቤቶች ህበረት መካከል ውጊያ እንደተጀመረ ከሶማሊያ ሸሽተው ኬንያ ከገቡ በኃላ እዚያ ታስረው ወደ መቅዲሾ ከተላኩ በኃላ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የተወሰዱት ። ለመሆኑ የስዊድን መንግስት ግለሰቦቹ ሶማሊያ ለምን እንደሄዱና የት እንደተያዙ ያውቅ ይሆን ?
“በትክክል የት እንደተያዙ አናውቅም እንዲሁም በዕርግጥ ሶማሊያ ውስጥ ምን ይሰሩ እንደነበርም አናውቅም ። ቢያንስ ከአንድ ዓመት በፊት አንስቶ ሰዎች ወደ ሶማሊያ እንዳይሄዱ እንመክራለን ። ካለፈው ገና ወዲህም ማናቸውም ሶማሊያ የሚገኝ የስዊድን ዜጋ ሶማሊያን ለቆ እንዲወጣ ተናግረናል ። ምክንያቱም እዚያ ያለው የጦርነት ዓይነት ሁኔታ ነው ። ሆኖም እነርሱ እዚያ ምን ይሰሩ እንደነበር አናውቅም ። “
ሶስቱን ስዊድናውያን ለማስፈታት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተካሄደው ድርድር የስዊድን መንግስት የልማት ዕርዳታን መያዝን የመሳሰሉ ግፊጦችን አድርጎ እንደሆነም ቃል አቀባይ ኒና አርስማን ተጠይቀው ነበር ።
“የተካሄዱትን ድርድሮችና በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸውን ወገኖች ዝርዝር ይፋ ወደ ማድረግ አንገባም ። ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር የሚያገናኘንን አማራጭ በሙሉ ሞክረናል ። እዚህ ስዊድን እንዲሁም በአዲስ አበባና በኬንያ በያለበት ሁሉ ግባችን ለመምታት ይኽውም ለፍርድ እስካልቀረቡ ድረስ ከዕስር እንዲለቀቁ ያለውን አማራጭ ሁሉ ሞክረናል “
በአሸባሪነነት ተጠርጥረው ሶማሊያ ውስጥ የታሰሩ አርባ አንድ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መላካቸውን የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ወር አስታውቆ ነበር ። ከመካከላቸው የዩናይትድ ስቴትስ የቱኒዚያ የዩጋንዳ የሳውዲ አረብያ እና የታንዛኒያ ዜጎች ይገኙበታል ። ስለተለቀቁት የስዊድን ዜጎችና ስለተቀሩት ዕስረኞች የኢትዮጵያ መንግስት ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እና የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሀላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም ።