1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

የሽግግር ፍትሕ አተገባበር ጉዳይ ምን ላይ ደረሰ?

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 21 2017

የፍትሕ ሚኒስቴር ባዋቀረውና 13 አባላት ባሉት የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን ሲከናወን የነበረው ሥራ ውጤቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ሂደቱ ምን ላይ ይገኛል? የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሳምንታት በፊት ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ ሲያደርግ "ከሕግ ረቂቅ ሰነዶች ውጪ ሌሎች ተግባራት በታቀደላቸው ጊዜ አለመከናወናቸው አሳሳቢ ነው" ብሏል።

የፍትኅ ምልክት
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዝያ 9 ቀን 2016 የጸደቀው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲደረግ በኢትዮጵያ “ዘላቂ ሰላም፣ ዕርቅ፣ የህግ በላይነት፣ ፍትሕ እና ዲሞክራሲ የሚረጋገጥበት መደላድል የመፍጠር” ዓላማ ነበረው። ምስል፦ picture-alliance/dpa/U. Baumgarten

የሽግግር ፍትሕ አተገባበር ጉዳይ ምን ላይ ደረሰ?

This browser does not support the audio element.

የፍትሕ ሚኒስቴር ያዋቀረውና ገለልተኛ በተባለ 13 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ጥናት ተደርጎ "ጉልህ በሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም ወንጀሎች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት" እንዲኖር፣ "ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት" እንደደረግ፣ "አዲስ ወይም ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም ክስ የመስማት እና ውሳኔ የመስጠት ተግባር ማከናወን" የሚሉ እና ሌሎች አቅጣጫዎን ሰጥቶ ተግባሩን ማጠናቀቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሳምንታት በፊት ይፋ ባደረገው ዓመታዊ የመብቶች አያያዝ ሪፖርት የሽግግር ፍትሕን በሚመለከት "አሳሳቢ" ካላቸው  ጉዳዮች መካከል "ከሕግ ረቂቅ ሰነዶች ውጪ ሌሎች ተግባራት በታቀደላቸው ጊዜ አለመከናወናቸው" አንደኛው ነው። "ረቂቅ ሕጎችም ለሕዝብ ውይይት እስከ አሁን አልቀረቡም" ያለው ኮሚሽኑ "አጠቃላይ ሂደቱ እየተመራ ያለበት አግባብ ለሕዝብ ግልጽ አልተደረገም" ሲልም ገልጿል።

ለትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ውጥረት ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጥ ተጠየቀ

ኢሰመኮ "የሽግግር ፍትሕን የመተግበር የፖለቲካ ቁርጠኝነት በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶችን የማስቆም ጥረቶችን ሊያካትት ይገባል" በማለት "በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች እና የጸጥታ ችግሮች መኖራቸው ለእነዚህም ምላሽ ለመስጠት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ውጤታማ አለመሆን
የሽግግር ፍትሕ ትግበራ አሳሳቢ ተግዳሮቶች ናቸው" በማለት በሪፖርቱ ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ "የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ከተሸጋገረ በኋላ የመቀዛቀዝ አዝማሚያ እያሰየ መሆኑ" ሌላው "አሳሳቢ ጉዳይ" እንደሆነ ጠቅሷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍትሕ ሚኒስቴር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ምላሽ አላገኘም።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አርቃቂ ባለሙያዎች ምን እየሠሩ ይኾን ?

የሕግ ባለሙያው አደም ካሴ ዛሬ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ሙያዊ መብራሪያ "የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መዳከም" እና በጉዳዩ ዙሪያ "የውጭ ጫና" መቀነሱ አተገባበሩ ላይ መቀዛቀዝ እንዲታይ አድርጓል ብለዋል።

የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ከየትኛው ጊዜ ይጀምር ለሚለው የፖሊሲ ጥያቄ የባለሙያዎች ቡድን "ለክስ ጉዳይ ከ 1983 ዓ .ም ጀምሮ፣ ለሌሎች ጉዳዬች ደግሞ መረጃ እና ማስረጃ እስከተገኘበት ድረስ" የሚል አማራጭ አቅርቦ ነበር።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሳምንታት በፊት ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ ሲያደርግ "ከሕግ ረቂቅ ሰነዶች ውጪ ሌሎች ተግባራት በታቀደላቸው ጊዜ አለመከናወናቸው አሳሳቢ ነው" ብሏል።ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን "ያለፉ ጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመፍታት እና ዳግም እንዳይከሰቱ ዋስትና
ለመስጠት የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር ግልጽ የሆነ መነቃቃት መኖሩን" በሪፖርቱ በአዎንታ ጠቅሶታል።

የሕግ ባለሙያው አደም ካሴ መንግሥት ቅድሚያ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ መስጠቱ ለሽግግር ፍትሕ ሥራ መቀዛቀዝ አንድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል። ከምንም በላይ ግን ለአተገባበሩ "የውስጥም የውጭም ጫና መቀነሱን" በምክንያትነት አንስተዋል።

የሲቪክ ድርጅቶች ስለ የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ

ኢሰመኮ "እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት በመፍታት፣ በመላ ሀገሪቱ ሰላምና ጸጥታን በማስጠበቅ እና የሕግ የበላይነትን በማስከበር፣ አካታች፣ ተጎጂዎችን ያማከለ እና ሰብአዊ መብትን የሚያከብር የሽግግር ፍትሕ ሂደት ለመተግበር ምቹ ሁኔታን መፍጠር በዋነኝነት ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሠራ ይገባል" የሚል ምክረ ሀሳብ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ አለመረጋጋት፣ ግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት መቀጠሉ ዜጎች ለሞት፣ ለመፈናቀል አደጋ እየተጋለጡ በመሆኑና ለነዚህ ችግሮች ከዚህ በፊት የተሰጡ ምላሾች ሙሉ አለመሆናቸው የአጥፊዎችና የተጎጅዎችን ቁጥር ማብዛቱ ፣ የበደሎች መደራረብ እና የጥፋቶች ማሕበረሰባዊ ቅርጽ መያዝ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት እና አካሄድ ፍትሕ መስጠትንም ሆነ ይቅርታ እና እርቅን ማከናወን አላስችል ማለቱ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና እርቅን ለመስጠት የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ መሆኑን መንግሥት እንዳመነበት እና ወደ ሥራ መግባቱን ከዚህ በፊት አስታውቋል።

ሰለሞን ሙጪ

ኂሩት መለሠ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW