1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ምስቅልቅል፣ የአፍሪቃ ቀንድ ትርምስ

ሰኞ፣ ጥር 29 2015

ከ1991 ጀምሮ አምባ ገነን አገዛዝን ለማስወገድ፣የጎሳ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣የጦር አበጋዞችን በመደገፍ የነበረዉ ዉጊያ አዲስ መልክና ባሕሪ ተላብሶ ቀጠለ።ዓመት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ዉጊያዉ የሶማሌዎች ከመሆን አልፎ ከጋና ፖሊስ እስከ ዩጋንዳ ጦር፣ ከኬንያ ወታደር እስከ አሜሪካኖች ኮማንዶ ያነካካ፣ መቶ ሺዎች የሚያረግፍ ሆነ።15 ዓመቱ።

Gipfeltreffen der Frontstaaten Somalias in Mogadischu
ምስል Ethiopian PM Office

የአፍሪቃ ሕብረት ጦር እስከ 2024 ከሶማሊያ እንዲወጣ ተወስኗል

This browser does not support the audio element.

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሕሙድ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊዉን አሸባብን ለማጥፋት ሙሉ ጦርነት ካወጁ ሰባተኛ ወራቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ከሶማሊያ አስወጥታዉ የነበረዉን እግረኛ ጦሯን መልሳ ካዘመተች ስምንተኛ ወሯ።የአፍሪቃ ሕብረት ሶማሊያ ዉስጥ 22 ሺሕ ወታደሮች ካሰፈረ 15ኛ ዓመቱ።ባለፈዉ ሳምንት ሞቃዲሾ ዉስጥ የተሰበሰቡት የራስዋ የሶማሊያ፣ኢትዮጵያ፣ የጅቡቲና የኬንያ መሪዎች «ሶማሊያን ከአሸባብ ነፃ ለማዉጣት» ፎከሩ።እስካለፈዉ ሳምንት የትነበሩ? ሶማሊያ ለ32ኛ ዓመት፣ኢትዮጵያ ለ5ኛ ዓመት እየተተራመሱ፣ሶማሊያ፣ኢትዮጵያ፣ኬንያ ከ20 ሚሊዮን የሚበልጥ ዜጋቸዉ በረሐብ እየተሰቃየ የጦሩ ዘመቻ፣የመሪዎቹ ዛቻለዉጤት ይበቃ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ከሰሜንና ሰሜን ምስራቅ የአደን ባሕረ ሰላጤን የተንተራሰችዉ፣ ከደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሕድን ዉቅያኖስን የተረገጠችዉ ያቺን ሾጣጣ፣ ስልታዊ ሐገርን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች ወዲሕ አንድ አድርጎ ለመግዛት ብዙ  ርዕዮተ-ዓለምና ስልት ተሞክሮባታል።አብዲረሺድ ዓሊ ሸርማርኬ የምዕራባዉያኑን፣ ዚያድ ባሬ ሾሻሊስታዊዉን ርዕዮተ ዓለም ገቢር አድርገዉባታል።ጄኔራል ፋራሕ አይዲድ የጦር አበጋዝ አገዛዝን፣ከአብዲ ቃሲም ሳላት አሕመድ እስከ አብዱላሒ የሱፍ አሕመድ የተፈራረቁት የጎሳ፣የፖለቲካና የጦር አበጋዝ ስብጥር አስተዳደርን ሞክረዉባታል።አልተሳካም።

ሰኔ 2009 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ዶቸ ቬለ እዚሕ ቦን ባዘጋጀዉ ስብሰባ ላይ የተካፈለ አንድ የሶማሊያ ጋዜኛ እንዳለዉ ሶማሌዎችን አንድ ሊያደርግ ከሚችለዉ ሁሉ ያልተሞከረዉ እስልምና ኃይማኖት ነበር አለ።እሱን ደግሞ ኃያል ወዳጆቻንም ጎረቤቶቻችንም ስላልፈቀት በቅጡ ሳይሞከር ፈረሰ።

አላበለም።ዋሽግተን-ብራስልስ ለንደኖች አልፈለጉትም።ኢትዮጵያ ለዉስጥ ችግሯ መሸፈኛ ይሁን ምዕራባዉያኑን ለመደለያ ብቻ አልፈቀደችዉም።የፖለቲካ ተንታኞች ብዙ ጊዜ አንድሚሉት የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ አገዛዝ በ2006 የኢትዮጵያን ጦር ሶማሊያ ያዘመተዉ በሁለት ምክንያት ነዉ።

የአፍሪቃ ሕብረት ጦር በሶማሊያ በከፊልምስል Mohamed Abdiwahab/AFP/Getty Images

በ2005 ኢትዮጵያ ዉስጥ የተደረገዉ ምርጫ  ዉጤት ባስከተለዉ ዉዝግብ ሰበብ ምዕራባዉያን መንግስታት የመለስን አገዛዝ ገሸሽ ገለል ማድረጋቸዉን እንዲያቆሙ ለመማረክ፣ ወይም አቅጣጫ ለማሳት-አንድ፣ የያኔዋ የኢትዮጵያ ጠላት ኤርትራ ከሶማሊያ የሸርዓ ፍርድ ቤት ሕብረት ሹማምታት ከፊሉን በመደገፏ-ሁለት።

ምክንያቱ አንዱም  ሆነ ሁለቱ ወይም ሌላ በፕሬዝደንት ጆርጅ ዳብሊዉ ቡሽ አስተዳደር ሙሉ ፈቃድ ኢትዮጵያ ያዘመተችዉ ጦር፣ የሸርዓ ፍርድ ቤቶች ስብስብን ከቪላ ሞቅድሾ ሲያስወጣዉ እስከዚያ ዘመን ድረስ ብዙም የማይታወቀዉ አሸባብ የሶማሊያ ጠንካራ ኃይል ሆኖ ብቅ አለ።ሶማሊያ፣የሽብር ምድር

ከ1991 ጀምሮ አምባ ገነን አገዛዝን ለማስወገድ፣የጎሳ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣የጦር አበጋዞችን በመደገፍ ወይም በመቃወም ይደረግ የነበረዉ ዉጊያ አዲስ መልክና ባሕሪ ተላብሶ ቀጠለ።ዓመት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ዉጊያዉ የሶማሌዎች ከመሆን አልፎ ከጋና ፖሊስ እስከ ዩጋንዳ ጦር፣ ከኬንያ ወታደር እስከ አሜሪካኖች ኮማንዶ ያነካካ፣ መቶ ሺዎች የሚያረግፍ ሆነ።15 ዓመቱ።

አሸባብን ለሚወጋዉ የዉጪ ጦር አማካሪ የነበሩት አሜሪካዊዉ የጦር አዋቂ ጄሰን ሐርትዊግ ሶማሊያዊዉ ጋዜጠኛ «የቀረን አማራጭ ከሸፈ» ባለ በ10ኛ ዓመቱ በ2019 እንደጻፉት ለሶማሊያ ሰላም አብነቱ ከአሸባብ ጋር መደራደር ነዉ።የምስራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝና ደራሲ የሱፍ ያሲንም ወታደራዊ ሐይል ዉጤት ማምጣቱን ይጠራጠራሉ።

« እንደዚሕ ዓይነት አክራሪ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ቡድኖች በአፍሪቃም ይሁን በሌላዉ ዓለም ለመመስረታቸዉ ምክንያት የሆኑ ማሕበራዊ፤ኃይማኖታዊና ሌሎችም ጉዳዮች ካልታከሙ በወታደራዊ ኃይል ብቻዉን ዉጤት መምጣቱን አላዉቅም።ያጠራጥራልም።»

የእስከዛሬዉ እዉነት ከማጠራጠርም በላይ የጦር ጡንቻ ዉጤት አልባነቱን ያረጋግጣል።የዩናይትድ ስቴትስ ታንከኛ ጦር መኮንን የነበሩት ጄንሰን ሐርትዊንግ እንደሚሉት የርስ በርስ ጦርነት ለመሪዎች ወይም ለፖለቲከኞች ሶስት አማራጮችን ይሰጣል።

የአሸባብ ተዋጊዎች ትርዒትምስል picture alliance / AP Photo

ወሳኝ ድል-አንድ።የድርድር አማራጭ-ሁለት ወይም ግጭት ጦርነቱን መቀጠል-ሶስት።የሶማሊያ መንግስት በጎሳ ዉክልና ባዲስ መልክ ከተዋቀረ ከ2009 ወዲሕ የተፈራረቁት መሪዎች በአፍሪቃ ሕብረትና በዩናይትድ ስቴትስ ጦር ድጋፍ አሸባብን ለማስወገድ ተዋግተዋል።አላሸነፉም።

ለወትሮዉ ከፖለቲካ ይበልጥ ወደ ኃይማኖቱ፣ ከወታደራዊዉ ኃይል ይብስ ወደ ሰብአዊነቱ ያዳላሉ የሚባሉት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ የፕሬዝደንነቱን ስልጣን ለሁለተኛ ጊዜ ከያዙ በኋላም በጦር ኃይል ከመታበይ ሌላ አማራጭ አላቀረቡም።

ባለፈዉ ነሐሴ በአሸባብ ላይ ሙሉ ጦርነት አወጁ።አሸባብ ቪላ ሞቃዲሾ አጠገብ ሳይቀር ማሸበሩም ቀጠለ።ባለፈዉ ጥር 12 በአደባባይ ሰልፍ አሸባብን አስወገዙ።ዜጎቻቸዉን አስጠነቁም።

«የማታዉቁትን ሰዉ መለየትና ማንነቱን ማወቅ እዚሕ ከተማ ዉስጥ ፀጥታን ለማስከበር በጣም አስፈላጊ ነገር ነዉ።ባካባቢያችሁ ያለዉን ሰዉ ማንነት ማጣራት ካልቻላችሁ ለሚመለከተዉ ባለስልጣን ጠቁሙ።ይሕ መጥፎ ነገር አይደለም።ጎረቤቶቻችንም አይጎዳም።ይልቅዬ መተማመንና ፀጥታን ለማስፈን ይጠቅማል።ይሕን ስታደርጉ ብቻ ነዉ ሰላም ማስከበር የሚቻለዉ።»

 

የፕሬዝደንት ሐሰን ሼሕ ማሕሙድ የዉጊያ ስልት፣ ፀጥታ የማስከበር ዕቅድ፣ ዛቻና ዘመቻ ሲተነተን ባናዲር የተሰኘዉ የሞቃዲሾ ክፍለ-ከተማ የአስተዳደር ቢሮን አሸባብ አወደመዉ።እምስት ሰዉ ተገደለ።የአካባቢዉ ነዋሪ «ምፀት» ይሉታል።አስገራሚ»

                                         

«በዚሕ ጥቃት ሁላችንም ተጎድተናል።ተራዉ ሰዉ ይሁን የተማረዉ ሁሉም ተነክቷል።የንግድ መደብሮች ተዘግተዋል።ጦር በሰፈረበት ቦታ ይህ መድረሱ በጣም አስገራሚ ነገር ነዉ።»

ሶማሊያ ዉስጥ ከ2007 ጀምሮ የሰፈረዉ ከ22 ሺሕ የሚበልጥ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር አሸባብን ከሶማሊያ ትላልቅ ከተሞች ለማባረር ጠቅሟል።ጦሩ አሁንም ሶማሊያ አሸባብ ጋር እየተዋጋ ነዉ።የሶማሊያ መንግስት ጦር፣ ተባባሪ ሚሊሻዎችና የአካባቢ ኃይላትም አሸባብን ይወጋሉ።

እኒያ ቀጫጫ፣ ፂማም፣በቅጡ ያልሰለጠኑ፣ ወታደራዊ ዕዛቸዉ የማይታወቅ ደፈጣ ተዋጊዎች ግን ሲመቻቸዉ በፊት ለፊት ዉጊያ፣ ሲያቅታቸዉ  ከቦምብ አረር ጋር እያረሩ መቶዎችን መፍጀታቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።

የአክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አባላት ከሶማሊያ አልፈዉ ኬንያና ኢትዮጵያንም ያጠቃሉ።የሞቃዲሾ፣የአዲስ አበባ፣የናይሮቢና የጅቡቲ መሪዎች ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ግን አሁንም አክራሪዉን ቡድን በኃይል ከማንበርከክ ዉጪ የድርድር  አማራጭ አልታያቸዉም።አቶ የሱፍ ያሲን ግን የሞቃዲሾዉ ጉባኤና ዉሳኔ የአካባቢዉ ሐገራትን ተለዋዋጭ የኃይል አሰላለፍ ከማሳየት ባለፍ ለሶማሊያም ሆነ ለአካባቢ ሰላም የሚተክረዉ የለም ባይ ናቸዉ።

ምስል DW

አንድ ጊዜ ይተባበራሉ።ከዚያ ይፋለሳሉ።እንደገና የሆነ አዲስ ሕብረት ይፈጥራሉ።እንደገና ሲሰላለፉ፣ሲወጋገኑ ነዉ የምናየዉ።እንዳልከዉ ሶማሊያ ዉስጥ ሰላም የመፍጠሩ ሒደት በቀላሉ የሚሆን አይደለም----ምናልባት ያሜሪካ መንግስት በሰማይም ይሁን በሚሳዬል የሚያደርገዉ ነገር ከሌለ በስተቀር ለችግሩ ምክንያት የሆኑት መፍትሔ ካላገኙ እነሱን (አሸባብን) ከስር መሰረቱ መንቀል የሚቻልበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም።»

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ካየር በሰዉ አልባ አዉሮፕላን (ድሮን) ከምድር በልዩ ኮማንዶ ጦር የአሸባብ ተዋጊዎችን እያደነ ይገድላል።

በ2018 የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከሶማሊያ አስወጥተዉት ከነበረዉ 750 እግረኛ ጦር 500 ያክሉ ተመልሰዉ ወደ ሶማሊያ መዝመታቸዉን የአሜሪካ ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።ጦሩ በቅርቡ በሶማሊያ የእስላማዊ መንግስት ተጠሪ የተባለ ግለሰብን መግደሉን የአሜሪካዉ የአፍሪቃ ዕዝ አስታዉቋል።

ከሶማሌያ መንግስት የወገኑ ሶማሌዎች ግን ዛሬም በነገ ተረኛ ሟችነት እየተሸማቀቁ ነዉ።አስከፊ ረሃብ በሶማልያ

«በአሸባብ አዋኪዎች ከሚገደሉት አንዱ እሆናለሁ ብዬ አስባለሁ።ይሁንና ሲያጠቁኝ እራሴን እንደምከላከል መዘንጋት የለባችሁም።እነሱን መቋቋም የሚቻለዉ በዚሕ መንገድ ብቻ ነዉ።እዚሕ የተሰለፍነዉም እርስበርሳችን ለመደጋገፍ ነዉ።»

ሶማሊያ ዉስጥ በርካታ ጦር ካሰፉሩት የአፍሪቃ ሐገራት መካከል የዩጋንዳዉ ፕሬዝደንት ዩሪ ሙሴቬኒ በሞቅዲሾዉ ጉባኤ አለመገኛታቸዉ አነጋጋሪ ነዉ።አንዳዶች እንደሚሉት አንጋፋዉ ፖለቲከኛ በሶማሊያዉ ማብቂያየለሽ ግጭት ስለተሰላቹ ወይም ከሶማሊያዉ ይልቅ የኮንጎዉ ቀዉስ ይበልጥ ስለሚጠቅማቸዉ ወይም ትኩረታቸዉን ስለሰባዉ ሊሆን ይችላል።

ምዕራባዉያን ሐገራት ደግሞ ከሶማሊያ፣ከኢትዮጵያ፣ ከኮንጎ፣ ከማሊም ሆነ በተቀረዉ ዓለም ካሉ ግጭት ቀዉሶች ሁሉ ለዩክሬን ጦርነት ልዩ ትኩረትና ለዩክሬን ድጋፍ መስጠት ከጀመሩ ዓመት ሊደፍኑ ሳምንታት ቀራቸዉ።

የሞቃዲሾ ሰላማዊ ሰልፍምስል AP

እስካለፈዉ ዓመት ድረስ ሶማሊያ ለሰፈረዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር 2.3 ቢሊዮን ዩሮ የከሰከሰዉ የአዉሮጳ ሕብረት ድጋፉን ለመቀነስ ወስኗል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም የአፍሪቃ ሕብረት ጦር እስከ 2024 ድረስ ወደየሐገሩ እንዲበተን ወስኗል።

የሞቃዲሾ ጉባኤተኞች ከሚመሯቸዉ ሐገራት  ከጅቡቲ በስተቀር ከ20 ሚሊዮን የሚበልጥ የሶስቱ ሐገራት ሕዝብ በረሐብ እየተጠበሰ ነዉ።

በተለይ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ብዙ መቶ ሺሕ ሕዝብ ያረገፈዉን ጦርነት በድርድር የማስወገዳቸዉ ድፈረት፣ብልጠት ሲዘረዘር የጎሳ ጥቃት፣ ግጭትና የፀጥታ መታወክ ሺዎችን እያረገፈባት ነዉ። በኃይማኖት ሰበብም የተቋጠረባት ቂም ፈጥኖ ካልረከሰ ለሌላ ምናልባትም ለአስፈሪ ግጭት እየተንደረደረች ነዉ።በዚሕ መሐል የ115 ሚሊዮኖቹ ሐገር ሶማሊያ ዉስጥ ሰላም ታሰፍናለች ብሎ መጠበቅ በርግጥ ጅልነት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW