1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀድሞ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባል ኢሕአዲግን ወቀሱ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 5 2010

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ለሃገር ውድመት እና ለበርካታ ሕዝቦች ሞት ተጠያቂ የሆኑ የመንግሥት አመራሮች ሕግ ፊት እንዲቀርቡ በኢትዮ-ኤርትራ በጦርነቱ የተዋጉ አንዳንድ የቀድሞ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ጠየቁ ።

Karte Äthiopien Eritrea Grenze Amharisch

«ኢሕአዲግ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ብዙ ደባዎችን ፈጽሟል»

This browser does not support the audio element.

                                                                                 

በባድመው ጦርነት በተለያየ አውደ ውጊያ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ምክትል አስር አለቃ አዲስ ኃይሉ እና በአሁኑ ወቅት በማሕበራዊ ድሕረገጾች ከፍተኛ ተሳትፎ የሚያደርጉት የፖለቲካ አክቲቪስቱ መስፍን ፈይሳ መንግሥት ከፍተኛ የሕይወት ዋጋ እና መሥዋዕትነት የተከፈለባቸውን ባድመን ጨምሮ በርካታ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸው የኢትዮጵያ የድንበር ከተሞች በአልጀርስ ሥምምነቱ እና በድንበር ኮምሽኑ ውሳኔ መሰረት ለኤርትራ ለመስጠት የደረሰበትን ውሳኔም በጥብቅ አውግዘዋል። 

ከባድ የሕይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት እና የንብረት መውደም የተከሰተበት በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ 70 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚገመት ሕዝብ ህይወቱን ያጣበት በወቅቱ ከ 275 ሺህ በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉበት የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብ 20 ዓመት ሞላው ።ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ውዝግቡ ዛሬም አላባራም:: ገዥው መንግሥት ኢሕአዲግ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአሁን ቀደም የሰረዟቸውን የቅኝ ግዛት ውሎች መሰረት ያደረገውን የአልጀርሱን ስምምነት በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መፈራረሙ እና በኋላም ይግባኝ በሌለው የድንበር ኮሚሽኑ ፍርድ ቤት መዳኘቱ ከግዛት ሉአላዊነቱ በርካታ አካባቢዎችን እንዲያጣ አድርጎታል ሲሉ የፖለቲካ ጠበብት ሲተቹ ቆይተዋል። የሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር እንዲሁም ሰላም እና ጦርነት አልባው መርህ በተለይም በጦርነቱ ቀጣና አካባቢዎች የልማት እድገት ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል የሚለው መንግሥት ለዘላቂያዊ ሰላም እና ብልጽግና ሲል ሙሉ ለሙሉ የአልጀርሱንም የድንበር ኮምሽኑንም ስምምነት እና ውሳኔ እንደሚቀበል ሰሞኑን አስታውቋል። ይህ ውሳኔ ደግሞ በሕዝቡም ሆነ በድንበር ውዝግቡ ወቅት የሃገርን ዳር ድንበር ለማስከበር በዘመቱ አንዳንድ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ዘንድ ተቃውሞን ቀስቅሷል። በስዊድን ነዋሪ የሆኑት ምክትል አስር አለቃ አዲስ ኃይሉ ሃገር ተወረረ የሚለውን ዜና እንደሰሙ ገና በአፍላ በ18 ዓመት እድሜያቸው በትግሉ ላይ ከተሰው ወንድማቸው ጋር ከምሥራቅ ሸዋ ሞጆ ከተማ ዘምተው በቡሬ ግንባር 12ተኛ ከፍለጦር 121ኛ ብርጌድን ተቀላቅለው በጥይት ጉዳት እስከደርስባቸው አስፈላጊውን መስዋዕትነት ከፍለዋል:: በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ደም የፈሰሰበት የብዙዎች አካል የጎደለበት ትዳር እና ጎጆ የፈረሰበት እንዲሁም ሕዝብ የተፈናቀለበት የሃገር ሉዓላዊነት ጉዳይ በቀላሉ መታየቱ እንዳሳዘናቸው ይገልጻሉ።

በአሜሪካ ሜኒሶታ ነዋሪ የሆኑት የቀድሞ የሃገር መከላከያ አባል እና የፖለቲካ አክቲቪስት አቶ መስፍን ፈይሳም በባድመው ጦርነት በነበረው የውጊያ አመራር አሻጥር ቆስለው ለምርኮ መዳረጋቸውን አስታውሰው ገዢው መንግሥት ኢሕአዲግ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ከሃገር እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ ብዙ ደባዎችን ፈጽሟል። የአልጀርሱ ስምምነት ውሳኔም አንዱ መገለጫ ነው ሲሉ ይተቻሉ።

ኢሕአዲግ አሁን የደረሰበትን ውሳኔ ከሃገር የግዛት ሉአላዊነት እና ከሕዝቦች መሰረታዊ መብቶች ጋር በማያያዝ ብዙዎች በበጎ ጎኑ አልተመለከቱትም ። ብዙ ዋሽተውናል የሚሉት ወንድማቸውን በጦርነቱ ያጡት የባድመው ዘማች ምክትል አስር አለቃ አዲስ ለሃገር ውድመት እና ለበርካታ ሕዝቦች ሞት ተጠያቂ የሆኑ የመንግሥት አመራሮች ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

የፖለቲካ ጠበብት ኢትዮጵያ የባድመን ጦር ድል ካደረገች በኋላ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያም ሆነች የዓለም መንግስታት ውድቅ ያደረጓቸውን ከጣልያን ጋር ጋር የተደረጉ ቀደምት አስገዳጅ የቅኝ ግዛት ሥምምነቶችን መሰረት ያደርጉትን የአልጀርስ ውል እና በኋላም ይግባኝ የሌለውን የድንበር ኮሚሽኑን የውሳኔ ስምምነት መፈራረማቸው እና መቀበላቸው ተገቢ እንዳልነበረ ይገልጻሉ። እ.ኤ.አ በ 1947 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ ከኢጣልያ ጋር የተፈራረመችውን የድንበር ውሎች ውድቅ ናቸው በማለት መሰረዙን እና የኢትዮጵያ መንግሥትም በ1952 ዓ.ም ባወጣው የነጋሪት ጋዜጣ ከጣሊያን ጋር የተደረጉት የድንበር ውሎች ውድቅ ናቸው የሚል አዋጅ መደንገጉ አይዘነጋም። በተመሳሳይ ጣሊያንም በኢትዮጵያ ከገጠማት ሽንፈት በኋላ ጎረቤት ሶማሊያን በመውረር ያቋቋመችው " ኢስት አፍሪካን ኢምፓየር " ሲፈርስ ቀደም ሲል ከኢትዮጵያም ጋር የተፈራረመቻቸው ማናቸውም ውሎች ውድቅ ናቸው ስትል መስማማቷን የፖለቲካ ምሁራኑ ይገልጻሉ። በመሆኑም በውሳኔዎቹ በርካታ ከተሞች ያጣችውን ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ለማድረግ ድንበሩ መካለል ያለበት የሕዝብ አሰፋፈርን ቀደምት ታሪክን መልክዕአ ምድራዊ አቀማመጥን እና የሃገሪቱን ዘላቂ ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅምን መሰረት አድርጎ እንጂ ኢትዮጵያም ሆነች ዓለም ውድቅ ያደርጓቸውን ቀደምት የቅኝ ግዛት ውሎችን ተመስርቶ መሆን የለበትም በማለት አሁን መንግሥት የደረሰበትን ውሳኔ ይተቻሉ።

 

እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW