1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀኝ ጽንፈኞች በፈረንሳይ ምክር ቤት የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ማሸነፍ አንድምታ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 25 2016

በፈረንሳይ የተፈራው ደርሷል።በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ ሆኖ የማያውቅ የተባለው እሁድ የተካሄደው የመጀመሪያው ዙር የምክር ቤት ምርጫ ውጤት አሳስቧል። RN በ2ተኛው ዙር ምርጫ እዳያሸንፍ የማድረግ ጥረቶች ቀጥለዋል።ሆኖም በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ያሸነፉ የእነለፔን እጩ ተወዳዳሪዎች ብዙ በመሆናቸውው ምናልባት ከማክሮን ጋር አብረው ሊሰሩ ይችሉ ይሆናል።

የአሸናፊው የNational  Rally መሪ ማሪን ለፔን
የአሸናፊው የNational Rally መሪ ማሪን ለፔንምስል Maillard/Maxppp/Imago

የቀኝ ጽንፈኞች በፈረንሳይ ምክር ቤት የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ማሸነፍ አንድምታ

This browser does not support the audio element.

የፈረንሳይ ምክር ቤት የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ውጤት አሳስቧል

በፈረንሳይ የተፈራው ደርሷል። በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ ሆኖ የማያውቅ የተባለው እሁድ የተካሄደው የመጀመሪያው ዙር የምክር ቤት ምርጫ ውጤት ያልተጠበቀ ባይሆንም ብዙዎችን ማስደንገጡ ማሳሰቡም አልቀረም። ድሮ በዘረኛነቱ ፈረንሳውያን ያገለሉት የነበረው በፈረንሳይኛ መጠሪያው Rassemblement National ወይም በእንግሊዘኛው National Rally የተባለው የፈረንሳይ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ በመጀመሪያ ዙር ምርጫ የበላይነትን ማግኘቱ ደጋፊዎቹን ሲያስፈነጥዝ ተቃዋሚዎችን አስደንግጧል። ከአንድ ወር በፊት በተካሄደው የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ምርጫ ቀኝ ጽንፈኞች አብላጫ ድምጽ ሲያሸንፉ ፣የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ የመሀል አቋም ያለው ፓርቲ ደግሞ ፣አነስተኛ ድምጽ ካገኘ በኃላ ማክሮ የፈረንሳይ ፓርላማ  ተበትኖ አዲስ ምርጫ እንዲጠራ ድንገት ባሳለፉት ውሳኔ ነው መሠረት ነው ምርጫው የተካሄደው። ይሁንና በአሁኑ የፈረንሳይ ምክርቤታዊ ምርጫም ቀኝ ጽንፈኛው የለፔን ፓርቲ በአውሮጳ ፓርላማ ካገኘው ድምጽ የበለጠ 33.2 በመቶ ድምጽ በማሸነፍ ድል ሲያደርግ ፣የግራ ክንፍ ፓርቲዎች ጥምረት በ28 በመቶ ድምጽ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።የመሀል አቋም የሚያራምደው የማክሮ ፓርቲ ደግሞ 20 በመቶ ድምጽ ብቻ አሸንፎ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።ጽንፈኝነት በአውሮጳ

ድሉ ቀኝ ጽንፈኞቹን አስፈንድቋል። የባለድሉ የRN ፓርቲ መሪ ማሪን ለፔን ውጤቱን ታሪካዊ ብለውታል።«ታሪካዊ ውጤት ነው። እስከዛሬ በመጀመሪያ ዙር ምክር ቤታዊ ምርጫ አንድም የNATIONAL RALLY እጩ ተወዳዳሪ አሸንፎ አያውቅም ነበር።  ዛሬ ግን በመጀመሪያው ዙር ምርጫ በርካታ እጩ ተወዳዳሪዎች ተመርጠዋል። እንደሚመስለኝ ይህ በሚሊዮኖች ለሚቆጠር የፈረንሳይ ህዝብ የትልቅ ተስፋ አንድ አካል ነው።»

National Rally እንዴት ለድል በቃ 

የዛሬ 48 ዓመት የተመሰረተው ናሽናል ራሊ በፈረንሳይ እንደ ፋሺስት ቡድን የሚወገዝ ፓርቲ እንደነበር ከ40 ዓመታት በላይ ፈረንሳይ የኖሩትና ፈረንሳይም የተማሩት  የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አቶ ፉአድ እስማኤል ያስታውሳሉ ።  የፓርቲው መሪ ማሪን ለፔን ፓርቲውን ካቋቋሙት ከአባታቸው ዦን ማሪ ለፔን ከተጣሉ በኋላ ፓርቲውን ጠቅለው ሲይዙ የፓርቲውን ገጽታ ለመቀየር ብዙ ጥረት ማድረጋቸው ለአሁኑ ድል ካበቋቸው ምክንያት ውስጥ አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል። ስልጣን ከያዙ በኃላ የሀብታሞችን ጥቅም በማስጠበቅ ወቀሳ የሚቀርብባቸው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ ደግሞ ቀስ በቀስ የህዝብ አመኔታን በማጣታቸው የቀኝ ጽንፈኞች መድረክ እየሰፋ አሁን ለደረሱበት ደረጃ እንዳበቃቸውም አስረድተዋል።አቶ  ፉአድ « ህዝቡ ለፔንን ብንሞክራትስ ወደሚል አማራጭ መሄዱን ገልጸዋል።

የፓሪስዋ የዶቼቬለ ዘጋቢ ሃይማኖት ጥሩነህ የእሁዱ ምርጫ ውጤት በፈረንሳይ ፖለቲካ ብዙ ለውጦች ሊመጡ እንደሚችሉ ጠቋሚ መሆኑን ገልጻለች። እነለፔንን ለመመረጥ ያበቃቸውም የተጠራቀሙ የፈረንሳይ ችግሮች ድምር ውጤት ነው ትላለች።የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ምርጫ ውጤትና አንድምታው

ስልጣን ለመያዝ የተቃረበው የማሪን ለፔን ፓርቲ

የለፔን ፓርቲ አሁን ስልጣን ለመያዝ በሩ ላይ ቆሟል እየተባለ ነው። ከፓርቲው አመራሮች በተለይ የRN ሊቀመንበር የ28 ዓመቱ  ወጣት ጆርዳን ባርዴላ ለሁለተኛው ዙር ምርጫ ህዝቡ በአብላጫ ድምጽ እንዲያሸንፉ ከመረጣቸው የወደፊቱ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን እያስብኩ ነው ብለዋል።  

ጆርዳን ባርዴላ የNational Rally ሊቀመንበር ምስል Sarah Meyssonnier/REUTERS

«በሚቀጥለው እሁድ የፈረንሳይ ህዝብ ሀገሪቷን በእግሯ እንድናቆም ፍጹም አብላጫ ድምጽ ከሸለመን የሁሉም የፈረንሳይ ህዝብ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን አስባለሁ። እያንዳንዱን ሰው እያዳመጥኩ ተቃዋሚዎችን እያከበርኩ ስለ ብሔራዊ አንድነትም ትኩረት እሰጣለሁ።»

ቀኝ ጽንፈኛው RN  ስልጣን ለመያዝ ባኮበከበበት በዚህ ወቅት ላይ ማክሮ ከአንድ ወር በፊት ምርጫ እንዲጠራ ለምንና እንዴት ወሰኑስ የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። አቶ ፉአድ እንደሚሉት ማክሮ ለብቻቸው አሳለፉ በሚባለው በዚህ ውሳኔ ሳይሳሳቱ አልቀሩም።

ከሁለተኛው ዙር ምርጫ ምን ይጠበቃል?

የቀኝ ጽንፈኞች ድል በሁለተኛው ዙር ምርጫም ከተደገመ የፈረንሳይን የፖለቲካ አቅጣጫ ሊቀይር በአውሮጳ ኅብረት ሆነ በዓለም የፖለቲካ መድረክ  ፈረንሳይ የምትጫወተው ግንባር ቀደም  ሚናም ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር መቻሉ ይነገራል። በፈረንሳይ የዴሞክራሲ ታሪክ እስከዛሬ ያልታሰበ ስጋት የፈጠረ የተባለውን የለፔን ፓርቲን ዳግም የማሸነፍ እድል መከላከል ዋነኛ ዓላማቸው መሆኑን የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋብርየል አታ ከእሁዱ ምርጫ ውጤት በኋላ ተናግረዋል። የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሂደትና ውጤት   

«የዛሬው ትምሕርት ቀኝ ጽንፈኞች ስልጣን በር ላይ መድረሳቸው ነው። በዴሞክራሲያችን ታሪክ በብሔራዊ ምክር ቤታችን የቀኝ ጽንፈኞች የመበራከት ስጋት አጋጥሞን አያውቅም። እናም ዓላማችን ግልጽ ነው። NATIONAL RALLY በሁለተኛው ዙር ምርጫ ፍጹም አብላጫ ድምጽ እንዳያገኝ ፣ አባላቱ በብሔራዊው ምክርቤትም እንዳያመዝኑ  እና አጥፊ በሆነው መርኃቸው ሀገሪቱን እንዳይመሩ መከላከል ነው።»

RN ዳግም እንዳያሸንፍ  የሚደረጉ ጥረቶች 

የRN ተቃዋሚዎች ሰልፍ በፓሪስምስል Sebastien Salom-Gomis/AFP/Getty Images

RN አብላጫ ድምጽ አግኝቶ እዳያሸንፍ የማድረግ ጥረቶች ቀጥለዋል ሆኖም አቶ ፉአድ እንደሚሉት በመጀመሪያው ዙር ያሸነፉ ብዙ የእነለፔን እጩ ተወዳዳሪዎች በመኖራቸው ምናልባት  ከማክሮ ጋር አብረው ሊሰሩ የሚችሉበት እድል ሊያጋጥማቸው ይችል ይሆናል። የፈረንሳይ ምክር ቤት የሁለተኛውን ዙርና ወሳኙን ምርጫ ውጤት ከወዲሁ መተንበይ አስቸግሯል። የግራ ፓርቲዎችና የመሀል አቋም ያላቸው ፓርቲዎች የለፔን ፓርቲ በመጀመሪያው ዙር ያገኘው ውጤት በሁለተኛው ዙርም እንዳይደግም ጥረታችንን እናጠናክራለን እያሉ ነው። ምንም እንኳን ምርጫው ጥቂት ቀናት የቀሩት ቢሆንም የለፔን ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ቀኝ ጽንፈኛው ፓርቲ በሁለተኛው ዙር ምርጫ አይሳካለትም የሚል መላምቶችንም እየሰነዘሩ ነው።እንግዲህ ሁሉም በመጪው እሁዱ ምርጫ የሚለይለት ይሆናል። 

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW