«ኢትዮጵያ የአፍሪካን ከ60 እስክ 70% የቀርቀሀ ደን ሀብት ትሸፍናልች»
ቅዳሜ፣ ጥር 17 2017
የቀርቀሀ ተክል በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኝ ሲሆን በተለይ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደርና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በስፋት እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። ተክሉ በባህላዊ መንገድ እየተዘጋጀ ለመቀመጫ፣ ለምግብ ማቅረቢያ፣ ለቤት ማስጌጫ ይውላል። በዚሁ በባህላዊ የቀርቀሀ ምርት ሥራ ከተሰማሩ ወጣቶች መካክል አንዳንዶቹ ምረቱ በባህላዊ የሚመረት በመሆኑና ወደ ዘመናዊነት ባለመሻገሩ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አላደገም ይላሉ።
“... ችግሩ ወደ ዘመናዊነት ያልተሸጋገረው ትንንሽ ማሽኖች አሉ፣ እነሱ መግባት አልቻሉም፣ በእጃችን ነው የምንፈቀፍቅ፣ እሱም አድካሚ ነው፣ ጊዜ ይጨርሳል፣ 3 ቀን 4 ቀን ሠርተን የምንሸጥበት ዋጋ አይመጣጠንም አድካሚ ነው በጣም፡፡” ብለዋል አስተያየታቸውን ከሰጡን የእንጅባራ ከተማ ወጣቶች።
ቀርቀሀን በዘመናዊ ማሽን ታግዞ ለአገልግሎት ማዋል አልተቻለም
ሌላው ወጣትም የተሻለና ተወዳዳሪ የሆነ ዘመናዊ ምርት ለማምረት በማሽን መታገዝ እንደሚያስፈልግ ይናገራል። ይሁን እንጂ ለዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱ ለቀርቀሀ ማምረቻ የሚሆን ማሽንም ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባ አስመጪ እንደሌለ ገልጻል።
ባህላዊ የቀርቀሀ ሥራም ቢሆን በስልጠና ያለተደገፍ፣ የገበያ ትስስር የሌልውና የማሸጫና የመስሪያ ቦታ ያልተመቻቸለት እንደሆነ ነው ወጣቶቹ የሚናገሩት፡፡
በግል ተቋማት የሚሰጡ ሥልጠናዎች መሰርታዊ እውቀት የሚያስጭብጡ አይደሉም
የሚሰጡ ስልጠናዎች አጫጭርና መሰራታዊ እውቀት የማይሰጡ እንድሆነ ገልጠዋል፣ ስልጠና እየተባለ ለዓመታት ቢሰጥም ውጤት የለውም ነው የሚሉት፡፡ ይህን አስተያየት የሰጠን ወጣት በመንግስት ሁለት ወር ሰልጥኖ የተሻለ ስራ እየሰራ ቢሆንም በግል እየመጡ አሰለጥናለሁ የሚሉ አካላት ግን በቂ ስልጠና አይሰጡም ሲሉ ነው ያብራሩት።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ተተተኪ መምሪያ ኃላፊ አቶ ወለሌ ጌቴ የወጣቶችን ጥያቄ ለመመለስና ሀብቱን በሰፊው ለመጠቀም የበሔረሰብ አስተዳደሩ በጀትና አቅም በሚፈቅደው መጠን እየተሰራ ነው ብለዋል። ተከታታይነትና ረጅም ስልጠና ለመስጠት የበጀት እጥረት ቢኖርም ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት እየተደረገ ነው ብለዋል። ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደርግሁት ጠረት ግን አልተሳካም።
የብድር መስፈርት ለሚያቀርቡ ማህበራት ማሸን ማቅረብ ስለመቻሉ
የመስሪያ ማሽንን በተመለከተ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ምን ዓይነት መሳሪያ እንደሚፈልጉ፣ መሳሪያው የት እንደሚገኝ ከገለፁና የብድር መስፈርት ካሟሉ፣ የአዋጭነት እቅድ ካመጡ የቀርቀሀ ማምረቻ ማሽን ተቋማቸው ሊያቀርብ እንደሚችል በአማራ ክልል የዋሊያ ካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንዳለ ጌታሁን ተናግረዋል።
“ቀርቀሀ አመርታለሁ ብሎ ዝርዝር መግለጫውን፣ ዋጋውን፣ ማሽኑ የት እንደሚገኝ አዋጪነቱን አጥንቶ ማቅረብ ያለበት ተበዳሪ ማህበሩ ነው፣ የዋሊያ ካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበር በራሱ እየገዛ አያቀርብም፣ ስለዝህ ራሳቸው መትተው ቀርቀሀ ማምረት ፈልገናል፣ ይህ ግብዓት እዚህ አል፣ ምርቱን በዚህ በዚህ መንገድ እናመርታለን፣ በዚህ መንገድ እሸጣለሁ፣ አዋጪ ነው ከእናንተ ጋር ብንሰራ ብለው መጠየቅ አለባቸው፣ ክዚያም እቅዳቸውና ማመልከቻቸው ተመዝኖ አዋጪ መሆኑ በአክሲዮን ማህበሩ ሲፀድቅ ማሽኑ ተገዝቶ በብድር ሊሰጣቸው የችላል” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ የአፍሪካን 70% የቀርቀሀ የደን ሀብት ትሸፍናለች”
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በቀርቀሀ ተክል ላይ ሰፋ ያለ ምርምር ያደረጉት ዶ/ር ሽፈራው አበበ የቀርቀሀ ተክልን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ያለውን የአቅም ክፍተት በስልጠና መሙላት፣ ዘመናዊ ማሽኖችን አስገብቶ ወደ ሥራ ማስገባትና ለዘርፉ ትኩረት መስጠት ተገቢ እንደሆን አመልክተዋል።
ባለሙያው እንዳሉት ኢትዮጵያ የአፍሪካን ከ60 እስክ 70% የቀርቀሀ ደን ሀብት ትሸፍናልች፣ በአገራችን 14% በደጋማው አካባቢ በባህላዊ መንገድ ቀርቀሀ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ምርት የሚመረትበት ቢሆንም ከአጠቃላይ ሽፋኑ አኳያ ግን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ገና ምኑም አልተነካ ነው ያሉት።
ዓለምነው መኮንን
ልደት አበበ