የሽብር ጥቃት ዛቻን ተከትሎ የ«ፔጊዳ» ሠልፍ ተሰረዘ
እሑድ፣ ጥር 10 2007ማስታወቂያ
ከጀርመን የፌዴራል እና የክፍለ ሃገር ባለሥልጣናት በተገኘው መረጃ መሠረት የሽብር ጥቃቱ ሊደርስ ይችላል የተባለው በተለይ «ፔጊዳ» በተሰኘው ቡድን ላይ ነው። የሽብር ጥቃቱን በተለይ የ«ፔጊዳ» አመራሮችን በመግደል ለመፈፀም አቅዷል የተባለው እራሱን «እስላማዊ መንግሥት» እያለ የሚጠራው ቡድን መሆኑም ተጠቅሷል። «በምዕራባውያን ሃገራት እስልምና እንዳይስፋፋ የሚታገሉ የአዉሮፓ አርበኞች» በምኅፃሩ «ፔጊዳ» በማለት እራሱን የሚጠራው ቡድን በነገው እለት ድሬስደን ውስጥ ሰፊ የተቃውሞ ሠልፍ ለማከናወን አቅዶ ነበር። ቡድኑ ቀደም ሲል በጠራው የተቃውሞ ሠልፍ ከ18 ሺህ በላይ ደጋፊዎቹ አደባባይ መውጣታቸው ይታወሳል። «ፔጊዳ» እስልምና በምዕራቡ ሃገራት እንዳይስፋፋ ከሚያደርገው ዘመቻ በተጨማሪ፥ ስደተኞችን የሚመለከተው ሕግም እጅግ ጠበቅ ያለ እንዲሆን የሚሟገት ቡድን መሆኑ ይታወቃል። «ፔጊዳ» ለነገ ባቀደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ 25,000 ሰዎች ሊሳተፉ ይችሉ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ልደት አበበ