የሽግግር ፍትሕ መመሪያ
ዓርብ፣ ጥር 26 2015
የኢትዮጵያ የፍትሕ ሚንስቴር ለሐገሪቱ የታቀደዉ ሽግግር ፍትሕ የሚመራበትንና ሥራ ላይ ሚዉልበት ሥለተባለዉ የፖሊሲ ሰነድ ዛሬ ማብራሪያ ሰጠ።መስሪያ ቤቱ በቅርቡ ይወጣል ባለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ውስጥ የማስፈፀሚያ ስልቶቹ ክስ፣ እውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማድረግ፣ እርቅ ፣ ምህረት እና ማካካሻ መሆናቸው ተገልጿል።
የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት መዘርጋት ዘላቂ ሰላም ፣ እርቅ እና ፍትሕ በማስገኘት ረገድ ውጤታማ መሆኑንና በግጭት፣ በጦርነት ወይም በሌላ ምክንያት ለተፈፀሙ ጥቃቶች ፣ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና በደሎች የተሟላ መፍትሔ ይሰጣል ሲል ሚኒስቴሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ያስጠናው ሰነድ ይዘረዝራል።
በሌሎች ሀገራት ክስ እና ቅጣት ዋነኛ የሽግግር ፍትሕ ማስተግበሪያ ስልቶች ሆነው መታየታቸውንም ሰነዱ ያትታል። ማብራሩያ የተሰጠበት እና በሂደት ላይ ያለው ይህንን የተመልከተው ፖሊሲ ከክስ እና ቅጣት ባለፈ "እውነት እየተጣራ ይፋ የሚሆንበት ፣ እርቅ የሚሰፍንበት፣ የማካካሻ እርምጃ እና የተቋማት ለውጥ የሚካሄድበት ይሆናል" ተብሏል። የፖሊሲው አጥኚ ቡድን አባል አቶ ምስጋናው ሙሉጌታ።
ፍትሕ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትሕ በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች አስፈላጊ መሆኑን አስታውቋል። ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሀገራዊ አውድ ማለትም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፣ አለመረጋጋት፣ ግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት በመቀጠሉ ዜጎች ለሞት፣ ለመፈናቀል አደጋ እየተጋለጡ በመሆኑና ለነዚህ ችግሮች ከዚህ በፊት የተሰጡ ምላሾች ሙሉ አለመሆባቸው የአጥፊዎችና የተጎጅዎችን ቁጥር ማብዛቱ ፣ የበደሎች መደራረብ እና የጥፋቶች ማህበረሰባዊ ቅርጽ መያዝ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት እና አካሄድ ፍትሕ መስጠትንም ሆነ ይቅርታ እና እርቅን ማከናወን አላስችል በማለቱ የመጀመርያው ነው።
የተሳካ የሽግግር ፍትሕ ለሀገረ - መንግሥት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ማለትም ባለፉ በደሎች ይቅር ለመባባልና እርቅ ለማውረድ ብሎም እየተከፋፈለ ያለውን ሕዝብ ለማቀራረብ ግንኙነትን ለመጠገን ፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና እርቅን ለመስጠት ለዚህም የሰውን ክብር ለመምለስ፣ ላለፈ ቁስል እውቅና ለመስጠት እንዲሁም ለጋራ ዳግም ውህደት ሁለተኛው ሲሆን የተሳካ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ሳይተገበር የዴሞክራሲ ሽግግርም ሆነ ዘላቂ ሰላም ማስፈን የማይቻል መሆኑ እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚሉት ናቸው።
በጉዳዩ ዙሪያ ከዚህ በፊት ለዶቼ ቬለ ማብራሪያ የሰጡት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት አቶ አሮን ደጎል የችግግር ፍትሕ "ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን የሚውል" ስልት መሆኑን ገልፀው ነበር።
በሽግግር ፍትሕ ውስጥ የገለልተኛ ወገን ተሳትፎ መሠረታዊ ጥያቄ ነው። ይህንን የሽግግር ጊዜ ፍትሕ ማስፈፀሚያ ሆነው ከቀረቡ ስልቶች ደግሞ ዋነኛው ክስ ነው። ማን ይከሰሳል የሚለውም ዋነኛ ነጥብ ነው። እውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማድረግ፣ እርቅ ፣ ምህረት፣ ማካካሻ ወይም ለደረሱ የመብት ጥሰቶች ብሎም የሀብት ውድመቶች ውጤታማና ተመጣጣኝ የገንዘብ ወይም ሌላ ካሳ ፣ መጠገኛ ፣ ማደሻን ማገዝን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ያካትታል።
ይህ ሀገራዊ ጉዳይ መቼ ይጀመር የሚለው ግን ገና የመንግሥትን ውሳኔ የሚጠይቅ ነው ተብሏል።
ሰለሞን ሙጩ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ