1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሽግግር ፍትሕና የትግራይ ጊዚያዊ ፕሬዝደንት ትችት

ረቡዕ፣ መጋቢት 11 2016

በሰብአዊ መብቶች ኮምሽኑ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ከሆኑ ማርክል ክሊመንት ጋር የተወያዩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ እስካሁን ባለው በጦርነቱ ወቅት ለተፈፀሙ ወንጀሎች የተጠያቂነት ጉዳይ የሚፈልገው ያክል ርቀት እንዳልሄደ አመላክተዋል።

አቶ ጌታቸዉ የኢትዮጵያ መንግስት ያረቀቀቁን የሽግግር ፍትሕ መርሕ «ያልተሟላ» ብለዉታል
አቶ ጌታቸዉ ረዳ የትግራይ ክልላዊ መስተዳድር ጊዚያዊ ፕሬዝደንት ምስል Million Haileselassie/DW

የሽግግር ፍትሕና የትግራይ ጊዚያዊ ፕሬዝደንት ትችት

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ፈደራዊ መንግስት የቀረፀዉን የሽግግር ፍትሕ ፓሊሲየትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት «ክፍተቶች አሉበት» በማለት ተቹት።አቶ ጌታቸዉ ትናትት የተባበሩት መንግስት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮምሽነር ተወካዮችን ሲያነጋገሩ እንዳሉት በትግራዩ ጦርነት ወቅት ለተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይገባል።የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂነትን ያረጋግጣል የሚለዉን የሽግግር ፍትሕ መርሕን ግን የትግራዩ መሪ የተሟላ አይደለም ባይ ናቸዉ።የመቀሌዉ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ዝርዝ ዘገባ ልኮልናል

 

በተባበሩት መንግስት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮምሽን የምስራቅ አፍሪካ ፅሕፈት ቤት ተጠሪ የተመራ ልኡክ ትላንት በመቐለ በነበረው ቆይታ ከትግራይ ግዝያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት ጋር የተወያየ ሲሆን፥ የሰላም ስምምነቱ የእስካሁን አፈፃፀም ሂደት፣ የተጠያቂነት ጉዳዮች እና ሌሎች ተነስተው ምክክር ተደርጎባቸዋል። በሰብአዊ መብቶች ኮምሽኑ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ከሆኑ ማርክል ክሊመንት ጋር የተወያዩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ እስካሁን ባለው በጦርነቱ ወቅት ለተፈፀሙ ወንጀሎችየተጠያቂነት ጉዳይ የሚፈልገው ያክል ርቀት እንዳልሄደ አመላክተዋል። አቶ ጌታቸው እንዳሉት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ አሰራር ሂደት ክፍተቶች ያሉት ሲሆን፥ በርካታ ወንጀሎች የፈፀሙ አካላት ጭምር ተጠያቂ ሊያደርግ የማይችል መሆኑ አንስተዋል።

 

አቶ ጌታቸው ረዳ "በመጀመርያ ደረጃ የሽግግር ፍትሕ የፕሪቶርያው የጋራ ውል አካል ነው። ይሁንና ሂደቱ በአዲስአበባ ያለ ትግራይ ተሳትፎ ነው የተጀመረው። በሁለተኛ ደረጃ የሽግግር ፍትሕ ተጠያቂነት ያረጋግጣል ብለን የምናስብ ከሆነ፥ በኤርትራ የተፈፀሙትስ ብለን ማንሳት ይጠበቃል። ባሉት መረጃዎቻችን መሰረት 75 በመቶ የሚሆን የፆታ ጥቃት የፈፀሙ የኤርትራ ሐይሎች ላይ እንዴት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ይቻላል ?"  ብለዋል።

የትግራይ ክልላዊ መስተዳድር ርዕሰ ከተማ መቀሌ በከፊልምስል Million Hailesilassie/DW

 

ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ፥ የፕሪቶርያው ውል በሙሉእነት ሳይፈፀም ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደማይቻል ያነሱ ሲሆን አሁንም የተለያዩ ወንጀሎች «ወራሪ» ባልዋቸው ሐይሎች በያዝዋቸው አካባቢዎች እየተፈፀሙ መሆኑ ገልፀዋል። በተባበሩት መንግስት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮምሽን የምስራቅ አፍሪካ ፅሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ማርክል ክሊመንት በበኩላቸው፥ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የተፈፀመበት ደም አፋሳሹ ጦርነት መቆሙ እና አንፃራዊ ሰላም መስፈኑ በአወንታ ያነሱ ሲሆን፥ የሰላም ስምምነቱ ፈራሚ አካላት በፈተናዎች ላይ ሆነው ጭምር ለሰላም ያሳዩት ቁርጠኝነት እውቅና የሚሰጠው ብለውታል።

 

"ሰላም የማስቀጠል ጥረት ትልቅ ዋጋ ያለው እና እውቅና የሚሰጠው ነው። በፌደራል መንግስቱ እና በእናንተ በኩል ለሰላም ያላችሁ ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው። ይህ ጥረታችሁ እንዲቀጥል ነው የምንፈልገው" ብለዋል።

 

የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ሂደት፣ የተፈናቃዮች ሁኔታ እና ሌሎች በዋነኝነት በውይይቱ የተነሱ ጉዳዮች ሲሆን፥ በተለይም በቅርቡ ከተካሄደው የሰላም ስምምነቱ ግምገማ በኃላ ተፈናቃዮች ለመመለስ ጥረቶች ተጠናክረው ቢቀጥሉም፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደርአቋም ግን ያፈናቀሉ አካላት ቦታቸው ሳይለቁ የተፈናቀሉት መመለስ አስቸጋሪ መሆኑ እንደሚያምን ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው ረዳ "በቅርቡ፥ በተለይም በአፍሪካ ሕብረት ፓነል ከተደረገው ግምገማ በኃላ ተፈናቃዮች ወደቦታቸው እንዲመለሱ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር እየተጣረ ነው። በዚህ የእኛ አቋም ችግር የፈጠሩ፣ ያፈናቀሉ አካላት ባሉበት ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው ሊመለሱ የሚችሉበት ሁኔታ ስለሌለ ቦታው ወደ ግዚያዊ አስተዳደሩ ይመለስ ነው" ብለዋል።

ትግራይ/ ኢትዮጵያ ግዛት አሁንም እንደሰፈረ ነዉ የሚባለዉ የኤርትራ ጦር ከያዘዉ አካባቢ እንዲወጣ የሚደረገዉ ግፊት እንደቀጠለ ነዉምስል Loredana Sangiuliano/SOPA Images/ZUMAPRESS.com/picture alliance

በጦርነቱ ወቅት ለተፈፀሙት ወንጀሎች በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እየሰራሁ ነው የሚለው የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ በኩል ተቃውሞ ደርሶበታል። በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ከወራት በፊት ለኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር የፃፉት ደብዳቤ፥ በፌደራሉ መንግስት የተቀረፀው የሽግግር ፍትሕ ፓሊሲ የፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት ያላደረገ፣ የትግራይ ልዩ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ የትግራይ ወሳኝ ተሳትፎ ያላካተተ መሆኑ በማንሳት መተቸቱ ይታወሳል።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW