1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የቀድሞዉ የትግራይ ጊዚያዊ ፕሬዝደንት የሚመሩት የህወሓት አንጃ አዲስ ፓርቲ መሰረተ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 19 2017

በሁለት ተከፍለው ለረዥም ግዜ ሲወዛገቡ ከነበሩት የህወሓት ቡድኖች መካከል የሆነው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ክንፍ አስቀድሞ ሲገልፀው እንደነበረ አዲስ ፓርቲ በመመስረት፥ በሌላ መንገድ ወደ ትግራይ ፖለቲካ ተቀላቅሏል።

አዲስ የሚመሠረተዉ የፖለቲካ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ የተሰኘ እንደሆነ መሥራቾቹ አስታዉቀዋል
የቀድሞዉ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸዉ ረዳ የሚመሩት የህወሓት አንጃ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ከምርጫ ቦርድ ፍቃድ አገኘ።ምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

የቀድሞዉ የትግራይ ጊዚያዊ ፕሬዝደንት የሚመሩት ቡድን አዲስ ፓርቲ ሊመሰርት ነዉ

This browser does not support the audio element.

በእነ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግዚያዊ የምዝገባ ፍቃድ አገኘ። ህወሓት የማሻሻል እና ማዳን ጉዳይ የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር በአዲስ ፓርቲ ለመምጣት መቻላቸው ከአዲሱ ፓርቲ ምስረታ አስተባባሪዎች መካከል የሆኑት አቶ ረዳኢ ሓላፎም ለዶቼቬለ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ለረዥም ግዜ በህወሓት ላይ በተለይም ከምዕራባውያን ይቀርብ የነበረ ትችት የሚመልስ ጭምር ነው የተባለ ሲሆን በቅርቡ መስራች ጉባኤው እንደሚያደርግም ተገልጿል።

በሁለት ተከፍለው ለረዥም ግዜ ሲወዛገቡ ከነበሩት የህወሓት ቡድኖች መካከል የሆነው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ክንፍ አስቀድሞ ሲገልፀው እንደነበረ አዲስ ፓርቲ በመመስረት፥ በሌላ መንገድ ወደ ትግራይ ፖለቲካ ተቀላቅሏል። ትላንት የተሰራጨ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ ምስክር ወረቀት እንደሚያሳየው፥ በእነ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን ዴሞክራሲ ስምረት ትግራይ የሚል ስያሜ የተሰጠው ፖርቲ መስርቶ ግዚያዊ የምዝገባ ፍቃድ ማግኘቱ ተገልጿል። የቀድሞ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጨምሮ በርካታ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች የያዘ መሆኑ የተገለፀው ይህ በአህፅሮት ስምረት ተብሎ የሚጠራው ፓርቲ፥ በትግራይ እንዲንቀሳቀስ የክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ ፍቃድ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓመተምህረት ማግኘቱ ተመላክቷል። 

 

አዲሱ ፓርቲ ስምረት ይፋ ባደረገው የማሕበራዊ መገናኛ ገፁ በኩል እንዳለው፥ ሰላምና ድህንነት የሰፈነባት፣ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት፣ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ የዜጎች ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ የሚከበሩባት ትግራይ ለመገንባት ሁሉም የትግራይ የማሕበረሰብ ክፍል ከጎናችን ተሰለፍ ብሏል። በቅርቡም በመላው የትግራይ አካባቢዎች እና በተለያየ የዓለም ክፍል አባላት እና ደጋፊዎች እንመዘግባለን ሲል አዲሱ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ አስታውቋል። ህወሓት ለማሻሻል እና በትግራይ ያለው የለውጥ ፍላጎት ለመምራት ሰነዶች ስናዘጋጅ ቆይተናል ያሉት ከፓርቲው ምስረታ አስተባባሪዎች መካከል የሆኑት የቀድሞ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባል አቶ ረዳኢ ሓለፎም፥ ህወሓት የማሻሻል እና ማዳን ጉዳይ የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር በአዲስ ፓርቲ ለመምጣት መቻላቸው ለዶቼቬለ ገልፀዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ለረዥም ግዜ በህወሓት ላይ በተለይም ከምዕራባውያን ይቀርብ የነበረ ትችት የሚመልስ ጭምር ነው ብለውታል። ከዚህ በተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ማእከሉ ትግራይ አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ እንዲሁም [በቅርቡ] 'ከክረምት በፊት'  መስራች ጉባኤው እንደሚያደርግ አቶ ረዳኢ ሓለፎም ለዶቼቬለ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠዉ ጊዚያዊ ፈቃድ መሠረት የፓርቲዉ መሥራቾች የፓርቲዉን መስራች ጉባኤ ማድረግና ሌሎች መሥፈርቶችን ማማላት አለባቸዉ።ምስል፦ National Election Board of Ethiopia

በሌላ በኩል አሁን አዲስ ፓርቲ ከመሰረተው ቡድን ጋር ውዝግብ ውስጥ የቆየው በእነ ዶክተር ደብረፅዮን የሚመራ የህወሓት ቡድን፥ በሕጋዊ እውቅናው ማግኘት ጉዳይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየተወዛገበ ያለ ሲሆን፥ የሚጠበቁበት ግዴታዎች አልተወጣም በማለት ደግሞ ባለፈው ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓመተምህረት ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለፁ አይዘነጋም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW