1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶስቱ ኃያላን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ጉብኝት በኢትዮጵያ

ቅዳሜ፣ ጥር 6 2015

ሚንስትሮቹ በጉብኝታቸው ወቅት የህብረቱን አንድ አቋም ግልጽ አድርገዋል። « በኢትዮጵያ ያለ ፍትህ እርቅ አይኖርም» ። አዲሱ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግም እንደቀደሙቱ ቻይናውያን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ሁሉ ስልጣናቸውን አፍሪቃን በመጎብኘት ለመጀመር ባለፈው ማክሰኞ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘዋል።

Äthiopien Annalena Baerbock zu Besuch
ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

ቻይና ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ አዲስ አበባ የመገኘታቸው አንድምታ

This browser does not support the audio element.

የሰሜን ኢትዮጵያው ደም አፋሳሽ ጦርነት ካበቃ በኋላ የአውሮጳ ሁለቱ ኃያላን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የጀርመኗ  አናሌና ቤርቦክና የፈረንሳይዋ አቻቸዉ ካተሪነ ኮሎና ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሐሙስ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘዋል። ሚንስትሮቹ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረዋል።  ሚንስትሮቹ በጉብኝታቸው ወቅት የህብረቱን አንድ አቋም ግልጽ አድርገዋል። « በኢትዮጵያ ያለ ፍትህ እርቅ ሊኖር አይችልም» ። አዲሱ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግም እንደቀደሙቱ ቻይናውያን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ሁሉ ስልጣናቸውን አፍሪቃን በመጎብኘት ለመጀመር ባለፈው ማክሰኞ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘዋል። ጤና ይስጥልን የተከበራችሁ የዝግጅታችን ተከታታዮች የምዕራቡ እና ምስራቁ ኃያላን ጉምቱ ባለስልጣናት በሁለት ቀናት ልዩነት አዲስ አበባ መገኘታቸው የዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዐቢይ ጉዳያችን ነው ፤ መልካም ቆይታ

አይገመቴ እና ብርቱ ሰብአዊ ብሎም ቁሳዊ ውድመት ያስከተለው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም በዓለማችን የቅርብ ዓመታት ታሪክ አስከፊው ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። ከትግራይ ጀምሮ በኋላም ወደ አማራ እና የአፋር ክልሎች በተዛመተው ጦርነቱ በትክክል ምን ያህል ሰው እንዳለቀበት መተንበይ አስቸጋሪ ነው።  ነገር ግን በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደቆየው በጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳያልቁበት እንደማይቀር ነው። ይህ ብቻ አይደለም ከእልቂቱ ባልተናነሰ  አካላዊ ፣ ስነልቦናዊ እና ማህበራዊ መስተጋብሩን ያጠለሸው እና በከፋ ጥላቻ ላይ የተመሰረተው ሁነት ሊሽር ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ ማንም አስቀድሞ መተንበይ አይቻለውም ። ቁሳዊ ውድመቱ ደግሞ በራሱ ሌላ ታሪክ ነው ። ለወትሮም የአበዳሪ ሀገራት የዕዳ ጫና ትከሻዋን ላጎበጠባት ሀገር በጦርነቱ የወደመውን መሰረተ ልማት ለመጠገን ብሎም ወደ ነበረበት ለመመለስ ምን ያህል ገንዘብ እና ጊዜ እንደሚወስድባት ለማወቅ ጊዜው ገና ነው።

በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመጠገን የጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን ቀደም ሲል እስከ 20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጸው ነበር።የአውሮጳ ኅብረት የሰብአዊ ጉዳዮች ልዑክ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

ነገር ግን ዘግይተው የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር ተወያይቶ የደረሰበት እና ለውድመቱ መልሶ ግንባታ  ከ28 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማስፈለጉን ነው። ይህ አሃዝ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ቀድሞውኑ በዕዳ ጫና ውስጥ ላሉ ሃገራት የማይታሰብ ነው።

የሆኖ ሆኖ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እየተካሄደ በነበረባቸው ሁለቱ ዓመታት ከኢትዮጵያ ጎን እና በተቃራኒው የቆሙ የምስራቁ እና የምዕራቡ ኃያላን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ሰሞኑን ወደ አዲስ  አበባ የመጓዛቸው አንድምታ ማነጋገሩ አልቀረም። አዲስ አበባ አንድም ሁለትም ናት ። አንድም የኢትዮጵያ መዲና ሁለትም የአፍሪቃ ህብረት መቀመጫ እና የአህጉሪቱ መግቢያ በር። በሩ ለሁለቱም ጎራ ተከፍቷል። በእርግጥ ነው ምርጫ የለውም ።

ባለፈው ሐሙስ ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክና የፈረንሳይዋ አቻቸዉ ካተሪነ ኮሎና ጠቅላይ ሚስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረዋል።

የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚስትር አናሌና ቤርቦክ ጉብኝታቸውን አስመልክተው በጋራ መግለጫው ላይ ካነሱት ሃሳብ እንዲህ ብለዋል።

« በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ ይህንን ጉብኝት ለማድረግ ስናቅድ የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም የደረሰበትን ለመመልከት እና ለማበረታታት ፣እንዲሁም ሁለተኛው ወሳኝ  የሆነው የሰብአዊ ረድኤት ተደራሽነት ጉዳይ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የተጠያቂነት ጉዳይ ዋና ትኩረታችን ሆነው ነው ጉብኝታችንን ከመዲናዬቱ የጀመርነው »

"እኛ ጀርመኖች እና ፈረንሳዮች » አሉ ባርቦክ «በአንድ ጀንበር እርቅ እንደማይሆን ከራሳችን ልምድ እናውቃለን። ነገር ግን  ለተጎጂዎች ፍትህ እስካልተረጋገጠ ድረስ እርቅ እና ዘላቂ ሰላም መፍጠር አይቻልም » በማለት ነበር ሀገራቸው በጦርነቱ ውስጥ ብርቱ የሰብአዊ መብት ጥሰ,ት በፈጸሙት ላይ ተጠያቂነት እንደረጋገጥ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

የፈረንሳይዋ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኮሎና በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ «እያሳየ ያለውን መሻሻል እና ቀጣይነት » በደስታ እንደሚቀበሉ ነው የተናገሩት።

ሁለቱም እንስት  የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በዚህ ጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተናጥልም ሆነ እንደ ህብረት መልሶ ለማጠናከር ይቻል ዘንድ አጽንዖት የሰጡበት አንድ መሰረታዊ ጉዳይ አለ።በኢትዮጵያ ጉዳይ የአውሮጳ ሕብረት መወያየቱ

በጦርነቱ ወቅቱ  ጭካኔ የተሞላባቸውን  ግፎች የፈጸሙት የእጃቸውን ያገኙ ዘንድ «የሽግግር ፍትህ ይቋቋም » ዘንድ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው በጉብኝቱ ማጠቃለያ የጋራ መግለጫ ወቅት ታሪካዊ ባሉት የኢትዮጵያ እና የሁለቱን አውሮጳውያን ሃገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ዕድል መፍጠሩን ነው  የጠቀሱት።

የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች አዳማ የሚገኘውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም መጋዘን ሲጎበኙምስል Florian Gaertner/photothek/picture alliance

« ከሁለቱም ሀገሮች ጋር ታሪካዊ እና የቅርብ ወዳጅነት አለን። ይኽ ጉብኝት ግንኙነታችንን ይበልጥ ለማጠናከር ዕድል ይሰጠናል። በዚህ ወቅት በወቅታዊ ጉዳዮች በቀጠናዊ እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር መክረናል። በሀገራችን ስላለው የሰላም የዴሞክራሲ እና የልማት ሁኔታ እንዲሁም ስለ አካባቢያችንም መክረናል። በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ወደ አፈጻጸም ገብቶ በጥሩ ሁኔታ እየቀጠለ እንደሆነ ይህም በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር በትኩረት እንደሚሰራ የመንግስትን ቁርጠንነት አረጋግጠንላቸዋል። » ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ ዓሕመድም ቢሆኑ  ሚንስትሮቹን ካነጋገሩ በኋላ ቀደም ሲል  በትዊተር ገፃቸዉ ባሰራጩት አጭር መልዕክት ኢትዮጵያ ከጀርመንና ከፈረንሳይ ጋር ያላትን «ጠንካራ ግንኙነት» የሚያንፀባርቅ ነዉ ብለዋል።

የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክ  ቀደም ሲል ጉዟቸውን በተመለከተ በትዊተር ባጋሩት አጭር መልዕክት  «በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም በሚመጣበት ፣ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ማገዝ በሚችሉበት ሁኔታ ፣ እንዲሁም በአፍሪቃ ቀንድ የምግብ ዋስትና ላይ ለመምከር እና የአውሮጳ ህብረት ከአፍሪቃ ህብረት ጋር ያለውን አጋርነት ለማጠናከር ያለመ ነው ። » ብለው ነበር።

የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ከአፍሪቃ ህብረት ዋና ጸሐፊ ጋር ተነጋገሩምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

በእርግጥ ነው ቻይናን ጨምሮ የምስራቁ ክፍለዓለም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪቃ እያሳደሩት ባለው ተጽዕኖ ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮጳ ህብረት በተለይ ከሰብአዊ መብት ጥበቃ አንጻር የሚከተሉትን መሰረታዊ የተጠያቂነት መርህ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጸመው አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያረጋግጣሉ የሚለው ጥያቄ መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ጀርመን እና ፈረንሳይን ጨምሮ የአውሮጳ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል። ሀገራቱ ለኢትዮጵያ መንግስት ይሰጡ የነበረውን መልከ ብዙ የፋይናንስ ድጋፎችን አቋርጠው ቆይተዋል። ይህ በእርግጥ በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ላይ የከፋ የሚባል ተጽዕኖ ማሳደሩን በግልጽ አሳይቷል።

የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ተነጋገሩምስል Florian Gärtner/imago images/photothek

ሀገራቱ በተናጥል እንዲሁም ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራቸውን መጻኢ የሁለትዮሽ ግንኙነት መሰረቱ «ያለፍትህ እርቅ የለም» መርህ የተከተሉ ይመስላል። በጦርነቱ ወቅት በሁሉም ወገኖች ለተፈጸመ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነት እንዲኖር በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል። ጥያቄው በምን ያህል ጊዜ እና እንዴት ተፈጻሚ ይሆናል የሚለው  እንደተጠበቀ ሆኖ ። ነው ወይስ ቻይና እና ሌሎች ከምዕራባውያን በተቃራኒ የቆሙት ሀገራትን ለመገዳደር ሲባል በለዘበ መርህ የቀደመውን ሁለንተናዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማደስ ምርጫቸው ያደርጉ ይሆን ?የአውሮጳ ህብረትና የአፍሪቃ ህብረት አዲስ አጋርነት ተስፋ

ባለፈው ማክሰኞ አስቀድመው አዲስ አበባ የደረሱት አዲሱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግ ምንም እንኳ አምስት የአፍሪቃ ሃገራትን የመጎብኘት አላማ ይዘው ቢነሱም የጉብኝብኝታቸው መንደርደሪያ ኢትዮጵያ መሆኗ ሀገራቸው ከሁለትዮሽ ባሻገር ከአህጉራዊ ህብረቱ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ማሳለጫ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እና ከአፍሪቃ ህብረት ዋና ጸሐፊ ሙሳ መሀመት ፋኪ ጋር ተነጋግረዋል። ቺን ጋንግ ሀገራቸው  ለኢትዮጵያ የ30 ሚሊዮን ዩዋን የእዳ ስረዛ ማድረጓንም በአዲስ አበባ በነበራቸው ጊዜ ይፋ አድርገዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን የቻይናውን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግ ሲቀበሉምስል Fana Broadcasting Corporate

ምዕራባውያኑ በአንድ ወገን ፣ ቻይና ፤ ሩስያ እና ህንድ በሌላ ወገን ወዲህ ደግሞ ቱርክ በየፊናቸው በአፍሪቃ የፖለቲካ፣ ኤኮኖሚ እና ወታደራዊ ሚዛን ለመድፋት ደፋ ቀና በማለታቸው አፍሪቃ ይዞላት የሚመጣውን ገጸ በረከት በጥንቃቄ ከመቀበል ውጭ ለጊዜው ሚዛን የመድፋት ስራ ትሰራለች ተብሎ አይጠበቅም።

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግ በአዲስ አበባው ጉብኝታቸው አፍሪቃ የዓለም ሃያላን የውድድር ሜዳ መሆን የለባትም ሲሉ ተደምጠዋል። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ሃገራቸው ከአፍሪቃ ህብረት ጋር በትብብር አዲስ አበባ ውስጥ የገነባችውን የአፍሪቃ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ዋና መስሪያ ቤት ባስመረቁበት ወቅት «አፍሪቃ ለዓለም አቀፉ ትብብር ትልቅ መድረክ እንጂ የኃያላኑ መፎካከሪያ አውድማ መሆን የለባትም» ብለዋል።የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር በኢትዮጵያ

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ጋርምስል Fana Broadcasting Corporate

ቺን ጋንግ ከኢትዮጵያ በመቀጠል ሳምንት በሚወስደው የአፍሪቃ ጉብኝታቸው  ጋቦን ፤ አንጎላ ፣ ቤኒን እና ግብጽን ይጎበኛሉ። 

በእርግጥ ነው ፤ የቻይና አፍሪቃ ግንኙነት እጅጉን እያደገ መጥቷል። ከአፍሪቃ ጋር ሁነኛ የንግድ አጋር መሆኗንም  አስመስክራለች ። ከአፍሪቃ ጋር ያላት የንግድ ልውውጥ በሃያ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሃያ እጥፍ በላይ ማደጉ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው። በአህጉሪቱ በፋይናንስ አቅርቦት ፣ በመሰረተ ልማት እና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ውስጥ የላቀ ሚና እየወሰደች መምጣቷ ይነገራል። በአፍሪቃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሽን ባልደረባ ዶክተር ጌዲዮን ጃለታ እንደሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ጉብኝት ከዚሁ አንጻር የሚቃኝ መሆኑን ነው።

« ከ2015 ጀምሮ ቻይና 60 ቢሊዮን ዶላር ነው ለአፍሪቃ ሀገሮች ፈሰስ ያደረገችው።  ንግድን ለማስተዋወቅ፤ የኢንዱስትሪ መንደሮችን ለመገንባት ፤ የተለያዩ የግብርና ስራዎች ለማዘመን የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ለማሳደግ ማለት ነው። በመንገድ ፣ በባቡር መስመር ዝርጋታ እንደገና ደግሞ እንደምናውቀው የአዲስ አበባ ጂቢቲ የባቡር መስመር አለ ፤ እሱን እስከ ሴኔጋል ድረስ የመውሰድ ዕቅድ አለ፤ እና የቻያኖች በአፍሪቃ መገኘት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ  እና ዘርፉን እያሰፋ ነው ያለው ። »

በእርግጥ የቻይናውያኑ በአፍሪቃ ሚዛን ያዛባ የመሰለው የትብብር ግንኙነት ዳራ ምዕራባውያኑ ጉዳዩን በቸልታ እንዲያዩት አላደረገም ። ይልቁኑ  ከአፍሪቃ አንጻር ያላቸውን ግንኙነት መልሰው ለማጤን የተገደዱ ይመስላል። ይህ ብቻም አይደለም። ምዕራባውያኑ ከቻይና ኤኮኖሚያዊ ጫና ባሻገር የሩስያ እና ቱርክ ወታደራዊ የትብብር ግንኙነት በእርግጥ ያሳስባቸዋል።  የሩስያም ሆነ የቻይና ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ አፍሪቃ ለሚያደርጓቸው ይፋዊ ጉብኝቶች አጸፋ የመስጠታቸው እውነታ ከዚህ ስለመራቁ ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም።የዩናይትድ ስቴትስና የቻይና ሽሚያ

አንድ ነገር ግን ልብ ሊባል ይገባል ፤ ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ ተጎትታ መውጣት ከፍተኛ የመዋዕለ ንዋይ ድጋፍን ጨምሮ  ሌሎች በተሻሻሉ ዲፕሎማሲያዊ ግኙነቶች ውስጥ  ዘርፈብዙ ዓለማቀፍ ድጋፎች ትሻለች። በእርግጥ አ,ዲስ አበባ የሁለቱ ጎራ ማሻኮቻ ሜዳ ትሆን ወይስ ከራሷም አልፋ ለአህጉሪቱ ገጸ በረከት ትሆን ይሆን ፤ ለነገ እናቆየው ፤ እኔ ግን በዚህ ላብቃ ፤ ለአብሮነታችሁ ምስጋናችን ትልቅ ነው ። ጤና ይስጥልን።

ታምራት ዲንሳ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW