የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ሙሀማዱ ቡሀሪ ሲታወሱ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 12 2017
ከወታደራዊ መሪነት እስከ ዝግተኛው ሽምግልና
አንዴ በወታደራዊ ኹንታነት ሌላ ጊዜ ደግሞ በሲቪል ደንብ ናይጀሪያን በፕሬዝደንትነት የመሩት መሀማዱ ቡሀሪ ለህክምና በሄዱበት ብሪታንያ ባሳለፍነው ሳምንት እሑድ ይህቺን ዓለም ተሰናብተዋል። 82 ዓመታቸው ነበር። የናይጀሪያ የቀድሞው መሪ ምንም እንኳ ሞት ለማንም የማይቀር ቢሆንም የመጨረሻ ዕድሜ ዘመናቸውን በትውልድ ሀገራቸው ሳይሆን በቀድሞ የናይጀሪያ ቅኝ ገዢ ብሪታንያ ያውም ክሊኒክ ውስጥ መጠናቀቁን እንደ ብሔራዊ ውርደት የቆጠሩት አሉ። የናይጀሪያ ፓርቲዎች መማክርት ምክር ቤት ሊቀመንበር ዩሲፍ ዳንታሌ፤ ቡሀሪ ናይጀሪያን የተሻለች መኖሪያ ለማድረግ ጥረት እንዳደረጉ ቢናገሩም ጉድለቶችም እንደነበሯቸው አልሸሸጉም። እሳቸው ይበልጥ የቆጫቸው ግን የአዛውንቱ የቀድሞው የናይጀሪያ መሪ በሰው ሀገር ሕይወታቸው ማለፉ ይመስላል።
«ናይጀሪያን በምድር ላይ ለመኖሪያ ምርጥ ቦታ ስለማድረግ የሚያምን ሰው ነበር። እንደ ወታደራዊ የሀገር መሪ እና በዲሜክራሲያዊ መንገድ ሁለት ጊዜ እንደተመረጠ ሲቪል የናይጀሪያ ፕሬዝደንትም ያንን ሞክሯል። አዎን ልክ እንደሌሎች ሰዎች ጉድለቶች ነበሩት፤ ግን በጥቅሉ ሞክሯል፤ ነፍሱ በሰላም ትረፍ። ሆኖም ግን ስለመሪዎቻችን በጣም የሚያሳፍረኝ አንድ ነገር አለ፤ የበፊት መሪዎቻችን አገልግሎታቸውን ሲጨርሱ በውጭ ሀገር ይኖራሉ፤ ህክምናም በውጪ ያደርጋሉ። ለእኔ ይህ አሳፋሪ ነው። እነዚህ ሰዎች እኮ ናቸው ናይጀሪያን አስተካክለው የተሻለ ነገር የመሥራት ዕድሉ የነበራቸው። ምክንያቱም የመሪዎቻችን በውጭ ሀገር መሞትና አስከሬናቸው ብቻ ወደ ሀገር ቤት መመለሱ፤ በዚያ ላይ ሀኪም ቤት ሳይሆን ክሊኒክ ውስጥ መሞታቸው ብሔራዊ ውርደት ነው።»
በናይጀሪያ ታሪክ በጎርጎሪዮሳዊው 1983 ታኅሣሥ ወር በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን የፕሬዝደንት ሼኹ ሻጋሪን መንግሥት ያስወገደው መፈንቅለ መንግሥት አማካኝነት እስከ 1985 ዓም ድረስ ሜጀር ጀነራል መሀመዱ ቡሀሪን የሀገሪቱ መሪ አደረገ። ሆኖም የቡሃሪ አመራር በአስተዳደሩም ሆነ በኤኮኖሚው ረገድ ያደረገው የረባ ማሻሻያ ባለመኖሩ በጀነራል ኢብራም ባባንጊዳ እሳቸውም በፋንታቸው ከሥልጣን ተፈነቀሉ።
ሙስና እና ኤኮኖሚን በሚመለከት የወሰዷቸው ያልተሳኩ እርምጃዎች
ቡሃሪ በሥልጣን ዘመናቸው ሕገመንግሥቱን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማገድ የሙስና አሰራርን ለመቀነስ ሞክረዋል፤ እንደውም በዚህ የሥልጣን ቆይታቸው ያለ ፍርድ ቤት ውጣ ውረድ 500 የሚሆኑ ሰዎችን ከሙስና እና ግብር ከመሰወር ጋር በተገናኘ ወደ ዘብጥያ አውርደዋል። በሥርዓተ አልበኝነት ላይ ጦነርት ከፍተዋል በመባል የሚወራላቸው ቡሀሪ አርፍደው ወደ ቢሮ የመንግሥት ሠራተኞች በይፋ እንዲያጎነብሱ እስከማድረግም ደርሰዋል። በአንጻሩ ጀነራሉ ቡሀሪ ትችት የማይታገሱ እና የፕረስ ነጻነት የገደቡም ነበሩ። የኖቤል ተሸላሚው ሎሬት ወሌ ሾይንካ በዚያን ወቅት ናይጀሪያውያን ፍርሃትን ባስከተለባቸው በጠንካራ አገዛዝ ሥር እንደነበሩ በአንድ ወቅት ገልጾታል። እናም የቡሀሪ የመጀመሪያው የናይጀሪያ መሪነታቸው እንዳጀማመሩ በመፈንቅለ መንግሥት ነው የተጠናቀቀው።
ዳግም ወደ ሥልጣን
እንዲያም ሆኖ ቡሀሪ በድጋሚ ወደ ናይጀሪያ የሥልጣን መንበር የመመለስ ዕድል አግኝተዋል። በጎርጎሪዮሳዊው 2015። ቡሀሪ እስከዛሬ በናይጀሪያ የምርጫ ታሪክ ሚዛናዊ ተብሎ በሚነገርለበት በተጠቀሰው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ጉድላክ ጆናታንን አሸንፈው ነው በድጋሚ ፕሬዝደንት የሆኑት። በወቅቱ የቀድሞ ፈላጭ ቆራጭ ወታደራዊ ጀነራል ተመልሶ ፕሬዝደንት መሆኑን አልወደዱትም ነበር። በተቃራኒው በርካቶች ታጣቂ ቡድኖችን አደብ ያስገዙልናል የሚል ተስፋ ማድረጋቸው ግን አልቀረም። ለዚህም ነው ዩሱፍ ዳንታሌ ናይጀሪያን የተሻለች ሀገር ለማድረግ የሞከሩ ሲሉ የተናገሩት። የዲጂታል ይዘቶች አቅራቢው ሸሪፍ አንሱ ግን፤ መሃማዱ ቡሀሪ በተለያዩ ሁለት የሥልጣን ዘመናቸው በተለይም ለናይጀሪያ ባበረከቱት አትተዋጽኦ የሚመሰገኑበት የሚወቀሱበትንም ውርስ ትተው አልፈዋል ነው የሚላቸው። አቡጃ ናይጀሪያ የሚኖሩት የሰብአዊ መብቶት ተሟጋቹ ኦሞይሌ ሶዎሬ በቡሀሪ ዘመን ተፈጽሟል ያሉትን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።
«ስለናይጀሪያ የዴሞክራሲ ጭለማ ዓመታት ሲነገር በሀፍረት እያስተጋባ የሚሰማው የቀድሞው ፕሬዝደንት ሙሀማዱ ቡሀሪ ስም ነው። የመጀመሪያው ዛራ ውስጥ የሺያቶች የጅምላ ግድያ ነው። ይህ የተፈጸመው በእሳቸው እይታና ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሥር በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ,ም ሲሆን፤ ከ300 የሚበልጡ ያልታጠቁ የሺያ ሙስሊሞች ዛራ ውስጥ ተጨፈጨፉ። ወንዶች፤ ሴቶች፤ ሕጻናት ጭምር። ወንጀላቸው ጥቂት ወታደሮችን መቃወማቸው ነበር። በጎርጎሪዮሳዊው 2020ም እንዲሁ የፖሊስን የጭካኔ ድርጊት የተቃወሙ ናይጀሪያውያን ወጣቶች በቡሀሪ ወታደሮች ተገድለዋል። እናም ይህ አይረሳም፤ ይቅርም አይባልም። ቡሀሪ የጎሳዎች ጠላት ነበር። የሕግ የበላይነት ላይ ንቀት ነበረበት። የፍርድ ቤት ትዕዛዛትንም አያከብርም ነበር። የሚቃወሙትን ተገደው እንዲጠፉ ያደርግ ነበር።»
ከወታደራዊ ጀነራልነት ወደ ሲቪል ፕሬዝደንትነት የተሸጋገሩት ቡሀሪ እራሳቸውን ወደ ዴሞክራትነት የተለወጡ አድረገው ይገልጹ እንደነበር ይነገርላቸዋል። ያኔም አለባበሳቸውን ሳይቀር ቀይረው፤ «ከማንም ወገን አይደለሁም፤ ሆኖም የሁሉም ወገን ነኝ» የሚለው አነጋገራቸው ለደጋፊዎቸውም ሆነ ለተቺዎቻቸውየሚተላለፍ መልእክት ነበር። እንዲያም ሆኖ ብዙም ለውጥ ያልታየበት አስተዳደራቸው የመገናኛ ብዙኃን ርዕሰ ጉዳይ እየሆነ «አዝጋሚው ባባ» የሚል ቅጽል ተሰጠው። ሚኒስትሮቻቸውን ለመሾም ስድስት ወራት ነበር የወሰደባቸው። ፀረ ሙስና እንቅስቃሴዎቻቸውም ትርጉም ያለው ፍሬ አላፈሩም።
የመገናኛ ብዙኃን ባለቤት የሆነችው ኦሳሱ ኢግቢንዲዮን ኦግዋቺ ስለቡሀሪ አስተዋጽኦ እንዲህ ነው የገለጸችው።
«ናይጀሪያውያን አስተዳደሩን በወታደራዊ ዓይነት ሥርዓት እና የግል ቁርጠኛነት ያረጋጋል ብለው ጠብቀው ነበር። ሆኖም ግን ልክ እንደሌሎቹ አስተዳደሮች፤ የእሱም ዘመነ ሥልጣን ስኬቶችና ተግዳሮቶች ነበሩት። ጎልቶ የወጣው በእሱ የፕሬዝደንትነት ዘመን በብሔራዊ ደረጃ ስለ አመራር ተጠያቂነት፤ ወጣቶችን ስለማካተት እና ለበለጠ ውጤታማነት እና ዲሞክራሲያዊ ሥርአቶችን መልሶ የማዋቀር አስፈላጊነት መነጋገሪያ ሆነ። እነዚህ ችላ የማንላቸው ውይይቶች ናቸው። በናይጀሪያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጥልቀት እንደሚያምን ሰው፤ የእሳቸው ውርስ በዚህ ረገድ የበለጠ መደረግ እንዳለበት እና በውሳኔ ሰጪነት ክፍል ውስጥ አዳዲስ ድምፆች እንደሚያስፈልጉ እንደማሳሰቢያ ይታየኛል።»
ከፉላኒ ጎሳ የተገኙት ጠንካራው ሙስሊም አማኝ ቡሀሪ በጎርጎሪዮሳዊው 1947 ታኅሣሥ 17 ቀን ነው በሰሜናዊ ናይጀሪያ ካትሲና ግዛት የተወለዱት። በ20 ዓመታቸው ወታደር የሆኑት ቡሀሪ በሽምግልና ዘመናቸው ለዓመታት በህመም መቆየታቸው ከመነገሩ በቀር ምክንያተ ሞታቸው አልተነገረም። በፖለቲከኛነታቸው ብዙም ባይታወቁም በግላቸው ግን ታማኝ እንደነበሩ ተመስክሮላቸዋል። ሁለት ጊዜ ያገቡት ቡሀሪ 10 ልጆችን አፍርተዋል።
ሸዋዬ ለገሠ/ፕሪቪሌጅ ሙሳቫንሂሪ
ማንተጋፍቶት ስለሺ