የሸማቹ ኑሮ እና የንግድ እንቅስቃሴው እንዴት ሆኖ ይሆን?
ማክሰኞ፣ ኅዳር 24 2017ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር «የምርት ነፃ ዝውውርን የሚገድቡ» ያላቸው 283 ሕገ ወጥ የከተማ በር ወይም መቅረጫ ኬላዎች በመላው ሀገሪቱ መኖራቸውን ገለፀ ። ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ እንዳሉት፦ ይህ ለምርቶች ዋጋ መጋነን እና የሸቀጦች ዋጋ መናር ምክንያት ሆኗል ። ሚኒስትሩ መሥሪያ ቤታቸው ባለፉት አምስት ወራት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የንግድ ተቋማት ላይ ርምጃ ተወስዷል ቢሉም ከምክር ቤት አባላት ርምጃ ለምን እንደተወሰደ፤ ያ በመሆኑ ምን ውጤት እንደተገኘ እንደማይገለጽ ተጠቅሶ ሚኒስቴሩ ከደላላ ዕጅ አስወጥቶ የሀገሪቱን ንግድ በአግባቡ እየመራ ስለመሆኑ ጥያቄ ተነስቶበታል ።
የሕዝብ ተወካዮች ስለ ንግድ ሥራዎች ምን አሉ?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዛሬ ማግሰኞ ለንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ማብራሪያ ከጠየቁባቸው ጉዳዮች መካከል የሕገ ወጥ ንግድ መሥፋፋት፣ በንግድ ፈቃድ ሥርዓት ውስጥ ያልገቡ ግን አብዛኛው ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሕዝብ የሚመርጣቸው መደበኛ ያልሆኑ የንግድ ግብይቶችን መስመር ከማስያዝ ይልቅ የማሳደድ ስልት ብቻ መኖሩ፣ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት መናርን የተመለከቱት ይገኙበታል። «ሕጋዊ ነጋዴ በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች እና በደላላ እየተጠለፈ መሥራት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ።»
መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ግብይት በገበያ እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ አገልግሎት ሰጪዎች የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ የክፍያ ጭማሪ አድርገዋል። የትራንስፖርት፣ የቴሌኮም፣ የመብራት አገልግሎቶች ላይ እንዲሁም የነዳጅ እና መሰል ሸቀጦች ላይም የዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል፥ የሀገር ውስጥ የግብርና ምርቱም በተመሳሳይ።
"ያለምንም ምክንያት በየጊዜው ዋጋ የሚጨመርባቸው እንደ ጤፍ፣ ፊኖ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት፣ ፓስታ፣ ማካሬኒ እና የመሳሰሉት የፍጆታ ዕቃዌች ላይ ነጋዴው ከመሬት ተነስቶ ዋጋ ሲጨምር ለምን ተብሎ ስለማይጠየቅ፣ እርምጃም ስለማይወሰድ ዋጋው እንደተሰቀለ ይቀራል ።"
የሕገ-ወጥ ቀረጥ እና መቅረጫ ቦታዎች - ኬላዎች መብዛት
የንግድ እና ቀጣናዊ ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ መሥሪያ ቤታቸው የትኞቹ የንግድ ተቋማት ላይ፣ ምን እንደተደረገ እና የተገኘውን ውጤት ባያብራሩትም በመቶ ሺህ የሚቆጠር የንግድ ተቋም ላይ እርምጃ ተወስዷል ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት ምላሽ ሰጥተዋል። የተወሰደው እርምጃ በተጨባጭ ለሸማቹም ሆነ ለግብር ሰብሳቢው መንግሥት የፈየደውን ግን አላብራሩትም። "ከ105 ሺህ በላይ ነጋዴ በላይ እርምጃ የተወሰደበት፣ እና ከ 1000 ሰው በላይ በእሥር የተቀጣበት" ነው ብለዋል።
የሀገሪቱ ንግድ በደላላ እየተመራ ነው በሚል የቀረበባቸውን ትችት ያጣጣሉት ሚኒስትሩ እውነታው በዚያ ደረጃ የሚገለጽ እንዳልሆነ፣ ሆኖም ግን የደላላ ጣልቃ ገብነት አሁንም የሚቀር እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። በየክልሉ በከተሞች መግቢያ እና መመውጫ በር ላይ ገመድ ወጥረው ነጋዴውን ለድርብርብ ክፍያ እና ወጪ የሚዳርጉ ሕገ-ወጥ አሠራሮች በቀላል የማይታይ አደጋ መደቀናቸውን ግን በዚሁ ጊዜ ጠቅሰዋል። "ኬላ ይነሳ ተብሎ በመንግሥት ደረጃ ቢወሰንም የተለያዩ ሰበባሰበቦች እየተፈለጉ 283 ሕገ ወጥ ኬላዎች በመላው ሀገሪቱ ተንሰራፍተው ይገኛሉ ።"
በምክር ቤት አባላቱ ያልተነሳው ጦርነት እና ግጭት በዘርፉ ላይ ያሳረፈው ተጽእኖ
መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ያላቸው ግለሰቦች ምርቶችን ከውጭ እንዲያስገቡ ሰጥቶት በነበረው የፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ ሸቀጥ ለማስገባት ዕድል የማስፋቱን ያህል የኢኮኖሚ ዘርፉንም የማናጋት አደጋ እንደደቀነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ ለአብነትም በሀገር ውስጥ የሚመረት የስኳር ምርት ዋጋ ከውጪ ከሚገባው በመብለጡ የሀገር ውስጥ አምራቾችን አደጋ ላይ ጥሏል። የቤንዚን ነዳጅ አንድም ሙሉ በሙሉ ከፖርት ሱዳን ቀርቶ በጅቡቲ ብቻ የሚገባ በመሆኑ፣ በሌላ በኩል ከገባ በኋላ በሌብነት የተሳሰረ በመሆኑ ያንን ለመከላከል መንግሥት የነዳጅ ኩባንያዎች ላይ መረር ያለ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ኢትዮጵያን ያደቀቀው ጦርነት እና አሁንም ክፉኛ ብርቱ ጉዳት እያደረሰ ያለው የትጥቅ ግጭት፣ የዜጎች በነፃነት ያለመንቀሳቀስ ፈተና በአጠቃላዩ የምጣኔ ሀብት እና የኑሮ ሁኔታ ላይ ስላሳረፈው ችግር ያቀረቡት ጥያቄ ባለመኖሩ ሚኒስትሩ በዚህ ዙሪያ የሰጡት ማብራሪያ የለም።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ