1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሶማሊያ እና የሶማሊላንድ መሪዎች ሰሞነኛ የአዲስ አበባ ጉብኝት ዓላማው ምን ይሆን?

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ዓርብ፣ ጥቅምት 7 2018

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት እና ልዑካቸው ትናንት ወደ ሐርጌሳ ተመልሷል። ይህን ጉብኝት በሚመለከት ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምንም የተባለ ነገር የለም።

 የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን አብዲላሂ
የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን አብዲላሂ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ምስል፦ Ministry of Foreign affairs of Somaliland

የሶማሊያ እና የሶማሊላንድ መሪዎች ሰሞነኛ የአዲስ አበባ ጉብኝት ዓላማው ምን ይሆን?

This browser does not support the audio element.

 

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት እና ልዑካቸው ትናንት ወደ ሐርጌሳ ተመልሷል። ይህ ጉብኝት «ትልቅ ውጤት ያስመዘገበ» ነበር ያለው የራስ ገዟ ሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን አብዲላሂ «ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ውጤታማ» ያለውን ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቋል። ይህን ጉብኝት በሚመለከት ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምንም የተባለ ነገር የለም። ከአራት ቀናት በፊት አዲስ አበባን የጎበኙት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ «በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች» ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መወያየታቸው ግን ተጠቅሷል። ለመሆኑ ሁለቱ መሪዎች በአንድ ሳምንት ውስጥ አዲስ አበባን የመጎብኘታቸው ምክንያት ምን ይሆን? የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የፖለቲካ ተንታኝ በማነጋገር ሰለሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዘገባ አጠናቅሯል።

የጉብኝቶቹ ዓላማ «በቀጥታ ከፀጥታ ጋር የተገናኘ» ሊሆን ይችላል

የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሃመድ ሰሞነኛ የአዲስ አባባ ጉብኝት «ወዳጅነት እና የትብብር ግንኙነትን የማጠናከር» ብሎም «በመጓጓዣ፣ በንግድ፣ በደኅንነት እና በሌሎች የሁለትዮሽ መስኮች ትብብርን የማሳደግ» ዓላማ እንደነበረው የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስቀድሞ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ፕሬዝዳንቱ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ትናንት መመለሳቸውን በፎቶ ጭምር አስደግፎ አውጥቷል። ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት «ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል» ሲልም ገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአራት ቀናት በፊት የሶማሊያውፕሬዝዳንትም አዲስ አበባን ጎብኝተው ተመልሰዋል።

የሁለቱ መሪዎች ጉብኝት መገጣጠም ወይስ የታቀደበት የሚለውን ስማቸውን ትተው ትንታኔ የሚሰጡ አንድ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የፖለቲካ ተንታኝን ጠይቀናቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

«ጉብኝታቸው በቀጥታ ከፀጥታ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ምክንያቱም አሁን ያለው የፀጥታ ሁኔታ ለሁሉም ሰላም የሚነሳ ስለሆነ።»

የራስ ገዟ ሶማሊላንድ በርበራ ወደብፎቶ ከማኅደርምስል፦ Solomon Muchie/DW

«ኢትዮጵያ ሶማሊላንድን እንደ ሀገር ታይበት የነበረው አተያይ መቀየሩን በተግባር አይተናል»

ሶማሊያ እንጂ «ሶማሊላንድ የምትባል ሀገር የለችም» ያሉት ተንታኙ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን በአንካራ ከሸመገሉ በኋላ ውሉ አንዳቸው የሌላኛቸውን «ሉዓላዊነት ለማክበር ቃል መግባታቸውን ስላሳየን የወደብ አጠቃቀምን ጉዳይ በተመለከተ ከሞቃዲሾ እንጂ ከሐርጌሳ ጋር ሌላ ውል እንደማይኖራቸው መተማመኛ የተገኘ እና እየታየ ያለው ይሄው ነው» ሲሉ «እውቅና» የሚባለው ጉዳይ መቅረቱ በተግባር እየታየ ነውም ብለዋል።

«ኢትዮጵያ ሶማሊላንድን እንደ ሀገር ታይበት የነበረው አተያይ መቀየሩን በተግባር አይተናል። ምክንያቱም አብረው ሲቆሙ አናያቸውም፣ በይፋ ላውቅሽ ነው የሚለ እና በይፋ የሚገለጠውን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ አናይም።»

መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ እውነታ ይህ ከሆነ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድን ምን ያገናኛቸዋል?

ተንታኙ እንደሚሉት ሶማሊላንድ ውስጥ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ንብረት የሆነው ዱባይ ወርልድ (DP World) የተገነባውየበርበራ ወደብን ከመጠቀም አንፃን ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ምልከታቸውን ገልፀዋል።

«ለንግድ እና ለሌላ መሰል የንግድ ተግባራት የሚሆን ወደብን በተለይ እየለማ ያለው [የበርበራ ወደብ] ደንበኛ ይፈልጋል» ሲሉ በዚህ እና መሰል ጉዳዮች ሊገናኙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW