1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ አስፈትቶ ወደ መደበኛ ኑሮ መመለስ መጀመሩ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 18 2017

በትግራይ ክልል 17 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት እና ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ሥራ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ DDR መከወኑን ብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን አስታወቀ።

በትግራይ ክልል የቀድሞ የትግራይ ኃይሎች ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደመደበኛ ሕይወት የማስገባቱ ሥራ
በትግራይ ክልል የቀድሞ የትግራይ ኃይሎች ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደመደበኛ ሕይወት የማስገባቱ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።ምስል፦ Million/DW

የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ አስፈትቶ ወደ መደበኛ ኑሮ መመለስ መጀመሩ

This browser does not support the audio element.

 

 በክልሉ በፖለቲካዊ እና ከትጥቅ ርክክብ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ተቋርጦ ነበር የተባለው የቀድሞ ተዋጊዎችን የተሃድሶ ስልጠና ሰጥቶ ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሂደት የመጀመርያ ዙር እስከ ሰኔ ወር ድረስ እንደሚጠናቀቅ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን ኮምሺነር ተመስገን ጥላሁን ለዶቼቬለ ገልፀዋል። በትግራይ በኩል የዲዲአር መርኀግብሩን ጨምሮ ሁሉም የፕሪቶርያ ስምምነት ይዘቶች በምሉዕነት እንዲፈፀሙ ጥሪ ይቀርባል። 

በትግራይ ክልል በመጀመርያ ዙር ለ75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎች የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ታቅዶ፥ ባለፈው ኅዳር ወር አጋማሽ በብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን ተጀምሮ የነበረው እንስቅስቃሴ ብዙ ሳይዘልቅ ለወራት ተቋርጦ መቆየቱን ኮምሽኑ ይገልፃል። የብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን ኮምሽነር ተመስገን ጥላሁን ለዶቼቬለ እንዳሉት በትግራይ የነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲሁም ከትጥቅ ርክክብ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ተጀምሮ የነበረው የዲዲአር ሥራ ተደናቅፎ ቆይቷል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን ኮምሽነር ተመስገን ጥላሁን «በትግራይ ክልል በወቅቱ የነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለሥራችን ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ነበረ። ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞ ተዋጊዎች መረጃ ማጥራት፣ ከትጥቅ ርክክብ እና የትጥቅ ሁኔታ ማደራጀት ጋር ተያይዞ ማጥራት ያለብን ጉዳዮች ስለነበሩ በዚሁ ምክንያት ልናቋርጥ ተገደን ነበረ። እስከ ተቋረጠበት ታኅሣስ ወር መጨረሻ ድረስ ስምንት ሺህ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች በሂደቱ አልፈው ነበር» ብለዋል።

በትግራይ ክልል በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት እየተከወነ ያለው ይህ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ እንቅስቃሴ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ በያዝነው ወር መጀመርያ ዳግም ቀጥሏል።  እስካሁን ባሉ መረጃዎችም 17 ሺህ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ተዋጊዎች ትጥቅ ፈትተው፣ በተሃድሶ ስልጠና አልፈው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውን ብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን ገልጿል። 

ኮምሽነር ተመስገን ጥላሁን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በትግራይ ዳግም በተጀመረው ዲዲአር፥ በመቐለ እና ዕዳጋሓሙስ የሚገኙ ማእከላት በየቀኑ 350 የቀድሞ ተዋጊዎች ተቀብለው የተሃድሶ ስልጠና እየሰጡ ነው ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ከሠራዊት ማሰናበት እና ትጥቅ መፍታት ጋር በተገናኙ የተለያዩ ሀሳቦች የሚሰነዘሩ ሲሆን፥ ዲዲአር ጨምሮ ሁሉም የፕሪቶርያ ውል ይዘቶች ሊፈፀሙ እንደሚገባም በአስተዳደር አካላት በተደጋጋሚ ይገለፃል። ተቋርጦ የነበረው የዲዲአር ሂደት ዳግም በጀመረበት ስነስርዓት ለመገናኛ ብዙኀን ተናግረው የነበሩት የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሐላፊ ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ፥ የፌደራሉ መንግሥት ሙሉ የፕሪቶርያ ስምምነት ይዘት መፈፀም አለበት ብለዋል። 

ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ «ዲዲአር ብቻ የስምምነቱ ሙሉ መገለጫ አይደለም። ሉአላዊ ግዛታችን ሊመለስ፣ ሕዝባችን ወደቀዬው ሊገባና መደበኛ ኑሮውን ሊኖር ይገባል። ይህ የሚቀጥለው በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የሚፈፀም ከሆነ ነው» ብለዋል።

በጎርጎሪዮሳዊው 2023 ግንቦት ወር በተመሳሳይ ትጥቅ የማስፈታት ሥራ መከናወኑ በተገለጸበት ወቅት ከታዩ መሣሪያዎች በከፊልፎቶ ከማኅደርምስል፦ Million Hailessilasie/DW

በሌላ በኩል በመቐለ እና ዕዳጋ ሓሙስ ወዳሉ የተሃድሶ ማእከላት ገብተው ከወጡ የቀድሞ ተዋጊዎች እንደተረዳነው፥ የተሃድሶ ስልጠናውን ሲያጠናቀቁ ለእያንዳንዳቸው 90,400 ብር ተሰጥቷቸዋል። በትግራይ ሥራ ላይ ካሉ ሁለት ማዕከላት በተጨማሪ፥ በዓዲበራኽ ሌላ የተሃድሶ ማዕከል በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምርም ይጠበቃል።

ከትግራይ ክልል ውጭ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን በአፋር፣ኦሮሚያ እና አማራ ክልል የነበሩ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ማድረጉን የሚገልፅ ሲሆን፥ በአፋር ክልል የነበሩ ከ1,700 በላይ የአፋር ፌደራሊስት ሐይሎች ታጣቂዎች፣ በኦሮሚያ ከ5,000 በላይ «ሸኔ» የተባሉ ተዋጊዎች እንዲሁም በአማራ ክልል በሽምግልና የገቡ የተባሉ «የፋኖ» ታጣቂዎች በተለያዩ ማዕከላት የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲመለሱ ማድረጉን የተሃድሶ ኮምሽኑ ጨምሮ ይገልፃል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት፣ የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ በአራት ምዕራፎች በሁለት ዓመት ለመከወን ማቀዱን የሚገልፀው ብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን፥ ከዚህ መካከል ከፍተኛ ቀጥር የሚይዘው በትግራይ ክልል ያሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን የተሃድሶ ስልጠና ሰጥቶ ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ተግባር ገና በአንደኛ ዙር ላይ ያለ ሲሆን፥ ይህን የመጀመርያ ዙር ሥራ በመጪው ሰኔ ለማጠናቀቅ መታቀዱም ተገልጿል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW