1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

የቀጠለው የኦሮሚያ ግጭት እና ለዘላቂ መፍትሄ የፖለቲከኞች አስተያየት

ሰኞ፣ ኅዳር 24 2016

በኦሮሚያ ክልል ለዓመታት የዘለቀው ጦርነት በቅርቡ ካልተሳካው የሰላም ንግግር ማግስትም እንደተባባሰ ነው። ግጭቱን በኃይል የበላይነት ለመደምደም የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን መንግሥት እያመለከተ ነው። በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ሀይሎች በፊናቸው የጦርነት መቋጫ መፍትሄ ለፖለቲካዊ ስብራቱ ሰላማዊ አማራጭ መፈለግ ብቻ እንደሆነ ያሳስባሉ።

ፎቶ ከማኅደር፤  ኦሮሚያ ክልል በከፊል
በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው የመንግሥት ኃይሎች እና የኦነሰ ውጊያ አዎንታዊ መፍትሄ አለመሆኑን ፖለቲከኞች እያሳሰቡ ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ ኦሮሚያ ክልል በከፊልምስል Seyoum Getu/DW

የቀጠለው የኦሮሚያ ግጭት

This browser does not support the audio element.

 

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛን ዋቢ አድርጎ እንደ ዘገበው መንግሥት በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ሸኔ በሚል የተጠቀሰውና በሽብር የተፈረጀውን እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሰ) ያለው ታጣቂ  ቡድን ላይ ጠንካራ የተባለው ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል። ኃላፊው «በተከፈተው የፖለቲካ ምህዳር ባለመጠቀም ኃይልን መሠረት ያደረገ የትጥቅ ትግል አንስቶ ባለፉት ዓመታት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ቢያደርስም፤ መንግሥትም ቡድኑ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመጣ ጥረት ተደርጓል» ማለታቸውን ያስነበበው ዘገባው፤ «ታጣቂ ቡድኑ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር የመምጣት ፍላጎት ባለማሳየቱ መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማስፈን የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ይወጣል» ማለታቸውንም ነው የገለጸው። የኢፌዴሪ የአገር መከላከያም በይፋዊ ማኅበራዊ ገጹ ደጋግሞ በሚለጥፋቸው መረጃዎች «አሸባሪ» ባለው ታጣቂ ቡድኑ ላይ ጠንካራ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን በመግለጽ ላይ ነው። በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ግን በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግሥት እና እራሱን ኦነግ-ኦነሰ ብሎ በሚጠራው በኦሮሚያ በትጥቅ መንግሥትን በሚወጋው ቡድን መካከል በታንዛንያ የተደረገው የስምምነት ጥረት ባይሳካም አሁንም የሰላማዊ አማራጭ ጥረቶች ሊቀጥሉ ይገባል ይላሉ። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ዑርጌሳ እንደሚሉት፤ «ይህ ጦርነት ዘመናትን እየተሻገረ ያለ፤ የተራዘመ ጦርነት እንደመሆኑ መፍትሄው አሁንም የፖለቲካ ልዩነትን ጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ መፍታት ነው» ብለዋል። ባለፈው በታንዛንያ በሁለት ዙር የተደረገው የሰላም ስምምነት ጥረቱ ተስፋ የተጣለበት ነበር ያሉት ፖለቲከኛው ተፋላሚዎቹ በንግግር ላይም ሆነው ሲካሄድ የነበረው የጦርነት ስምሪት እና ዜናዎች ሂደቱ እንደማይሰምር ከጅምሩም ያሳውቅ ነበር ይላሉ። አቶ በቴ አሁንም ቢሆን የፓርቲያቸው ግፊት ለልዩነቱ ሰላማዊ እልባት እንዲፈለግ ነው ብለዋል።

ድርድሩ «አስቀድሞም በአገር ደረጃ ሰላምን ለማውረድ ታስቦበት ሲካሄድ የነበረ አይመስልም» ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፖለቲከኛ ጥሩነህ ገምታ ናቸው።  «ውይይቱ እየተደረገም ጦርነት ሲካሄድ ነበር። አሁንም ያ ጦርነት ነው የቀጠለው። አሁን በሁለቱም ወገኖች የማሸነፍ ነጋሪት እየተጎሰመ ቢሆንም ይህ ጦርነትን እንደማሸነፍ መታየት የለበትም» ብለዋል። ጦርነቱ በህዝብ መሃከል የሚደረግ እንደመሆኑ አሸናፊና ተሸናፊን መለየት ከባድም ነው ብለዋል ፖለቲከኛ በአስተያየታቸው።

ፖለቲከኛ በቴ ሊደረግ ተይዞ የነበረው የሰላማዊ አማራጭ ውጥኑ እንዲሳካ ከታጣቂዎች በተጨማሪ በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ የፖለቲካ ኃይሎች ጋርም ንግግር ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት። «ችግሩ እዚህም ካሉት በሰላማዊ ኃይሎች ጋር ሳይነጋገሩ ከታጠቀ ኃይል ጋር በመነጋገር ብቻ የሚፈታ አይደለም» ብለዋል። ፖለቲከኛው ልዩነቶቹ አሁንም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የፖለቲካ ድርጅታቸው ፍላጎት መሆኑን አስረድተው ግጭቱ በዚሁ ከቀጠለ ግን ውድመቱ የማያቧራ ይሆናል የሚለውን አስተያየታቸውን አክለዋል።

ፖለቲከኛ ጥሩነህ በፊናቸው፤ «ማስተዋል የተሳናቸው ኃይሎች» ያሏቸው ሀይሎች መካከል የሚደረግ ጦርነት «ልማትና አገርን ከማውደም የዘለለ ፋይዳ የለውም» ሲሉ ነው አስተያየታቸውን ያከሉት። በጦር የሚፈታ ችግር ጎዶሎ ነው ያሉት ፖለቲከኛው ሁለቱም ተፋላሚዎች በተፋጠነ ጊዜ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ጠይቀዋል። በታንዛንያ ተካሂዶ ያለስምምነት የተጠናቀቀውን የሰላም ጥረት ተከትሎ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በተናጥል ባወጡት መግለጫ ለሂደቱ መደናቀፍ አንዱ ሌላውን ሲወቅስ ነበር። ይሁንና ሁለቱ ሀይላት ለሰላማዊ መፍትሄው ሁሌም በራቸው ክፍት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹም ይስተዋላል።

 ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW