1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች የረሃብ አድማ

ረቡዕ፣ ግንቦት 9 2015

በቅርቡ መንግስት በሽብር እና በተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥሬያቸዋለሁ ካለው 47 ተከሳሾች 44ቱ የረሃብ አድማ ማድረቸውን ቤተሰቦቻቸውና ጠበቃቸው ገለጹ፡፡ ከሰኞ ጀምሮ የሶስት ቀናት የርሃብ አድማ ማድረጋቸው የተሰማው እስረኞቹ፤ “መንግስት የህግ የበላይነትን አስከብራለሁ በሚል በርካታ የአማራ ሊሂቃንን እያሰረ ነው” በሚል ተቃውሞ ነው ተብሏል፡፡

Justitia
ምስል Volker Hartmann/dpa/picture alliance

በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ እስረኞች የረሃብ አድማ ላይ መሆናቸው ተገለጸ

This browser does not support the audio element.

የእስረኞች የረሃብ አድማ

በቅርቡ መንግስት በሽብር እና በተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥሬያቸዋለሁ ካለው 47 ተከሳሾች 44ቱ የርሃብ አድማ መምታታቸውን ቤተሰቦቻቸውና ጠበቃቸው ገለጹ፡፡

ከሰኞ ጀምሮ እስከ ዛሬ የሶስት ቀናት የርሃብ አድማ ማድረጋቸው የተሰማው እስረኞቹ፤ “መንግስት የህግ የበላይነትን አስከብራለሁ በሚል በርካታ የአማራ ሊሂቃንን እያሰረ ነው” በሚል ተቃውሞ ነው ተብሏል፡፡

በቅርቡ መንግስት በሽብር ወንጀል መጠርጠራቸውን ይፋ አድርጎ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው 47 ሰዎች ሶስቱ ብቻ በዋስ መለቀቃቸውም ተነግሯል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ባለስልጣን ግን ተደርጓል ስለተባለው የርሃብ አድማው የሚታወቅ ነገር እንደሌለ እና በዚህም ጤናው የታወከ ግለሰብ የለም ብሏል፡፡

መንግስት በቅርቡ በተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገባቸው ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች መካከል መምኅርት መስከረም አበራ ይገኛሉ፡፡ ባለቤታቸው አቶ ፍጹም ገብረሚካኤል ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት መምህርት መስከረም አበራን ጨምሮ በተለያዩ መዝገብ የተከሰሱት ከ40 በላይ ሰዎች ከሰኞ ጀምሮ የረሃብ አድማ ላይ በመሆናቸው የሚወሰድላቸውንም ምግብ አልተቀበሉም ብለዋል፡፡ “በዚህ ሶስት ቀናት ምንም ኤነት ምግብ ሲቀበሉ አልነበረም፡፡ ይህም በአማራ ሊዕቃን እና በክልሉ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና በመቃወም ጉዳዩ የአገር ውስጥ ህዝብ እና የዓለማቀፍ ማህበረሰብ ትኩረት እንዲያገኝ ጫና ለመፍጠር ነው፡፡”

የሌላው ተከሳሽ የዶ/ር አሰፋ አዳነ ቤተሰብ እንዳረጋገጡትም፤ እስረኞቹ ከሰኞ ጀምሮ እስከ ዛሬ በርሃብ አድማ ላይ ነበሩ፡፡ “እውነት ነው የርሃብ አድማ ላይ ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን ሄደን አይተናቸዋል ደህና ናቸው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡

ከተከሳሾቹ ጠበቆች አንዱ ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩትም ተከሳሾቹ የሶስት ቀናት የርሃብ አድማቸውን ዛሬ ያጠናቅቃሉ፡፡ “የርሃብ አድማቸው ለሶስት ቀናት ከሰኞ እስከ ዛሬ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ የተቃወሙትም እተፈጸመ ነው ያሉትን ጅምላ እስር እንዲቆም ጫና ለማሳደር ነው፡፡”

እንደ ጠበቃ ሰለሞን ማብራሪያ እነዚህ ተጠርጣሪዎች የታሰሩት በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሶሰርተኛ ፖሊስ ጣቢያ ነው፡፡ “ለአብነት እኔ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሚገኙት ውስጥ ወደ ዘጠን የሚሆኑትን አግኝቼ አውርቼአቸዋለሁ፡፡ በአራት መዝገብ በዚህ ክስ መመስረቱንም አይቻለሁ፡፡”

በአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምድም ችሎት የጊዜ ቀጠሮ ላይ ብቻ ወደ ሰባት መዝገብ ተከፍቶ እንደነበርም ያነሱት ጠበቃው፤ መንግስት በቅርቡ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው 47 ሰዎች ሶስቱ ብቻ በዋስ መለቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ጠበቃ ሰለሞን እና የመምህርት መስከረም ባለቤት አቶ ፍጹም የተከሳሾቹን ክስ ሂደትም በተመለከተ ይህን ብለዋል፡፡ “የክስ ሂደቱ በጊዜ ቀጠሮ ላይ ነው ያለው፡፡ እንደየመዝገቡ የተለያየ ቀን ነው ቀጠሮያቸው፡፡ አስቀድሞ ሁከት በማስነሳት የተከሰሱም አሁን ላይ በሽብር ተከሰዋል፡፡”

ዶይቼ ቬለ ስለ እስረኞቹ አሁናዊ ሁኔታ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከፍትህ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃለፊዎች መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በህቡዕ ተደራጅተው የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ ተገኝተዋል ያሏቸውን 47 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ መግለጹ ግን ይታወሳል፡፡ ግብረኃይሉ ተጠርጣሪዎቹን ከበርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች፣ ቦንቦችና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች እንዲሁም ከሳተላይት መገናኛ መሣሪያዎች እና የተለያዩ መረጃዎችን ከያዙ ላፕቶፖች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም ገልጾ ነበር፡፡

የተጠርጣሪዎቹን ማንነት በስም ጭምር የዘረዘረው ጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል “የአማራን ህዝብ የማይወክሉ” ያሏቸውና በጽንፈኝነት የፈረጃቸው ተጠርጣሪዎቹን የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን የግድያ ዒላማ በማድረግ፤ ክልሉን እና የፌደራል መንግሥትን በኃይል ለመቆጣጠር ያልማሉ ሲል መክሰሱም አይዘነጋም፡፡

ባለፈው ወር ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የነበሩ አቶ ግርማ የሺጥላ መገደላቸውን ተከትሎ፤ መንግስት በክልሉ እያደረገ ያለውን የፀጥታ ማስከበር ኦፕሬሽን ማጠናከሩንም በተለያዩ ጊዜያት ባወጣቸው መግለጫዎች ደጋግሞ አብራርቷል።

ሥዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW