የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በተቃዋሚዎቻቸው አንደበት
እሑድ፣ ነሐሴ 14 2015
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ 11 ዓመት ሊሞላ ጥቂት ቀናቶች ቀርቶታል። ይሁንና በዛሬዉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ አዉድ በክፍ የሚኮንኗቸዉ እናዳሉ ሁሉ እጅጉንም የሚያሞግሷቸዉ ጥቆቶች አይደሉም። ለመሆኑ መለስ በህይወት እያሉ በፖለቲካ ፓርቲ ማዕቀፍ ውስጥ ይቃወሟቸው የነበሩ ሰዎች ዛሬ እንዴት ያስታውሷቸዋል ? ኢትዮጵያ አንድ ዓመት ከጠ/ሚ መለስ ሞት ወዲህ
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ፤ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው በይፋ ከተገለጸ 11 ዓመት ሊሞላው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተዋል። መለስ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን በነበሩባቸው ዓመታት በሀገሪቱ ማህበረ ፖለቲካ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት የመሪነት ሚና ላይ ደጋፊዎቻቸውም ሆኑ ተቃዋሚዎቻቸው በተለያየ መንገድ ይገልጿቸዋል። አቶ መለስ ዜናዊ ካለፉ 11 ዓመታትን አስቆጠረ ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ በሀገሪቱ ቀውስ ያስከተ የተመሰቃቀለ ፖለቲካዊ ሁኔታን ጨምሮ ጨምሮ በርካታ ነገሮች ተለዋውጠዋል። ለመሆኑ ከዚሁ ሁሉ ጊዜ በኋላ እርሳቸው በህይወት እያሉ በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ሆነው ይቃወሟቸው የነበሩ አንጋፋ ፖለቲከኞች ዛሬ ስለ አቶ መለስ ምን ይሉ ይሆን ሲል ዶይቼ ቬለ ጠይቋል።
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከየኢትዮጵያፌደራላዊዴሞክራሲያዊአንድነትመድረክ ፓርቲ አመራር አንዱ ነበሩ ። በአንድ ዩኒቨርሲቲም የአንድ ዘመን ተማሪዎች እንደነበሩ ይናገራሉ ።
« እኛ እንዲያውም በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አንድ ባች ነበርን ። ኢንተለጀንት ነው ብዙ አንብቧል። ግን ደግሞ የዲክታተርነት ባህሪው ገደብ የለውም ። ሁለቱ ነው እንግዲህ ባላንስ የሚደረገው ፤ ኢንተለጀንት ነው ምንም ጥያቄ የለውም »
መለስ በግል የነበራቸውን የግል ችሎታ ዶሞክራሲዊ ሀገር ለመገንባት አልተጠቀሙበትም የሚሉት መረራ ፤ መለስ ምንም እንኳ አምባገነን ቢሆኖም ሀገር በቀውስ ውስጥም ሆና አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የተሻለ ስራ መስራታቸውን ይመሰክራሉ ።የአቶ መለስ ዜናዊ ዉርስና ቅርስ
«አምባገነናዊ ስረዓቶች ደረጃ አላቸው ሙሉ በሙሉn አፍኖ ለመያዝ ለመቆጣጠር ብዙ ነገሮችን ለማድረግ የሚሳካላቸው አሉ በተወሰነ ደረጃ ለጊዜው ወይም ደግሞ ሳይሳካላቸው በአችር ጊዜ ውስጥ ቀውስ ውስጥ የሚገቡ አሉ ። ስለዚህ እርሱ የመራው ስረአት 27 ዓመታት በቀውስጥ ውስጥም ቢሆን ቀውሱን የመቆጣጠር እና አምባገነናዊ የፖለቲካ ስረዓቱን ለማስፈን ከሞላጎደል አሁን ካለው ሁኔታ የተሻለ ስራ ሰርቷል።»
በወቅቱ እዚያው መድረክ ፓርቲ ውስጥ ከአመራሩ አንዱ የነበሩት አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕሬፌሰር በየነ ጴጥሮስ አቶ መለስን እንዴት ያስታውሷቸው ይሆን ?
« በመሰረቱ በቂ ብቃት ያላቸው ሰው ናቸው እሱ ላይ ምንም ጥርጣሬ አይኖርም ። እና ሃሳቦችን አርቲኩሌት የማድረግ ያመኑበትን መስመር ሌላው እንዲቀበል የሚያቀርቡት መከራከሪያም ሆነ የሚወስዱት ጊዜ ያንን ጉዳይ እሳቸው ያሉበት ሌላውም እንዲደርስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የዋዛ አልነበረም።»
ሰማያዊ ፓርቲ ተብሎ ይታወቅ የነበረ በርካታ ስመ ጥር የፖለቲካ ሰዎችን አሰባስቦ በነበረው ፓርቲ ውስጥ የነቃ እስከ ኃላፊነት የዘለቀ የነቃ ተሳትፎ የነበራቸው አቶ ወሮታው ዋሴ አቶ መለስን ከኢትዮጵያ አንጻር ሲገልጹ
« ማውራት ስለማልፈልግ ብዙ ጊዜ ፤ ከየት ወዴት ወሰዷት ካልክ ከቆመችበት ወደ ድምጥማጥ እንደዚህ ነው የምገልጻቸው ። በግል አላውቃቸውም ። ምንም የሚያቀራርበንም ነገር ስላልነበር ማለት ነው። የፖለቲካ መገለጫ ስብዕናቸውን ካልከኝ ግን ቅድም ያልኩት ነው ። »
የመለስ አድናቂ እንዳልነበሩ የሚናገሩት ደግሞ በትግራይ የተቃውሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ስማቸው ጎልቶ የሚሰማው የዓረና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዐምዶም ገብረስላሴ ናቸው ።
« እኔ የመለስ አድናቂ አይደለሁም ። ነገር ግን ከኢትዮጵያ መሪዎች አንጻር ሲታይ አቶ መለስ ያው በግላቸው ጠንካራ መሪ ናቸው ሊባል ይችላል። »የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሙት ዓመት
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ቅብብሎሽ ታሪክ በየዘመኑ የነበሩ መሪዎች ዛሬ በሀገሪቱ ውስጥ ለተፈጠሩ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ ሚና እንደነበራቸው በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ አስተያየታቸውን ያካፈሉን እነዚሁ ፖለቲከኞች ይናገራሉ ። አቶ አምዶም ዛሬ በሀገሪቱ ለተፈጠረው ችግር ተተኪ ሰው ባለማዘጋጀታቸው የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር ይተቻሉ ።
« የአቶ መለስ ዋነናው ችግር የተተኪ መሪ ኢህዴግ ላይ እና ህወሃት ላይ ሳይተኩ መሄዳቸው ነው ወይም ማለፋቸው ነው ። በኢትዮ ኤርትራ የነበራቸው አቋምም በተለይ ጦርነቱ እንዳይቋጭ ለዛሬ ጦርነት ከትግራይ ህዝብ አንጻር ሲታይ ዛሬ ላጋጠው ጭፍጨፋ እና የዘር ማጥፋት የሚባለውን የእርሳቸው የመሪነት ክፍተት ወይም የግል ስልጣን ማስቀደም የወለደው ነው ማለት እንችላለን።»
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አንድ አፍታ መለስን ሲያስታውሱ ውለታቸው መዘንጋት የለበትም ይላሉ ።ኢትዮጵያ ከመለስ በኋላ
«እኔ አንድ ውለታ ትተው ያለፉት የምለው የፈለገውን ያህል በርዕዮተ ዓለም ብለያቸውም ብቃታቸው ተጠቅመዋል። ምናልባትም ለኢትዮጵያ እንደ ቅርስ ሊወሰድላቸው ይችላል፤ አዲስ አበባ ትራንስፎርም ሆኗል። »
በየቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ 11 ዓመት ቢሞላቸውም የሙት ዓመት መታሰቢያ ቀናቸው ሲደርስ መታሰባቸው አይቀርም ። ደጋፊዎቻቸውም ሆኑ ተቃዋሚዎቻቸው በየፊናቸው ማስታወሳቸው አይቀርም ። ከሁለት አስርት ዓመታት ለተሻገ ጊዜ ኢትዮጵያን የመሩ ሰው የመሪነት ውጣ ውረድን ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ ከፖለቲከኛው ባሻገር ህዝቡ እንዴት ያስታውሳቸው ይሆን ?
ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ