1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ ወዳጆች ጉባኤ በኢስታንቡል

ሰኞ፣ መጋቢት 24 2004

የሶሪያ ወዳጆች ዓለምአቀፍ አገናኝ ቡድን ትናንት በቱርክ- መዲና ኢስታምቡል ለሶሪያ ችግር መፍትሄ ሲሻ ውሏል። ቱርክ የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ለተባባሰዉ የሶርያ ግጭት አንዳች ዉሳኔ ካላሳለፈ የሶርያ ህዝብ ራሱን ሊከላከል ይገደዳል ስትል፤

Turkey's Prime Minister Tayyip Erdogan (R) meets with members of the opposition Syrian National Council (SNC) in Istanbul March 31, 2012. REUTERS/Murad Sezer (TURKEY - Tags: POLITICS)
የሶሪያ ወዳጆች ጉባኤ በኢስታንቡልምስል Reuters

የሶሪያ ወዳጆች ዓለምአቀፍ አገናኝ ቡድን ትናንት በቱርክ- መዲና ኢስታምቡል ለሶሪያ ችግር መፍትሄ ሲሻ ውሏል።  ቱርክ የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ለተባባሰዉ የሶርያ ግጭት አንዳች ዉሳኔ ካላሳለፈ የሶርያ ህዝብ ራሱን ሊከላከል ይገደዳል ስትል፤

የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ጀርመን የሶሪያን ቀዉስ ለመፍታት የፖለቲካ መፍትሄ እንዲፈለግ እንደምትመርጥ ለጉባኤዉ አመልክተዋል።

ከትናንቱ የኢስታምቡል የሶሪያ ወዳጆች ዓለምአቀፍ ጉባኤ መገንዘብ የሚቻል ሁለት ነጥቦች አሉ።  በመጀመሪያ ለሶሪያ ዓመጽ በዲሞክራሲያዊ መልኩ መፍትሄ የማግኘቱ ሁኔታ እየቀነሰ መሆኑንን እና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አንዳንድ አገሮች ጠቀም ያለ ገንዘብ በማሰባሰብ የሶሪያ መንግስት ተቃዋሚያንን መርዳት እንደሚፈልጉ ነው።  የባህረ ሰላጤ አካባቢ የሚገኙ አገራት ማለትም እንደ ሳውድ አረቢያ፣ ካታር እና የተባበሩት የአረብ ኢሚራቶች በ200 ሚሊዮን ዶላር የሶሪያ መንግስት ተቃዋሚዎችን ለመደገፍ አስበዋል። ገንዘቡም  ከሶርያ መንግስት ጦር ከድተዉ በተቃውሞ ወገን ለተሰለፉ ወታደሮች ደሞዝ መክፈልን ጨምሮ ሥራ ላይ እንዲዉል የታሰበ ነዉ። ጉባኤው ላይ የተገኙ የሶርያ ብሄራዊ ምክር ቤት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን በግልፅ ገንዘቡ የጦር መሳሪያ ሊገዛበት እንደሚችል ሲናገሩ ተደምጧል።

ሶርያ ዉስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ መባባሱ ትዕግስቷን እንደጨረሰዉ ያመላከተችዉ የጉባኤዉ አስተናጋጅ ሀገር-ቱርክ ደግሞ ሩሲያና ቻይናን ጨምሮ የተመ የፀጥታዉ ምክር ቤት  ይህን ቀዉስ ለመግታት ርምጃ የማይወስድ ከሆነ የሶርያ ህዝብ ራሱን ለመከላከል ይገደዳል ስልት ተደምጣለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ሬቼፕ-ታይፕ-ኤርዶሃን በጉባኤው ማጠቃለያ «የሶሪያ ሁኔታ ክፉኛ አሳሳቢ ነው፤ የዘር ጭፍጨፋው እና ግድያው እንዲያበቃ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን»ነዉ ያሉት። አክለውም ፤ « ዛሬ 83 አገሮች እና አለም አቀፍ ድርጅቶች -ሌሎች አገሮች ለሰው ልጅ ክብር እንደሚታገሉት ሁሉ- የሶሪያ ህዝብን ፍላጎት እና ጥያቄ ደግፈዋል።»

ምስል Reuters

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ፤ ሶርያ ዉስጥ የመንግስት ኃይሎች የሚወስዱት የኃይል ርምጃ መባባሱን ቢጠቁሙም ሀገራቸዉ ከምንም በላይ ለሶርያ ቀዉስ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈለግ እንደምትመርጥ ነዉ ያመለከቱት።

«ሶሪያ ዉስጥ የሚወሰደዉ የኃይል ርምጃ ሊታገሱት ከማይቻልበት ሁኔታ ላይ ነዉ። ይህ የኃይል ርምጃ እንዲቆም ሁላችንም በጋራ ሆነን መስራት አለብን። ለዚህ ሁላ ጥቃት አንድ ተጠያቂው ነው ያለው። ይኸውም የአሳድ አገዛዝ ነው። የተባበሩት መንግስታትም ሆኑ የአረብ ሊጉ፤ ኮፊ አናንን የሶሪያው ልዩ መልዕክተኛ አድርገው መርጠው ፖለቲካዊ መፍትሄ መፈለጋቸው ትክክል ነው። እኛ ጀርመኖች የምንፈልገዉና የምንደግፈዉ ፖለቲካዉ መፍትሄ ነዉ፤ ስለዚህም የኮፊ  አናን ባለስድስት ነጥብ መርሃ ግብር ድጋሚ እድል እንዲሰጠዉ እንሻለን።»

ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ የሶርያ መንግስት ተቃዋሚ ኃይሎችን በዘመናዊ የመገናኛ መሣሪያዎች ለመርዳት ፍላጎቷን ኢስታንቡል ላይ አመላክታለች።  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂለሪ ክሊንተን  የሶሪያ  መንግስት ከእንግዲህ በአማፂያኑ እና በመንግስት ተቃዋሚያን ላይ ጥቃት የሚያደርስ ከሆነ መንግስቱ ላይ ከፍትኛ ርምጃም ሊጣል እንደሚችል  አስጠንቅቀዋል።

ምስል AP

« ኮፊ አናን ይህን ቀዉስ እንድንፈታ መርሃ ግብር ሰጥተውናል። ባሸር-አል-አሣድ የእሳቸዉን ተማፅኖ ለመቀበል እስካሁን አሻፈረኝ ብለዋል።  ምክንያት ለመስጠት ወይም  ለማጓተት ምንም ጊዜ የለም።  ጊዜው የእውነታ ነው። »ስለሆነም በሶሪያ መንግስት ላይ ለሚደረገው ርምጃ የሚቀጥሉት ሳምንታት ወሳኝ ናቸው። የሶሪያ ወዳጆች ጉባኤ  ፈረንሳይ - ፓሪስ ዉስጥ  በቅርቡ በቀጣይ  ይካሄዳል። ቢያንስ በፓሪሱ ጉባኤ በተግባር የሚዉል ውሳኔ ላይ መደረስ እንደሚገባል አንድ የሶሪያ ተቃዋሚ ቡድን ተወካይ ጠይቀዋል። ሌሎች የሶሪያ የተቃዋሚ ቡድን ተወካዮችም በበኩላቸዉ የምዕራቡ አገሮች የሶርያን ቀዉስ ለማብቃት የአየር ጥቃት ማድረጋቸዉ አስፈላጊ እንደሚሆን ለጉባኤው  ተናግረዋል። ከትናንቱ የሶሪያ ወዳጆች ጉባኤ በኋላ የሶሪያ ጉዳይ ይበለጥ የተጧጧፈ መስሏል።

ልደት አበበ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW