1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች ግድያና አዲሱ የመጠለያ ጣቢያ በመተማ

ሰኞ፣ ሐምሌ 15 2016

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ ስደተኞች ላይ ልታወቁ ታጣቂዎች በወሰዱት ጥቃት ሁለት ሱዳናውን ስደተኞች መገደላቸውንና ሌሎች 10 መቁሰላቸውን ስደተኞችና የተ.መ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) አስታወቁ፡፡ ከመጠለያው ከወጡ ስደተኞች መካከል ከ560 በላይ የሆኑት “አፍጥጥ” ወደተባለ አዲስ መጠለያ መዛወራቸው ተመልክtቷል።

ፎቶ ማህደር፤ የሱዳን ስደተኞች በአድሬ ሆስፒታል
ፎቶ ማህደር፤ የሱዳን ስደተኞች በአድሬ ሆስፒታልምስል Mohammad Ghannam/MSF/REUTERS

የስደተኞች ግድያና አዲሱ የመጠለያ ጣቢያ በመተማ

This browser does not support the audio element.

የስደተኞች ግድያና አዲሱ የመጠለያ ጣቢያ በመተማ

ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 13/2016 ዓ ም ምሽት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ ስደተኞች ላይ ልታወቁ ታጣቂዎች በወሰዱት ጥቃት ሁለት ሱዳናውን ስደተኞችመገደላቸውንና ሌሎች 10 ያክሉ ደግሞ መቁሰላቸውን ስደተኞችና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) አስታወቁ፡፡ በሌላ በኩል ቀደም ሲል ከመጠለያቸው ከወጡ ስደተኞች መካከል ከ560 በላይ የሆኑት “አፍጥጥ” ወደተባለው መጠለያ መዛወራቸውን ስደተኞችና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክተዋል፡፡

ባለፈው ግንቦት 2016 ዓ ም መጀመሪያ ላይ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ኩመርና አውላላ ከተባሉ መጠለያዎች ይኖሩ ከነበሩ ስደተኞች መካከል 1ሺህ 300 የሚሆኑት “የፀጥታና የተለያዩ ግብዓቶች ችግሮች ገጥሞናል” በሚል ከመጠለያቸው ወጥተው ጫካ ውስጥና በመንገድ ዳር መስፈራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ስደተኞቹ ወደ ቀደመ መጠለያቸው እንዲመለሱ በኢትዮጵያ መንግስት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም አብዛኛዎቹ አሁንም መመለስ እንዳልቻሉ የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በስደተኞች ላይ የደረሰ ጥቃት

ባለፈው ቅዳሜ በግምት ምሽት 1 ሰዓት አካባቢ በነኚሁ መንገድ ዳር ባሉ ስደተኞች ላይ ያልታወቁ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት ባልና ሚስት ስደተኞች መገደላቸውንና ሌሎች 11 ያክሉ እንደቆሰሉ አንድ ተፈናቃይ ለዶቼ ቬሌ አስረድተዋል፡፡

የቆሰሉት ሰዎች በተለያዩ ተቋማት ህክምና እወሰዱ እንደሆነም አስተያየት ሰጪው አመልክተዋል፣ ጥቃት የደረሰባቸው ስደተኞች ቀደም ሲል በፀጥታ ችር ምክንያት ይኖሩበት ከነበረ መጠለያ ወጥተው በመንገድ ዳር የነበሩ እንደሆኑም ገልጠዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ማረጋገጫ

የተባበሩት ምንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ለዶቼ ቬሌ በኢሜል በላከው ደብዳቤ እንዳሳወቀው “ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በስደተኞቹ ላይ ታጣቂዎች በወሰዱት ጥቃት 2ቱ መገደላቸውንና 9 መቁሰላቸውን ማረጋገጡን አመልክቷል፣ “ አሳዛኝ” ባለው ድርጊትም ድርጅቱ ማዘኑን ጠቅሷል፡፡

ሰኔ 9/2016 ዓ ም ምዕራብ ጎንደር ውስጥ ከገንዳ ውሀ ከተማ  ወደ ነጋዴ ባህር ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ላይ  ልዩ ስሙ “ደረቅ ዓባይ” ከተባለ ቦታ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 2 ኢትዮጵያውያንና አንዲት የሱዳን ስደተኛ መገደላቸውንና ሌሎች ሁለት ኢትዮጵያውያን ደግሞ መቁሰላቸውን የዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በወቅቱ ማሳወቁ የሚታወስ ነው፡፡

ፎቶ ማህደር፤ የሱዳን ስደተኞች ምስል LUIS TATO/AFP

የስደተኞች ወደ አዲሱ መጠለያ መመለስ መጀመር

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በፀጥታና በሌሎች ምክንያቶች ከኩመርና ከአውላላ የስደተኞች ጣቢያዎች ወጥተው በመንገድ ዳር ከነበሩ ስደተኞች መካከል የተወሰኑት “አፍጥጥ” ወደተባለው አዲስ የስደተኞች መጠለያ መመለሳቸውን ስደተኞች ተናግረዋል፣ አንድ ስደተኛ እንዳለው ውይይቶች ከተካሄዱ በኋላ የተወሰኑ ስደተኞች ወደ አዲሱ መጠለያ መመለስ ጀምረዋል፡፡ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ውጪ መሄድ እንፈልጋለን ያሉ ሌሎች ስደተኞች አሁንም ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም ነው ያለው፡፡

የስደተኞች ከኢትዮጵያ የመውጣት ፍላጎት

“ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ ከስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎትና ከኢትዮጵያ መንግስት የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች መንገድ ዳር ካሉ ስደተኞች ጋር ባደረጉት ውት መሰረት የተወሰንን ስደተኞች በኃይል ሳይሆን በፍላጎታችን ተመልሰናል፣ ከተመላሾች አንዱ እኔ ነኝ፣ ግን ብዙዎቹ ፈቃደኛ አይደሉም፣ ከኢትዮጵያመውጣት ነው የሚፈልጉ፡፡” ብሏል፡፡

አንዳንድ ተፈናቃዮች አዲስ ወደተሰራ መጠለያ መሄድ ቢጀምሩም ብዙዎቹ አሁንም ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ነው ሌላ አስተያየት ሰጪ ስደተኛ ያመለከተው፡፡የብዙዎቹ ፍላጎት ከኢትዮጵያ ምድር መውጣት እንደሆነ አስረድቷል፡፡

የመተማ ወረዳ አስተዳደር አስተያየት

በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ሞገስ መንገድ ዳር ያሉ ስደተኞች ወደ መጠለያ እንዲመለሱ ጥረት ቢደረግም አብዛኛዎቹ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለጥቃት እየተጋለጡ መሆኑን ለዶቼ ቬሌ በስልክ ገልጠዋል፣ መንገድ በመዝጋት ጭምር ለዞኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንቅፋት እየሆኑ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ሰሞኑን  ጥቃት የተፈፀመባቸም ከመጠለያ በመውጣታቸው እንደሆነ ገልጠዋል፡፡

“አፍጥጥ” የተባለው አዲስ መጠለያ ጣቢያም የተሻለና ጥበቃም የተመደበለት በመሆኑ ስደተኞች ወደተዘጋጀላቸው መጠለያ እንዲመለሱ አስተዳዳሪው ጠይቀዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ማሳሰቢያ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ትናንት ለዶይቼ ቬሌ እንዳሳወቀው የመጀመሪያዎቹ 561 ስደተኞች አዲስ ወደተገነባው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ገብተዋል፡፡

ፎቶ ማህደር፤ የሱዳን ስደተኞች ምስል Karel Prinsloo/AP/picture alliance

ድርጅቱ አክሎም መንገድ ዳር ያሉ ስደተኞች ሁኔታ እንዳሳሰበው አመልክተዋል፣ ስደተኞቹ የኢትዮጵያ መንግስትን ህግና ስርዓት አክብረው እንዲኖሩና ወደተዘጋጀላቸው አዲስ መጠለያ ጣቢያ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በኩመርና አውላላ የስደተኞች ጣያያ የሚገኙ 12ሺህ 500 ያክል አብዛኛዎቹ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን የኤርትራና የሶማሌያ ስደተኞች በሂደት ወደ አዲሱ መጠለያ ይገባሉ ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ከ1 ሚሊዮን 100ሺህ በላይ ስደተኞችን በመቀበል በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW