የሶማሊያ ጦርነትና ኤርትራ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 29 2004የኬንያ ጦር የሶማሊያዉን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብን ለመዉጋት ደቡባዊ ሶማሊያ መዝመቱ የኤርትራንና የአካባቢዉ ሐገራትን ዉዝግብ እንዳዲስ አግሞታል።ኬንያ ባለፈዉ ሳምንት ኤርትራ አሸባብን ሳታስታጥቅ አትቀርም ካለች ወዲሕ የኢጋድ አባል ሐገራት በተለይም ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ሁለተኛ ማዕቀብ እንዲጣል እየገፋፉ ነዉ።ኤርትራ ለአሸባብ ጦር መሳሪያ ታቀብላለች የሚለዉን ወቀሳ አጥብቃ ተቃዉማዋለች።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀብ እንዳይጥልም እየጠየቀች ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።
ምክር ቤቱ በኤርትራ ላይ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በሁለት-ዘጠኝ ከጣለባት ማዕቀብ በተጨማሪ ሌላ ማዕቀብ እንዲጥልባት የሚደረግበት ግፊት ሞቅ-ቀዝ ቀዝ ሲል ነበር የከረመዉ።ባለፈዉ ሳምንት የኬንያ ባለሥልጣናት ኤርትራ የሶማሊያዉን አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብን ታስታጥቃለች ብለዉ እንደሚጠረጥሩ ካስታወቁ ወዲሕ ግን በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ላይ የሚደረገዉ ግፊት ጠንከር ብሏል።
ምክር ቤቱ ሥለሁለተኛዉ ማዕቀብ የቀረበዉን ሐሳብ ከዚሕ ቀደም ሁለቴ ተነጋግሮበታል።ድምፅ ከሚሰጥበት ደረጃ ግን አልደረሰም።አሁንም ግፊቱ ማየሉ እንጂ ጉዳዩን አንስቶ የሚነጋገርበትም ሆነ ድምፅ የሚሰጥበትን ቀን አልቆረጠም።የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ ጃክ ዊሊያምስ እንደሚሉት ግን ምክር ቤቱ ፈጠነም ዘገየ በኤርትራ ላይ ሁለተኛ ማዕቀብ ከመጣል የሚመለስ አይመስልም።
«እንደሚመስለኝ ማዕቀቡ ይጣላል።የሶማሊያ ጉዳይ ተከታታይ ቡድን በቅርቡ ያወጣዉ ዘገባ ኤርትራ የምክር ቤቱን ዉሳኔ ጥሳ ሶማሊያ ዉስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ቡድናት የጦር መሳሪያ እንደምታቀብል በተገቢ ሁኔታ ግልፅ አድርጓል።»
ለአሸባብ ጭምር ማለትዎ ነዉ?
«ለአሸባብ ጭምር።»
ኤርትራ ለአሸባብም ሆነ ለሌቹ የሶማሊያ ታጣቂ ሐይላት የጦር መሳሪያ ታቀብላለች የሚለዉን ዘገባና ወቀሳ የኤርትራ መንግሥት ጨርሶ አይቀበለዉም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በተለይ ከኤርትራ የረጅም ጊዜ ጠላት ከኢትዮጵያ የሚደርሰዉን ጥቆማና መረጃ እንዳይቀበል ኤርትራ በተደጋጋሚ ጠይቃለች።የፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ትናንት እንደዘገበዉ ደግሞ የፅጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ሥለሚጣለዉ ማዕቀብ በሚያደርገዉ ዉይይት ላይ ፕሬዝዳት ኢሳያስ አፈወርቂ ራሳቸዉ እንገኙ ምክር ቤቱን ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳት ኢሳያስ በአካል ተገኝተዉ የመንግሥታቸዉን አቋም እንዲገልፁ አቀረቡት ለተባለዉ ጥያቄ እስካሁን በይፋ የተሰጣቸዉ መልስ ሥለመኖር አለመኖሩ የተዘገበ ነገር የለም።የኤርትራ ባለሥልጣናት ሥለ ጉዳዩ እንዲያስረዱን ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረም አልተሳካልንም።አዣንስ ፍራንስ ፕረስ የጠቀሳቸዉ የዓለም አቀፉ ድርጅት ዲፕሎማቶች ግን የኤርትራዉን ፕሬዝዳት ጥያቄን የተቀበሉት አይመስልም።
ምክንያቱም ለኤርትራዉ ፕሬዝዳት ከተፈቀደ ሌሎች ለምሳሌ የኢትዮጵያ መሪዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ካቀረቡ ሊፈቀድላቸዉ ይገባል ባዮች ናቸዉ።የፖለቲካ አዋቂ ጃክ ዊልያምስ እንደሚሉት ፕሬዝዳት ኢሳያስ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉይይት ላይ ተገኙም አልተገኙ በምክር ቤቱ ዉሳኔ ላይ የሚያመጣዉ ለዉጥ የለም።ማዕቀቡ ከተጣለ ግን ኤትርትራን ክፉኛ ይጎዳል።
«የማዉቀዉ ማዕቀቡ እንደሚባለዉ ማለት በማዕድናት መስክ የሚደረግ የምጣኔ ሐብት ትብብርን የሚያግድ ነዉ።ይሕ ቆንጣጭ ነዉ-የሚሆን።ኤርትራ ዉስጥ የካናዳ ኩባንዮች የሚያወጡት የወርቅ ማዕድን ለሐገሪቱ ከቀሯት ጥቂት የገቢ ምንጮች አንዱ ነዉ።»
በዚሕም ምክንያት አንዳድ ምዕራባዉያን መንግሥታት ሁለተኛዉ ማዕቀብ ከኤርት መንግሥት ይልቅ ወትሮም ከችግር ያልተላቀቀዉን የሐገሪቱን ሠላማዊ ሕዝብ ይጎዳል በማለት ማዕቀቡ ይጣል የሚለዉን ሐሳብ ብዙ አልደገፈቱም።ዩናይትድ ስቴትስ ግን ኤርትራ በቅጡ መቀጣት አለባት ባይ ናት። ኢትዮጵያም ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ኢርትራን ለማስቀጣት ከኢጋድ አባል ሐገራት ሁሉ ብዙ ርቃ ግፊት እያደረገች ነዉ።
አሁን ደግሞ ኬንያ ከዩናይትድ ስቴትስና ከኢትዮጵያ ጎራ የተቀየጠች መስላለች።የፖለቲካ አዋቂ ጃክ ዊሊያምስ እንደሚሉት ግን የኬንያና የኢትዮጵያ አለማ የተለያየ ነዉ።
«የሶማሊያዉ የርስ በርስ ጦርነት ወደ ኬንያም ተዛምቷል።ኬንያን የሚያሰጋት ይሕ ነዉ።በሌላ በኩል ኬንያ ራስዋን ሶማሊያ ዉስጥ ከትታለች።ይሕም እስካሁን ጥሩ ዉጤት ያመጣ ወይም የተሳከ አይመስልም።የኢትዮጵያ አላማ ግን እንደሚመስለኝ ከዚሕ የተለየ ነዉ።ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር እስካሁን ያላለቀ ጉዳይ አላት።የድንበር ጦርነት።ከሶማሊያ ጋር የሚገናኝ ምንም ነገር ሲከሰት የትኩረት አቅጣጫን ሥለሚቀይረዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ይሕን ይፈልገዋል።ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ግዴታዉን እንዳልተወጣ መዘንጋት የለብንም።»
የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ከሁለት ዓመት በፊት በኤርትራ ላይ የጣለዉ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብና የባለሥልጣናቷ የመዘዋወር እገዳ እስካሁን ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ አልሆነም።
ነጋሸ መሐመድ
አርያም ተክሌ