1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

የኦሮሚያው ግጭት፡ የቀድሞ ተዋጊዎች የታህድሶ ስልጠና

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 11 2016

በኦሮሚያ ክልል በትጥቅ መንግሥትን ሲወጉ ነበር የተባሉ ከ1, 500 በላይ ታጣቂዎች የሁለት ወራት የታህድሶ ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ። ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ የኦነግ-ሸነ አባላት ነበሩ ያላቸው ታጣቂዎቹ ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉት ለፈጸሙት ጥፋት ይቅርታ ተደርጎላቸው ነው ብሏል።

በኦሮሚያ ክልል የገጠር ከተማ
በኦሮሚያ ክልል የገጠር ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያው ግጭት፡ የቀድሞ ተዋጊዎች የታህድሶ ስልጠና

This browser does not support the audio element.

ሰላምን መርጠው ከጥፋት ድርጊታቸው የተጸጸቱ የተባሉት

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በትናንት ማምሻው መግለጫው ይቅርታ ተደርጎላቸው የታህድሶ ስልጠናውን በመውሰድ ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የተደረጉት የቀድሞ ተዋጊዎች፤ ህዝብን ሲያሰቃዩና ንብረት ሲያወድሙ የነበሩ፤ በዚህ ድርጊታቸው የተጸጸቱ ናቸው ብሏል። የሁለት ወራት የታህድሶ ስልጠናውን አጠናቅቀው ትናንት ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉት ቁጥራቸውም 1,521  ናቸው ያለው የክልሉ መንግሥት መግለጫ፤ ስልጠናውን የወሰዱ የቀድሞ ታጣቂዎቹ ሕይወት የማጥፋት፣ አስገድዶ መድፈር እና የማኅበረሰቡን ንብረት ከማውድም ከባድ ወንጀል ተመልሰው ሰላምን የመረጡ ናቸው ይላል።

የኦሮሚያክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ይህንኑን በማስመልከት ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ወደ ታህድሶ ገብተው ስልጠናውን ለሁለት ወራት የተቀላቀሉት የቀድሞ ተዋጊ ወጣቶቹ ወደ ሰላማዊ መንገድ የተመለሱት በሁለት መንገድ ነው ብለዋል።

አቶ ኃይሉ «በተሳሳተ መንገድ ሽብርተኛውን ቡድን የተቀላቀሉ» ያሏቸውን እነዚህ የታህድሶ ስልጠና ወስደው ኅብረተሰቡን ተቀላቅለዋል የተባሉትን ወጣቶች አንድም «የያዝነው መንገድ ትክክል አልነበረም ብለው ተጸጽተው የተመለሱ በሌላ በኩል ደግሞ በውጊ ተማርከው ሃሳባቸውን ወደ ሰላም ለማምጣት ፈቃደኛ የሆኑ» ናቸው ብለዋል። ታህድሶ የወሰዱት ወጣቶች «ኅብረተሰቡ ላይ በፈጸሙት ተግባር የተጸጸቱ ናቸው» ያሉት ኃላፊው  አሁን ወደ ማኅበረሰቡ ለተቀላቀሉት የአገር ኢኮኖሚ በፈቀደ መጠን የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ ደረጋል ነው ብለዋል።

በርግጥ ስለቀድሞ ታጣቂዎቹ የተሃዲሶ ስልጠና መውሰድ ከሌላኛው ወገን ማለትም መንግስት ሸነ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ካለው የታጠቀ ቡድን አስተያየት ማግኘት አልተቻለም። ቡድኑ ስለክልሉ መንግሥት መግለጫም እስካሁን ያለው ነገር የለም።

የኦሮሚያ ክልል ምስል DW

የቀጠለው የሰላም እጦት እና የነዋሪዎች ስጋት

እንዲያም ሆኖ ግን በኦሮሚያአሁንም በተለያዩ አከባቢዎች ውጊያና አለመረጋጋቱ መኖሩን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። በቅርቡ ከጉጂ ዞን ወደ ምሥራቅ ቦረና በመግባቱ ውዝግብ ከተነሳበት ጎሮዶላ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ነዋሪ ከሁለት ቀናት በፊት በወረዳው ቀረሮ በሚባል ቀበሌ ታጥቀው በጫካ በሚንቀሳቀሱ አካላት እና በመንግሥት ጦር መካካል ከባድ ውጊያ እንደነበር ነግረውናል።

ከቄሌም ወለጋ ሃዋ ገላን ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው ነዋሪ በፊናቸው አሁን ላይ በአካባቢው ውጊያ ባይስተዋልም ኅብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች በግጭቱ ዳፋ ይሰቃያል ብለዋል።  

በኦሮሚያው ግጭት ኅብረተሰቡ ከሚሰጠው አስተያየት በተጨማሪም የአገር መከላከያ ሠራዊት በየጊዜው በሚያወጣቸው መረጃዎች በታጣቂዎች ላይ ሰፊ ወታደራዊ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ያወሳል።

ዶይቼ ቬለ በኦሮሚያ አሁንም መቋጫ ስላላገኘው ጦርነት እና ዘላቂ እልባቱን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረበላቸው የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ ኃይሉ አዱኛ ግን፤ «እኛ እንግዲህ አሁን በሰላማዊ መንገድ የሚያታግል የፖለቲካ ምህዳር አለ ብለን ነው የምናምነው። ጫካ የሚያስገባ ሁኔታ የለም ብለን እናምናለን። ለዚያም እንዲረዳ መንግሥት ሰላም የፈለጉ ታጣቂዎች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ሰላማዊ መንገድን እንፈልጋለን ካሉ የመንግሥት የሰላም እጆች አይታጠፉም።» በማለት መንግሥት ወደ ሰላም የሚመጡትን ታጣቂዎች በምሕረት የመቀበልና በዚያ መንገድ የማይመጡት ላይ ግን ወታደራዊ እርምጃውን ወደ ማጠናከሩ እንደሚገፋ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ጦር ካንድ ወር በፊት በታንዛንያ ያካሄዱት የሰላም ስምምነት መክሸፉን ተከትሎ በኦሮሚያ ውጊያ ስለመበርታቱ ይነገራል፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት ከመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት የአገር መከላከያ ሠራዊት ኢታማጆች ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዳመለከቱት ግን መንግስት ከታጣቂው ቡድን ጋር የሚያደርገው ውጊያ ወደ ሰላማዊ መንገድ ሊመጣ የሚችልበት ዕድል መኖሩን ጠቁመዋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW