የቀጠለው የህወሀትና ፌደራል መንግሥት ውዝግብ
ሰኞ፣ ሰኔ 2 2017
ህወሓት የፕሪቶርያ ስምምነት እንዲፈፀም በተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረበ እንዳለ በመግለፅ የሚጀምረው የህወሓት መግለጫ፥ ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት የፈረመውን ውል ከማክበር በተቃራኒ ትግራይን የሁከት ማእከል ለማድረግ እና የትግራይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳያገግም የሚያደርጉ ክልከላዎች አጠናክሮ መቀጠል መርጧል በማለት ይከሳል። በፕሪቶርያ ውል መሠረት ታጣቂዎችን ከትግራይ መሬት ማስወጣት የሚጠበቅበት የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ወደጎን በማለት ታጣቂዎቹን በማጠናከር ላይ ይገኛል ሲልም ህወሓት በሳምንታዊ መግለጫው ጨምሮ ገልጿል። አያይዞም መቋጫ ያላገኘውን የተፈናቃዮች ጉዳይ ያነሳው ህወሓት፥ ታጣቂዎች አሁንም ተቆጣጥረዋቸው ካሉ አካባቢዎች በየጊዜው ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው፥ በየወሩ በአማካኝ ከ250 እስከ 300 የሚደርሱ ዜጎች ተፈናቅለው በሸራሮ በኩል መጥተው ወደ የተፈናቃዮች መጠልያ እንደሚገቡ አመልክቷል። በፌደራል መንግሥቱ ላይ በርካታ ክሶችን ያነሳው የህወሓት መግለጫ፥ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ለሸቀጦች መንገድ መዝጋት፣ ነዳጅ መከልከል፣ የኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዲቋረጡ ማድረግ እና ሌሎች ነጥቦች አንስቷል።
ጉዳዩን አስመልክተው ለህወሓት ልሳን ወይን የተናገሩት የህወሓት ሥራ አስፈፃሚኮሚቴ አባል አቶ ተኽላይ ገብረመድህን ከፕሪቶርያ ውል አፈፃፀም ጋር በተገናኘ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት፣ ለማስተካከል ከፌደራል መንግሥቱ ጋር መነጋገር እንደሚያስፈልግ በማንሳት፥ የአፍሪካ ሕብረት ፖነል ሊጠራ ይገባል ብለዋል።
አቶ ተኽላይ «የአፍሪካ ሕብረት ፓነል ቆሞ ነው ያለው። ይህ ስህተት ነው። አሁንም ቢሆን በአስቸኳይ ዳግም ሊቀጥል፣ ውይይት ሊደረግ ይገባል። የፕሪቶርያ ውል አብዛኛው ያላለቀ እና ጨርሶ ያልተሠራ በመሆኑ፥ ይህ ሊፈፀም ከሆነ መነጋገር መቻል አለብን» ብለዋል።
ከፕሪቶርያ የተኩስ ማቆም ስምምነት አፈፃፀም እንዲሁም ከተፈናቃየች ወደ ቀዬአቸው መመለስ ጋር በተገናኘ ህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚያወዛግቡ አጀንዳዎች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። በእነዚህ ጉዳዮች አንዱ ሌላውን ይከሳል። በዚህ መካከል በትግራይ የተፈናቃዮች ሁኔታ ከመጥፎ ወደከፋ ተሸጋግሯል። ግጭት እንዳይፈጠር በሕዝቡ ዘንድ ስጋት ተፈጥሯል፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው ተመሰቃቅሏል።
እነዚህ ህወሓት በሚያነሳቸው ክሶች እና ሌሎች ጉዳዮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ