1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሌ ክልል መንግሥት እርምጃ ሥራ ያስቆማቸው ጋዜጠኞች

ቅዳሜ፣ የካቲት 18 2015

የሶማሌ ክልል በመገናኛ ብዙኃን እና ወኪሎቻቸው ላይ የወሰደው እርምጃ ቅሬታ እየቀረበበት ነው። የክልሉ መንግሥት ውሳኔ ከሚመለከታቸው አንዱ ሆነው ጋዜጠኛ ኢስማኤል ኢብራሒም "በክልሉ መስራት አቁመናል፣ አንዳንዶቻችን ወደ ኢትዮጵያ ሚዲያ ባለስልጣን በመምጣት ፍቃድ ለማደስ እየሞከርን እናገኛለን" ሲል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

Logo des Commitee to protect Journalists / CPJ

የሶማሌ ክልል መንግሥት እርምጃ ሥራ ያስቆማቸው ጋዜጠኞች

This browser does not support the audio element.

የሶማሌ ክልል "ፈቃድ የላቸውም " በሚል ከስራ ባስቆማቸው አስራ አምስት ያህል የሚዲያ ተቋማትና ወኪሎች እንዲሁም የክልሉን ጋዜጠኞች ማህበር ፍቃድያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሰረዙ የተለያየ ቅሬታ እየቀረበበት ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ በሚዲያ ተቋማቱ ሲሰሩ የቆዩ ወኪሎች የዘገባ ስራቸውን እንዳቆሙ መሆናቸውን ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል።

አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት በምዕፃሩ ሲፒጄ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫው ባለስልጣናት በቅርቡ እገዳ የተጣለባቸው የዜና ማሰራጫዎች ፣ የፕሬስ አባላት እና የጋዜጠኞች ማህበር በነጻነት እንዲሰሩ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝቧል።

በቅርቡ የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ "ፈቃድ የላቸውም" በሚል በክልሉ የዘገባ ስራ እንዳይሰሩ ካገዳቸው የሚዲያ ተቋማት አንዱ በሆነው የቢቢሲ ሶማልኛ ቋንቋ አገልግሎት ወኪል ሆኖ ሲሰራ የቆየው ጋዜጠኛ ኢስማኤል ኢብራሒም ስራ እንዳቆመ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

"በክልሉ መስራት አቁመናል፣ አንዳንዶቻችን ወደ ኢትዮጵያ ሚዲያ ባለስልጣን በመምጣት ፍቃድ ለማደስ እየሞከርን እናገኛለን። የሶማሌ ክልል ሚዲያ ጋዜጠኞች ማህበር የሚል ማህበር አለን የእርሱም ፍቃድ ያለ ምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ፈቃዱ ተሰርዟል። ማንም መጥቶ ያነጋገረን የለም"

በክልሉ በነፃነት ስራን በመስራት ረገድ ችግሮች እንዳሉ ያነሳው ኢስማኤል ለግዜውም ቢሆን ስራ ማቆሙን ምርጫ ማድረጉን ገልጿል።

"ቢቢሲን ወክዬ መናገር አልችልም አቋርጠዋል በእነሱ በኩል እስካሁን እያደረጉ ያሉትን ነገር አላውቅም።በእኔ በኩል ግን ስራዬን ለጊዜውም ቢሆን ለመተው እቅድ አለኝ ምክንያቱም ሁኔታውን እገነዘባለሁ ። የክልሉን መንግስት ሊያበሳጩ ይችላሉ የሚባሉ አንዳንድ ሪፖርቶችን ሰርቻለሁና።"

በክልሉ የሚገኙ ጋዜጠኞችን በስሩ አቅፎ ሲንቀሳቀስ የቆየው እና በቅርቡ ፈቃዱ የተሰረዘው የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር አብዱራዛቅ ሀሰን "ወሳኔው ትክክል አይደለም" ብሏል።

አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት በምዕፃሩ ሲፒጄ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ባለስልጣናት በቅርቡ እገዳ የተጣለባቸው የዜና ማሰራጫዎች ፣ የፕሬስ አባላት እና ፈቃዱ የተሰረዘበት የጋዜጠኞች ማህበር በነጻነት እንዲሰሩ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝቧል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚዲያ ማኅበር ላይ የተካሄደው ስረዛ እና 15 በሚሆኑ የመገናኛ ብዙኃን እና ወኪሎች ላይ የተደረገው እገዳ በክልሉ የሚከናወን የሚዲያ ዘገባ ስራ ላይ ያለውን አኩታዉ ጎን የጠቀሰው ማህበሩ

"የፈቃድ አሰጣጥ ደንቦች ማስከበር ጉዳይ የመገናኛ ብዙሃንን ለማፈን ጥቅም ላይ እንዳይውል ያለው ማህበሩ ባለስልጣናት በታገዱት የዜና ማሰራጫዎች የነበሩ ጋዜጠኞች ስራቸውን እንዲቀጥሉ መፍቀድ አለባቸው "ብሏል።

ይሁን እንጂ በፈቃድ ሳቢያ እገዳ የተጣለባቸው የሚዲያ ተቋማት እና ወኪሎች አሁንም ስራቸው እንደቆመ ነው። ቀጣዩን እጣ ፈንታ በተመለከተ ከክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን መ/ቤት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በኃላፊዎች የእጅግ ስልክ ብንደውልም ባለመነሳቱ ምላሻቸውን በዚህ ዘገባ ማካተት አልቻንም።

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW