የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች ስልጠና ማዕከላት መግባት ጀመሩ
ሐሙስ፣ ኅዳር 12 201775 ሺህ የትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማሕበረሰቡ ለመቀላቀል ትጥቃቸው ፈትተው ወደ ስልጠና ማዕከላት የሚገቡበት መረሃ ግብር ዛሬ ተጀመረ። የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት የደረሱት ስምምነትን ተከትሎ የተጀመረው ትጥቅ የማስፈታትና ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ህይወት የመመለስ ፕሮግራም በመጀመርያ ዙር ዛሬ 320 ስልጠና ማዕከላት ገብተዋል።
ብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን የሚመራው ይህ ሂደት 4 ወራት እንደሚቆይ እና በየቀኑ 320 ታጣቂዎች ወደ ስልጠና ማዕከላት እንደሚገቡ አስታዉቋል። በመቐለ፣ ዕዳጋ ሓሙስ፣ ዓድዋ እና ሌሎች አካባቢዎች በተቋቋሙ የስልጠና ማዕከላት የቀድሞ ተዋጊዎች ለሰላማዊ ህይወት የሚያስፈልጋቸው ስልጠና እንደሚያገኙ ተነግሯል።
የሁለት ዓመቱ ጦርነት ባስቆመ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት የተጀመረው የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎችወደ የተሃድሶ ማዕከላት የማስገባት ስራ፥ በተለያዩ ዙሮች እንደሚፈፀም የተገለፀ ሲሆን ዛሬ በመቐለ በይፋ በተደረገ ስነስርዓት በመጀመርያ ዙር በእጃቸው የነበረ ትጥቅ አስረክበው፣ ወደ ስልጠና ማዕከላት ገብተው፣ የማቋቋሚያ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደሰላማዊ ኑሮአቸው የሚገቡ የቀድሞ ተዋጊዎቹ የመቀበል መርሐግብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን ተካሂዷል።
በዚህ ዙር የተለያዩ የቀድሞ ተዋጊዎች በተመደቡላቸው የስልጠና ማዕከላት ማሕበራዊ እና ስነልቦናዊ ድጋፍ የሚያገኙበት እንዲሁም የስድስት ቀናት ስልጠናው ሲጨርሱ የፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደሰላማዊ ህይወት እንደሚቀላቀሉ የገለፁት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮምሽን ምክትል ኮምሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩርያ፥ በዚህ የተሃድሶ ስልጠናና ድጋፍ አስቀድሞ ተዋጊዎች የነበሩ አሁን ላይ ትጥቅ የፈቱ ሴት፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ተዋጊዎች እንዲሁም በአደረጃጀት ውስጥ ያሉ አመራሮች የተካተቱበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ዛሬ በመቐለ በተደረገ ስነስርዓት በእጃቸው የነበረ ቀላል መሳርያ የያዙ የቀድሞ ተዋጊዎች፥ በአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ታዛቢዎች ፊት ትጥቃቸው ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እያስረከቡ ወደ ተሃድሶ ማዕከላት ለስልጠና ተሸኝተዋል። በዚሁ መድረክ የተናገሩ የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሐላፊ ሌተናንት ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ በበኩላቸው የትግራይ ሐይሎች ለፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ታማኝ ናቸው፣ ለዚህም ትጥቃችን እያስረከብን ነው፣ በፌደራሉ መንግስት በኩል ሊወጣቸው የሚጠበቁ ሐላፊነቶች ይወጣ ብለዋል።
ሌተናንት ጀነራል ፍስሃ "ህዝባችን፣ ሁሉም ፀጥታ ሐይላችን ይሁን አመራሮች ሰላም ነው የሚሻው። ፈልጎ ያመጣው ይሁን የለኮሰው ጦርነት የለም። እኛም ከመከላከል ውጭ ያደረግነው ሀጥያት የለም። በቀጣይም ቢሆን ብቸኛ ፍላጎታችን ሰላም መሆኑ አምነን ነው የደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት የምናከብረው። ለሰላም ብለን እየከፈልነው ያለነው ዋጋ ግልፅ ነው።ለሰላም ህይወት ሰጥተናል፥ አሁን ደግሞ ትጥቃችን እየሰጠን ነው" ብለዋል። በአፍሪካ ሕብረት ውክልና የሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ተከታታይ ቡድን መሪ ጀነራል ስቴቨን ራዲና ሁለቱ የውሉ ፈራሚዎች ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እየሰሩ ነው ብለዋል።
ጀነራል ራዲና "ሁለቱ የፕሪቶርያም የሰላም ስምምነት ፈራሚ አካላት፥ ለስምምነቱ ተግባራዊነት መተማመን አላቸው" ብለዋል። ጀነራል ስቴቨን ራዲና፥ ዛሬ ላይ ከተረከቡ የግል መሳርያዎች ውጪ ከዚህ በፊትም የቡድን እና ከባድ የጦር መሳርያዎች ርክክብ መደረጉ ተናግረዋል። አሁን ላይ ወደሰላማዊ ህይወት እየተመለሱ ካሉት በተጨማሪ በርካታ የትግራይ ሐይሎች አባላት በቀጣይ ዙሮች ወደ ስልጠናው እና የድጋፍ ማዕቀፉ ሊገቡ ይጠበቃል ተብሏል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ