1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሌ ፖለቲከኞች ዉዝግብ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 16 2011

ኬንያ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ሕንድ ውቅያኖስ ጥግ በሚገኝ ግዛት ሰበብ ከሶማሊያ ጋር እንደተወዛገበች ነዉ።የሶማሊያ መዳከም፤የኬንያ ጦር ደቡብ ሶማሊያን እንዲቆጣጠር ኃያሉ ዓለምም፤አፍሪቃም፤ እነኢትዮጵያም መፍቀዳቸዉ ለናይሮቢዎች በብር ሳሕን የቀረበ «ሥጦታ» ነበር።

Somalia kenianische Soldaten der Afrikanischen Union
ምስል Getty Images/AFP/AU-UN Ist Photo/S. Price

የጁባላንድ ምርጫና የሶማሊያ ፖለቲከኞች ዉዝግብ

This browser does not support the audio element.

ጁባላንድ የተባለዉ የደቡብ ሶማሊያ ራስ ገዝ ግዛት ባለስልጣናት  እና የሶማሊያ ፌደራል መንግስት መሪዎች ዛሬ በተደረገዉ የግዛቲቱ ፕሬዝደንት ምርጫ ሰበብ እየተወዛገቡ ነዉ።የጁባላንድ መሪዎች የፌደራሉ መንግስት ኃይል ወደ ግዛታቸዉ እንዳይገባ፣ የግዛቲቱን መንገዶች፣የባሕርና የአየር ወደቦችን ካለፈዉ ሰኞ ጀምሮ ዘግተዋል።የፌደራሉ መንግስት ምርጫዉን አልተቀበለዉም።ለተጨማሪ ዘመነ-ሥልጣን  መመረጣቸዉ የተነገረዉ የግዛቲቱ ፕሬዝደንት አሕመድ መሐመድ መዶቤና ተከታዮቻቸዉ ኢትዮጵያንም የፌደራሉን መንግስት ደግፋ ጣልቃ ትገባለች በማለት ይወቅሳሉ።ኬንያ ባንፃሩ መዶቤን ደግፋ የምርጫዉን ሒደትና ዉጤት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲቀበለዉ ጠይቃለች።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አለዉ።
የቀድሞዉ የደቡብ ሶማሊያ የጦር አበጋዝ አሕመድ መሐመድ መዶቤ እና የሶማሊያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ሐሰን ዓሊ ኸይሬ አማቾች ናቸዉ።ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ (ፎርማጆ) እና ኸይሬ ደግሞ ከአለቃና የበታችነት በተጨማሪ ጥብቅ ወዳጆች ናቸዉ።
በኸይሬ በኩል መዶቤን የተዋወቁት ፕሬዝደንት መሐመድ በ2017 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሥልጣን እንደያዙ የጁባላንድን ገዢነት ለመዶቤ መርቀዉላቸዉ ከጠቅላይ ሚንስራቸዉ አማች ጋር ተወዳጅተዉ ነበር።

«በዚሕ ምክንያት» ይላል ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ መሐመድ ሁሴይን ዑመር (ሽኔ-በቅፅሉ) የፌደራል መንግስቱና የጁባላንድ ወዳጅነት ጠንካራ ነበር።
                               
«በማዕከላዊዉi የሶማሊያ መንግስትና በዚያች አካባቢያዊ መስተዳድር መካከል ጠንካራ ግንኙነት ነበር።»
ኋላ ግን ነገር ተበላሸ።በርግጥ የተበላሻዉ ድሮ ነበር።በ2006 ማብቂያ።የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ወደ ሶማሊያ እንዲዘምት ሲወሰን፣ ጦር የሚያዘምቱ ሐገራት ባንድ ወይም በሌላ በኩል ሶማሊያ ዉስጥ ጥቅም፣ ወይም ከሶማሊያ ጋር ጠብ፣ቂም-ቁርሾ የሌላቸዉ መሆን አለባቸዉ ተብሎ ነበር።የተባለ የሚደረግ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያና ኬንያ ጦር ማዝመት አልነበረባቸዉም።
ኢትዮጵያ  የሶማሊያ የሸርዓ ፍርድ ቤቶች ሕብረት የተባለዉን መንግሥት እንዲወጋ ካዘመተችዉ ጦር ከፊሉን እዚያዉ እንዳሰፈረች ስትቀጥል፣ ኬንያ ደግሞ አሸባብን ለመዉጋት በ2011 ማብቂያ ጦር አዘመተች።
ኬንያ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ሕንድ ውቅያኖስ ጥግ በሚገኝ ግዛት ሰበብ ከሶማሊያ ጋር እንደተወዛገበች ነዉ።የሶማሊያ መዳከም፤የኬንያ ጦር ደቡብ ሶማሊያን እንዲቆጣጠር ኃያሉ ዓለምም፤አፍሪቃም፤ እነኢትዮጵያም መፍቀዳቸዉ ለናይሮቢዎች በብር ሳሕን የቀረበ «ሥጦታ» ነበር።
ስልታዊቱን፣ የወደብ ከተማ ኪስማዩን ጨምሮ ደቡብ ሶማሊያን የሚቆጣጠረዉ የኬንያ ጦር አዛዦች ከአሕመድ መሐመድ መዶቤ ጋር በ2013 የጀመሩት ወዳጅነት አድጎ፣ የመዶቤና የፕሬዝደንት ኡኹሩ ኬንያታ ሆነ።
                                 
«አሕመድ መዶቤ፣የኬንያዉ የኡኹሩ ኬንያታ የቅርብ ወዳጅ ናቸዉ።የሶማሊያ መንግስት ደግሞ ይሕን አይፈልገዉም።እንደምናዉቀዉ ከጥቂት አመታት በፊት መዶቤን የሚቃወሙ የጁባላንድ ፖለቲከኞች  ሌላ ምክር ቤት (ፓርላማ) መርጠዉ ነበር።አሁንም ድረስ ሁለት ምክር ቤትና ሁለት አፈ-ጉባኤዎች ናቸዉ ያሉት።»
የመዶቤና የኬንያታ መፈላለግ ሲጠብቅ የመዶቤና የሞቃዲሾ አለቆቻቸዉ ወዳጅነት ፈረሰ።የናይሮቢና የሞቃዲሾ ግንኙነትም ሻከረ።የዛሬዉ  ምርጫ እንዳይደረግ የሶማሊያ መንግስት የሰጠዉን ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ የመዶቤ ተከታዮች  ከቁብ አልቆጠሩትም።ከሶማሊያ መንግስት አልፈዉ መንግስትን ትደግፋለች የሚሏትን ኢትዮጵያን እየወቀሱ ነዉ።መሐመድ ዑመር ሁሴይን ግን የጁባላንዶችን ወቀሳ «ሐሰት»፣ የኬንያዎችን ጣልቃገብነት ግን እዉነት ይለዋል።
                                  
«በተጨባጭ ያለዉ እዉነት፣ኢትዮጵያ በምርጫዉ በየትኛዉም መንገድ ጣልቃ መግባቷን አያመለክትም።ኬንያ ግን በቀጥታ ጣልቃ ገብታለች።ምክንያቱም የኬንያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ትናንት አሕመድ መዶቤን በመደገፍ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደብዳቤ ፅፈዋል።ሚንስሯ የጁባላንዱ ምርጫ ማንንም እንደማያሰጋና መሰረዝ እንደሌለበትም ጠይቀዋል።»
የጁባላንድና የፌደራል መንግስቱ ፖለቲከኞች ፍጥጫ ከቀጠለ የሶማሊያን ግጭት ብጥብጥ ለማቀጣጠል ሌላ ቤንዚን መሆኑ አይቀርም።

ምስል picture-alliance/dpa

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW