የቀጠለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና የተመድ ዋና ጸሐፊ ማሳሰቢያ
ቅዳሜ፣ መስከረም 30 2019
በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ትናንት ዓርብ በቃል አቀባያቸው በኩል ባወጡት መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ ሶስት ክልሎች ዳግም የተቀሰቀሰው ግጭት በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ዋና ጸሐፊው ጦርነቱ የቀጣናውን መረጋጋት የበለጠ የሚያዳክም አደጋ የደቀነ ነው ሲሉ በማስጠንቀቅ፤ የኤርትራ ኃይሎች ኢትዮጵያ መግባታቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች መሰማቱ አሳሳቢ ነው ብለዋል። ጉቴሬስ ተፅዕኖ ያላቸው አገራት ፍጥጫውን ለማርገብ እና ግጭቱን ሊያባብስ ከሚችል ከማንኛውም እርምጃ እንዲቆጠቡም ጥሪ አቅርበው ዓለማቀፍ ህግ እንዲጠበቅ ጠይቀዋል፡፡
የአራትዮሹ ስምምነት ለአፍሪቃ ቀንድ እና ኢትዮጵያ ያለው አንድምታ
የኤርትራ ሰራዊት በኢትዮጵያው ትግራይ ክልል መታየታቸውን በርካታ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ባሳለፍነው እሮብ በስፋት ከመዘገባቸው አስቀድሞ ግብጽ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ሱማሊያን አካቶ ባሳለፍነው እሁድ በግብጽ ባኖሩት ስምምነት የወታደራዊ እና የደህንነት ትብብር እንደሚያደርጉ ከገለጹ በኋላ ነው፡፡
ሮይተርስ የዜና ወኪል የአገራቱ የጸጥታ እና የፖለቲካ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው በስምምነቱ ከአባል አገራት የአንደኛው ድንበር ከተነካ ቀሪዎቹ ከተጠቂ አገር ጎን እንደሚቆሙ ተስማምተዋል፡፡
አገራቱ ከስምምነት የደረሱም ኢትዮጵያ እናኤርትራ መሃል ከፍተኛው ወታደራዊ ውጥረት መንገሱ በተሰማበትና ግብጽ እና ኢትዮጵያም ቢሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻቸው ባየለበት ወቅት ነው፡፡
ይህ የአገራቱ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያና ቀጣናው ይዞ የሚመጣው መዘዝ ምን ይሆን? የታሪክ አጥኚና የፖለቲካ ተንታኝ ዶ/ር ኢብራሂም ሙሉሸዋ እንደሚሉት ይህ የሚያስገርም አይደለም፡፡
“ፕሮጀክቱ የግብጽ ፕሮጀክት ሲሆን ይህም ኢትዮጵያን በምንም መልኩ ለማዳከም የምታደርገው ውጥን ማስፈጸሚያ መንገድ ነው” በማለት ሌሎቹ ከግብጽ ጋር በኢትዮጵያ ጥቅም ተቃራኒ የቆሙ አገራቱ የራሳቸው ሰፊ የቤት ስራ ያለባቸው ናቸው በማለት ስምምነቱ ከመግለጫ እንደማያልፍ እምነታቸው መሆኑን በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የውስጥ ግጭቶችን በመፍታት ጠንካራ መንግስት መመስረትና በብሔራዊ ጥቅሞች ጉዳይ በጋራ መቆም እንዲቻል መስራት እልባት እንደሚሆንም አመልክተዋል፡፡
ጦርነቱ የደቀነው የሰብዓዊ ስጋት
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰሜን ኢትዮጵያ ባገረሸው ጦርነት የዓለማቀፉ ማህበረሰብ ስጋቱን በሚገልጽበት ባሁን ወቅት የተባበሩት መንግስታት የረድኤት ድርጅቶች ትግራይ ክልል ውስጥ መግባት መጀመራቸውን እየገለጸ ይገኛል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ ቃል አቀባይ ስቴቬን ዱጃሪች እንዳሉትም፤ “በኢትዮጵያ አሁን ላይ የተሰማው መልካሙ ነገር የተወሰኑ የእርዳታ አቅርቦቶች ትግራይ ክልል መግባት መጀመራቸው ነው፡፡
በግጭቱ የተጎዱ የተወሰኑ ማህበረሰብ የምግብ እርዳታ ተቀብለዋል፡፡ የባንኮች ወደ ስራ መመለስም መልካም ነገር ነው፡፡ የተ.መ.ድ አጋር ድርጅቶች በዝርፊያ የተራቆቱ ማጠራቀሚያዎቹን ለመተካት ተጨማሪ እርዳታዎችን ለመላክ ዝግጁ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ለውጥ ቢኖርም አሁንም ፈተናዎች አሉ፡፡ በጦር ግንባሮች ካለው የፀጣታ ስጋት በተጨማሪ ዝርፊያ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ከፈተናዎቹ መሃል ናቸው፡፡ አሁንም የተ.መ.ድ ማንም ይሁን ማን ለአስቸኳይ እርዳታ ክፍት መሆን ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ እንዳሉትም የእርዳታ አቅርቦቱ ከትናንት ዓርብ ጀምሮ በተለያዩ ጣቢያዎች ሲሰራጭ ተመልክተዋል፡፡ “እርዳታ ጀምሯል፤ ትናንት ማንነታቸውን ባላውቅም በተለይም ለተፈናቃዮች የእርዳታ እህል ስራገፍላቸው ተመልክቻለው” በማለት የተመለከቱትን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ያገረሸው ግጭት ተባብሶ በቀጠለበት ባሁን ወቅት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው በመግባት ወረራ ፈጽመዋል በማለት ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ደብዳቤ መጻፋቸው ግጭቱ ምናልባትም ከወትሮም ባለመረጋጋት በሚታወቀው በአፍሪካ ቀንድ ወደ ሌላኛው የጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ እየሰፋ ይሆን የሚል ስጋትን አጭሯል።
ኢትዮጵያ በኤርትራ ተፈጽሞብኛል ላለችው ወረራ “ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት” በመግለጽ የተባበሩት መንግሥታት ያለውን ሁኔታ እንዲገነዘብ መጠየቋን ተከትሎም፤ የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረአብ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ ኤርትራ ኢትዮጵያ ትንኮሳዎችን ስትፈጽም ታግሳ መቆየቷን በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ክስ አጣጥለዋል።
ስዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ