1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የቀጠለው የኮሬ ዞን ጥቃት

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሐሙስ፣ ኅዳር 17 2019

በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮሬ ዞን ታጣቂዎች ትናንት ባደረሱት ጥቃት ሰዉ ተገደለ፤ ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ነዋሪዎች ሰሉ። ከዚህ በፊት በተፈጸሙ ጥቃቶች የተፈናቀሉ እና በዞኑ ጎርካ ወረዳ ጀሎ ቀበሌ ተጠልለው የነበሩ ነዋሪዎች ዳግም መፈናቀላቸውን ተናግረዋል። ታጣቂዎቹ ወደ ዞኑ በመግባት ጥቃት ማድረሳቸው ታዉቋል።

 የኮሬ ዞን ጥቃት
የቀጠለው የኮሬ ዞን ጥቃት እና የጥቃት አድራሾቹ ማንነትምስል፦ Shewangizaw Wogayehu/DW

የቀጠለው የኮሬ ዞን ጥቃት

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮሬ ዞን ታጣቂዎች ትናንት ባደረሱት ጥቃት አንድ ሰው በመግደል  ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ማቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ ፡፡ ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ጥቃቶችን በመሸሽ በዞኑ ጎርካ ወረዳ ጀሎ ቀበሌ ተጠልለው የነበሩ ነዋሪዎች ዳግም መፈናቀላቸውን ገልጸዋል ፡፡ ታጣቂዎቹ ወደ ዞኑ በመግባት ጥቃት ማድረሳቸውን የኮሬ ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል። 

የቀጠለው የኮሬ ዞን ጥቃት

በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮሬ ዞን ታጣቂዎች ትናንት ባደረሱት ጥቃት አንድ ሰው በመግደል  ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ማቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ ፡፡ ታጣቂዎቹ ትናንት ጥቃቱን ያደረሱት በኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ጀሎ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ነው ፡፡ በጥቃቱ አንድ ሰው ሲገደል አሥራ ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን ለዶቼ ቬሌ የተናገሩት ሁለት የከተማው ነዋሪዎች ‹‹ ተጨማሪ የቆሰሉ ሰዎች አሉ እየተባለ ሥለሆነ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ሊል ይችላል ›› ብለዋል ፡፡

ዳግም የተፈናቀሉት የጀሎ ቀበሌ ነዋሪዎች

በትናንቱ ጥቃት ከቀኑ ሰባት ሰዓት እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበር የአይን እማኞች ተናግረዋል ፡፡ በጥቃቱ ከሞቱት እና ከቆሰሉት በተጨማሪ በዞኑ ጀሎ ቀበሌ ከዚህ በፊት  የተፈጸመውን ጥቃት በመሸሽ በጊዜያዊነት ተጠልለው የቆዩ ነዋሪዎች ዳግም መፈናቀላቸውን ገልጸዋል ፡፡

በጥቃቱ ተፈናቃይ ቤተሰቦች ፍርሃት ውስጥ ወድቀው እንደነበር የጠቀሱት ነዋሪዎቹ ‹‹ አብዛኞቹም ተፈናቃዮች ቤተሰቦቻቸውን በመያዝ ወደ ኬሌ ከተማ ገብተዋል ፡፡ በተጨማሪም  ከተለያዩ የገጠር ቀበሌያት ለገበያ ወደ ኬሌ ከተማ ገብተው የነበሩ አርሶአደሮች በተኩሱ በመደናገጥ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብተው ነበር ፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አድማ በታኝ አባላት ከህዝቡ ጋር በመሆን የታጣቂዎቹን እንቅስቃሴ በመግታታቸው ከዚህ በላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ አድርገዋል ›› ብለዋል ፡፡

 የጥቃት አድራሾቹ ማንነት

ትናንት ረብዕ ታጣቂዎች ወደ ዞኑ በመግባት ጥቃት ማድረሳቸውን የኮሬ ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ሰባክ ሰሎሞን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል ፡፡ ጥቃት አድራሾቹ ‹‹ ሸኔ ›› በሚል የጠቀሷቸው የጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን አባላት ናቸው በማለት የተናገሩት አቶ ሰባክ ‹‹  ጥቃቱን ያደረሱት ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ  ወደ ኮሬ ዞን በመሻገር ነው ፡፡ ቡድኑ የከፈተብንን ጥቃት እስከ ምሽት በመከላከል መልሰነዋል ፡፡ በእኛ በኩል የሞቱም የቆሰሉም አሉ ›› ብለዋል ፡፡

የምክር ቤቱ እንደራሴ ጥያቄ

በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮሬ ዞን ታጣቂዎች በሚፈጽሙት ጥቃት ዜጎች ለሞትና መፈናቀል እየተዳረጉ እንደሚገኙ  እየተገለጸ ይገኛል ፡፡ የፀጥታ ችግሩ እንዲፈታ ለክልል እና ለፌዴራሉ መንግስት በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ዛሬም ድረስ መፍትሄ ያገኘ አይመስልም ፡፡ ዛሬ ሐሙስ በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን አራተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ይሄው የኮሬ ዞን የፀጥታ ጉዳይ በአንድ የምክር ቤቱ አባላት ተነስቷል ፡፡

የመንገድ መዘጋት ፣ የዜጎች ሞትና ሰብአዊ መብቶች ጥሰት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት እኝሁ የምክር ቤት አባል ‹‹ በተለይም የኮሬ ህዝብ በየትኛውም የኢትዮጵያ ታሪክ አይቶትም ሰምቶትም በማያቅበት ሁኔታ ላለፉት አሥራ አንድ ዓመታት በጽንፈኛ ታጣቂዎች እየተወረረ ህልውናው አደጋ ላይ  እየወደቀ መንግሥት ለምንድ ነው ቸል ያለው  ? የዚህ ህዝብ ተስፋ እና ዕጣ ፋንታስ ምንድ ነው ? በማለት ጠይቀዋል ››

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት የኮሬ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤትምስል፦ Shewangizaw Wogayehu/DW

የጠቅላይ ሚንስትሩ ምላሽ

በኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር አለ የተባለው ትክክል መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ‹‹ ነገር ግን ድሮ ከነበረው ከፍተኛ መሻሻል አለ  ›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡ የቀረውን ተባብረን እንሥራ የሚል ጥያቄ ያቀረቡት አብይ ‹‹ ከእናንተ የምፈልገውና የተከበረው ምክር ቤትን የምጠይቀው አንድ ችግር ሲያጋጥም ሃላፊነት በሚሰማው አካል መልክ አንድ ቋንቋ እንናገር ፡፡ ጥፋተኛን በጋራ አውግዘን በጋራ ከታገልን እናጠፋዋለን ፡፡ መፍትሄው ህዝቡና የጸጥታ ተቋማት ተናበው ፣ መረጃ ተለዋውጠው እነዚህ ጊዜ ጠብቀው አድብተው እንደምስጥ አፈር ውስጥ ተደብቀው እየወጡ ጥቃት የሚያደርሱትን በጋራ ለመከላከል መሥራት ያሥፈልጋል ›› ብለዋል። 

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ
አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ

 

Edited by: Negash Mohammed ነጋሽ መሐመድ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW