1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፓኖራማኢትዮጵያ

1000 ጥንዶች ጋብቻ የሚፈፅሙበት ሰርግ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ጥር 3 2016

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ የጥር ወር በርካታ ወጣት ጥንዶች ጋብቻ የሚመሰርቱበት ወር ነው። የዘንድሮውን ወር ለየት የሚያደርገው ደግሞ የፊታችን እሁድ 1000 ጥንዶች በአዲስ አበባ አብረው ጋብቻቸውን የሚፈፅሙበት መሆኑ ነው። የዝግጅቱ ዓላማ ወጪን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ከዛም በላይ ያለመ ነው።

ሙሽሮች
ኢትዮጵያ ውስጥ በ2005 ዓ.ም 500 ያህል ጥንዶች በአንድ ቀን በአንድ ቦታ የጋብቻ ስነ ሥርዓታቸውን ፈፅመዋል። ምስል Yament

1000 ጥንዶች ጋብቻ የሚፈፅሙበት ሰርግ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ውስጥ በ2005 ዓ.ም 500 ያህል ጥንዶች በአንድ ቀን በአንድ ቦታ የጋብቻ ስነ ሥርዓታቸውን ፈፅመዋል።  ዘንድሮ ደግሞ ይህ ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ 1000 ጥንዶች ወይም 2000 ተጋቢዎች ዕሁድ ጥር 5 ቀን፣ 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው የሚሊኒየም አዳራሽ ትዳራቸውን ይፈፅማሉ ተብሎ ይጠበቃል። «የሺ ጋብቻ ፕሮጀክት» የሚዲያ ኮሚኒኬሽን እና ስልጠና አማካሪ የሆነው እሸቱ ገለቱ በዘንድሮው ዝግጅት ስለታቀዱ ነገሮች ገልፆልናግል። « ጥር አምስት ቀን ጠዋት ላይ ልዩ የፎቶ ፕሮግራም ይኖራቸዋል። በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄደው ዝግጅት ላይ ባህላዊ እና ህብራዊ ቀለሙን ከመጠበቅ በተጓዳኝ በልዩ አይነት ሁኔታ 2000 ኪሎ ግራም የሚመዝን ዳቦ ይኖራል። » ይህም ብራዚል ላይ ከተመጠገበው 1500 ኪሎ ግራም ባዶ እንደሚበልጥ እና አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ሊሆን እንደሚችል እሸቱ ይናገራል። ሌላው ደግሞ በዚህ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር በጋራ ከ Yament ጋር ባዘጋጀው የሰርግ ሥነ ሥርዓት ላይ 1000 ቡና አፍዮች 1500 ሺ ስኒዎች ይዘው እንግዶችን የሚያስተናግዱ መሆኑ ነው።  እያንዳንዱ ጥንዶች ሶስት እንግዶችን እንዲጋብዙ የተፈቀደላቸው ሲሆን ሌሎች ቤተዘመዶች ግን በዝግጅቱ መታደም ከፈለጉ ቲኬት ገዝተው መግባት ግድ ይላቸዋል።

ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጡ ሙሽሮች

በዲላ ዩንቨርስቲ መምህር የሆኑት ተስፋዬ እና አስቴር ከእነዚህ ጥንዶች አንዱ ናቸው።  ሰርጋቸውን ለመፈፀም የተወሰኑ ቀናት ቀደም ብለው ከዲላ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘዋል። በዚህ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመሳተፍ የወሰኑት እነሱ እንደሚሉት እንደአጋጣሚ ነው። « ይህ ዝግጅት እንዳለ ስናቅ ትልቅ እድል ነው ብለን አሰብን » የሚለው ተስፋዬ « ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር አብሮ መሞሸር ትልቅ እድል ነው ብለን ወሰንን» ይላል። አስቴርም ብትሆን በጣም ደስተኛ ናት። « ኢትዮጵያ ልጆቿን ትድራለች ነው የሚለው እና በህይወታችን የማንረሳውን ታሪክ እንሰራለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።»
የሺ ጋብቻ ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚጓዙ ጥንዶች የሚሳተፉበት ይሆናል። ፍቅረኛዋ በአጋጣሚ ማስታወቂያውን እንዳየ እና በዚህ ታሪካዊ በሚሉት የጋብቻ ስነ ሥርዓት ላይ እንዲሳተፉ እንዳሳመናት የምትናገረው ሌላዋ ሙሽሪት አልማዝ የምትኖረው በኦሮምያ ክልል ሱሉልታ ከተማ ስለሆነ ሩቅ መጓዝ አይጠበቅባትም። « በስልክም አወራናቸው ሄደንም ስንጠይቃቸው ደስ የሚል እና ታሪካዊ ነገር ነው። በዛ ላይ ለሰርግ የሚወጣውን ወጪ ለቤት እቃ ማሟያ ይሆነናል። እና እሱንም ነገር ስለሚቀንስልን እዛ ላይ ለመሳተፍ ወሰንን።የዲላ ነዋሪዎቹ ተስፋዬ እና አስቴርም ለሰርግ ሊያውሉት የነበረውን ገንዘብ ለሌሎች ለሚያስፈልጋቸው ነገሮች ለማዋል ወስነዋል።

እጎአ በ2013 ዓም ደቡብ ኮርያ ውስጥ 3500 ጥንዶች አንድ ላይ ጋብቻ ፈፅመዋል።ምስል picture-alliance/AP Photo/Lee Jin-man

ሰርግ ያለ እንግዶች?

ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመዳር ሲያስቡ፤ ዘመድ አዝማድ እና ጎረቤትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ጠርተው በመሆኑ ቤተሰብን ማሰማኑ ከባዱ ፈተናቸው እንደነበር ተስፋዬ እና አስቴር ይናገራሉ።  « ከተመዘገብን በኋላ ነበር የነገርናቸው። እና አይሆንም ብለው ነበር። እነሱን ማሳመኑ ብዙ ጊዜ ወስዶብን ነበር» የምትለው አስቴር በመጨረሻ አምነው ተቀብለው ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ትናገራለች። ተስፋዬም « እውነት ነው ቤተሰብ ለመቀበል ተቸግሮ ነበር ይላል» ወጣቶቹ ጥንዶች ቤተሰባቸውን ማሳመን ሲኖርባቸው ጋዜጠኛ ዋሲሁን አራጌ ደግሞ የወደፊት ባለቤቱን ማግባባት ነበረበት። እሱም እሁድ ዕለት ከሚሞሸሩት ጥንዶች ውስጥ ነው። « ሚዲያውም ላይ ስለምሰራ እና አላማውን ከመጀመሪያው ጀምሮ እደግፈው እና ከሚያቀነቅኑ ሰዎች ውስጥ አንዱ ስለሆንኩ ይመስለኛል ይህንን ሀሳብ እንድቀበል ያደረገኝ። በርግጥ በጓደኛዬ በኩል ብዙ ሙግት ነበረኝ። ግን እዚህ ጋ የሚሳተፉ ሰዎች የኢኮኖሚ እና የገንዘብ ችግር ብቻ ያለባቸው ሰዎች አይደሉም። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ በጦርነቱም በድርቁም በተለያየ መንገድ የእኛን እገዛ የሚፈልጉ ወገኖች አሉን። ስለዚህ ለሰርግ የምናወጣውን ወጪ ለምን ለዛ ፈንድ አናደርገውም የሚለው  ሀሳብ ገዛት እና እሷም በሀሳቤ ተስማማች። አልማዝ እና የወደፊት ባለቤቷ በአንፃሩ ወላጆቻቸውን ማሳመኑ ብዙም አልከበዳቸውም ነበር።  ቤተሰቦቻችን እኛ ያልነውን የሚቀበሉ አይነት ሰዎች ናቸው። እና ምን አይነት ዝግጅት እንደሆነ አስረዳናቸው። እነሱም የእናንተ ፍላጎት የእኛም ፍላጎት ነው አሉ። እነሱም ደስተኛ ሆኑ።»ትላለች አልማዝ።

በዘንድሮው የሰርግ ሥነ ሥርዓት ላይ 2000 ኪሎ ግራም የሚመዝን ዳቦ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃልምስል Yament

ልብሳቸውንስ በተመለከተ? 

« እዛው ተመዝግበን የመጣን ቀን ነው ልብሱን ተለክተን አዘን የመጣነው » የምትለው አልማዝ « ሌላ ዝግጅት ላይ ልንለብስ የምንችለው የሀገር ባህል የጥበብ ልብስ ነው የምንለብሰው» ትላለች። ጋዜጠኛ ዋሲሁንም ልብሳቸው ተሰፍቶ እንዳለቀ ገጾልናል። « ቀሚስ ካባ ፤ የባህል ልብስ ነው። የመረጥነው አለባበስ አለ። እሱን በሰርጉ ሥነ ሥርዓት ላይ የምናሳይ ይሆናል» ይላል። « አቅማችን የሚመጥንን እና እኛን የሚገልፀን ነገር አዘጋጅተናል። የዛን ቀን ሰርፕራይዝ እናደርጋችኋለን »ስትል አስቴርም ብትሆን ስለ ሰርጓ ልብስ ብዙ ከመናገር ተቆጥባለች። « ሌሎች ያልተዘጋጁ ሰዎች ካሉ የግድ ውድ መሆን የለበትም» ስትል ምክሯን ትለግሳለች።
ከሰርግ ወጪ ጋር ተያይዞ በጋብቻ ወቅት እና ከዛ በኋላ ብዙ ጫናዎች እንዳሉ እና ለዚህ የሚሆኑ የምክር አገልግሎቶች ብዙ እንደሌሉ የሚናገረው  አማካሪ እሸቱ ገለቱ የሺ ጋብቻ ፕሮጀክት በርካታ ጥንዶችን ከከፍተኛ ወጪ የሚታደግ ብቻ ሳይሆን የከባቢ አየርን ከመጠበቅ አንፃር ብዙ አስተዋፅዎ እንደሚኖረው ያብራራል። « አንድ ጥንድ ተጋቢዎችን ለማጀብ ስንት መኪናዎች ይመጣሉ? » በማለት በተቃጠለ አየር የሚፈጥሩትን የአየር መበከል ያነሳል። ሌላው ደግሞ ለሰርግ ዝግጅት የሚውለውን ማገዶ ነው። ስለሆነም ዝግጅቱ « አረንጓዴው ጋብቻ » የሚል የፕሮጀክት ሀሳብም አለው ሲል ያስረዳል።

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW