1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ሠነድ ያዘጋጀው የባለሙያዎች ቡድን ሥራውን አጠናቀቀ

ሰኞ፣ የካቲት 4 2016

የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ሠነድ ሲያዘጋጅ የቆየው 13 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ሥራውን አጠናቆ መበተኑ ተገለፀ። ሥራውን ሕዳር 2015 ዓ.ም የጀመረው የባለሙያዎች ቡድን የፖሊሲ ረቂቅ ሰነዱን የመጨረሻ ውጤት ታኅሣሥ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ አድርጎ ነበር። ቅድሚያ ሥራው አማራጭ ሰነድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባት እንደነበርም ያስታውሳሉ።

የፍትህ ሚኒስቴር
የፍትህ ሚኒስቴር ምስል Solomon Muchie/DW

የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ ሠነድ 13 ባለሙያዎችን ያካተተ ነበር

This browser does not support the audio element.

የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ሠነድ ያዘጋጀው የባለሙያዎች ቡድን ሥራውን አጠናቀቀ

የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ሠነድ ሲያዘጋጅ የቆየው 13 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ሥራውን አጠናቆ መበተኑ ተገለፀ። ሥራውን ሕዳር 2015 ዓ.ም የጀመረው የባለሙያዎች ቡድን የፖሊሲ ረቂቅ ሰነዱን የመጨረሻ ውጤት ታኅሣሥ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ አድርጎ ነበር።

የባለሙያዎች ቡድን ተጠያቂነት ፣ እውነት ማፈላለግ፣ ምህረት ፣ ማካካሻ እና ካሳ በሚባሉት አምስት የሽግግር ፍትሕ ዐምዶች ላይ ለስምንት ወራት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሀገሪቱ ውይይት ማድረጉን አስታውቋል። የባለሙያዎች ቡድን ይህ ረቂቅ ፖሊሲ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ይልቅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት ቢፀድቅ የሚል ምክረ ሀሳብንም ለመንግሥት አቅርቧል።

ከሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ ሠነድ አዘጋጅ 13 ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ማርሸት ታደሠ የባለሙያዎች ቡድን የተሠጠውን ተግባር አጠናቆ ባለፈው ሳምንት ማስረከቡን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። የባለሙያዎች ቡድን በቅድሚያ ያደረገው አማራጭ ሰነድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባት እንደነበርም ያስታውሳሉ። "ረቂቅ ፖሊሲውን እንደባለሙያ ቡድን አዘጋጅተን ለመንግሥት አስረክበናል። ይህም የሆነው ጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ነው። እንደባለሙያ የተሰጠንን ኃላፊነት ተግባር ተወጥተን ሥራችንን ጨርሰናል"

የረቂቅ ፖሊሲው ዋና ዋና ጭብጦች 

ተጠያቂነት ፣ እውነት ማፈላለግ፣ ምህረት ፣ ማካካሻ እና ካሳ ዋናውቹ የሽግግር ፖሊሲ ዐምዶች ሲሆኑ ሠነዱ የትኞቹ አጥፊዎች ላይ ክስ ይመስረት ? ለሚለው ጥይልቄ "ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት ሊኖር ይገባል" የሚል ግኝት አመላክቷል። የፍርድ ሂደቱን ማን ያከናውነው? ለሚለው ጥያቄ አብዛኛው የሽግግር ፍትሕ የሕዝብ ምክክርተሳታፊዎች "አዲስ ወይም ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም ክስ የመስማት እና ውሳኔ የመስጠት ተግባር ማከናወን ይገባል" የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።
አብዛኛዎቹ የውይይቱ ተሳታፊዎች "ጉልህ በሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም ወንጀሎች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት ሊኖር ይገባል።" የፍርድ ሂደቱን ማን ያከናውነው ? ለሚለው ጥያቄም "አዲስ ወይም ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም ክስ የመስማት እና ውሳኔ የመስጠት ተግባር ማከናወን ይገባል" የሚል ሀሳብ ተሰጥቷል።
የወንጀል ምርመራ እና ክስ የመመስረት ሂደትን ማን ያከናውነው ? የሚለው "አሁን ካለው የምርመራ እና የዐቃቤ ሕግ ተቋም ውጭ የምርመራ እና የክስ ሂደቶችን የሚያስተባብር ልዩ፣ ነጻ እና ገለልተኛ የምርመራ እና የክስ ሥራ የሚሠራ ተቋም በማቋቋም እንዲሁም የተሻለ እውቀት እና ልምድ ያላቸውን የምርመራ ባለሙያዎች እና ዐቃቤ ሕግ በመመደብ" ሥራው ሊከናወን ይገባል በሚል ተመላክቷል። እውነት ማፈላለግ እና እርቅን በተመለከተ "በአዲስ የእውነት አፈላላጊ ተቋም" አማካኝነት መከናወን አለበት" ተብሏል። 


ፖሊሲውን በማን ይጽድቀው ? በፓርላማው ወይስ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ?


ፍትሕ ሚኒስቴር ይህንን ሰነድ መቼ ወደ ፖሊሲ ቀይሮ በተግባር ላይ ያውለዋል የሚለው ላይ እና ሂደቱ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ምላሽ እንዲሰጥበት የተቋሙን የሥራ ኃላፊዎች ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ዶክተር ማርሸት እንደሚሉት በቀጣይ የፍትሕ ሚኒስቴር በተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ውስን ምክክር በማድረግ ግብዐት ከተሰበሰበ በኋላ እንደምፀድቅ ገልፀዋል። የባለሙያዎች ቡድን ረቂቅ ፖሊሲውን ማን ያጽድቅ በሚለው ላይ አንድ መሠረታዊ ምክረ ሀሳብ ማንሳቱንም ባለሙያው ገልፀዋል።

የሽግግር ፍትሕ ያስፈለገበት ምክንያት


ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፣ አለመረጋጋት፣ ግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት መቀጠሉ ዜጎች ለሞት፣ ለመፈናቀል አደጋ እየተጋለጡ በመሆኑና ለነዚህ ችግሮች ከዚህ በፊት የተሰጡ ምላሾች ሙሉ አለመሆናቸው የአጥፊዎችና የተጎጅዎችን ቁጥር ማብዛቱ ፣ የበደሎች መደራረብ እና የጥፋቶች ማሕበረሰባዊ ቅርጽ መያዝ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት እና አካሄድ ፍትሕ መስጠትንም ሆነ ይቅርታ እና እርቅን ማከናወን አላስችል ማለቱ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና እርቅን ለመስጠት የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ መሆኑን መንግሥት እንዳመነበት ገልጿል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW