1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቅኔ ተማሪዎች ተበትነዋልን?

ዓርብ፣ ጥቅምት 4 2015

ቅሬታ አቅራቢዎች የወረታ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ግቢ ውስጥ የነበረ የቅኔ ጉባኤ ቤት በመፍረሱ በርካታ የቅኔ ተማሪዎች ተባረዋል ሲሉ ይወቅሳሉ። ወቀሳ የቀረበበት ወገን ደግሞ ፈረሰ ሳይሆን የሚባለው የተሻሻለ ቦታ ላይ መማሪያ ቦታ ሰጥተናቸዋል ፣ይሁንና የተማሪው ቁጥር እንዲቀንስ አድርገናል ይላል።

Äthiopien |  Kirchliche Schule in Gonder
ምስል Kidus Gebreal Qinee gubae bet

የቅኔ ተማሪዎች ተበትነዋልን?

This browser does not support the audio element.

«የወረታ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የሰበካ ጉባኤ ፅህፈት ቤት ለገንዘብ ብሎ መንፈሳዊ ትምህርት ሳይሆን አለማዊ ትምህርት ማስተማር መርጧል» የሚል ከባድ ትችት ቀርቦበታል።  የዛሬው ዝግጅት  ወደ አማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ወረታ ከተማ ይወስደናል።  በዚህች ከተማ የሚገኘው የወረታ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ግቢ ውስጥ ከአሁን በፊት የቅኔ ጉባኤ ቤት እንደነበረ እና መምህራን፤ ጳጳሳት ዲያቆናት እና ቀሳውስት የሚወጡበት ጉባኤ ቤት እንደነበር የነገሩን መምህር ተመስገን ዘገዬ ይባላሉ። « መምህሩ ከ 39 ዓመት በላይ በቅኔ መምህርነት አገልግለዋል።  ይህን ጉባኤ ቤት የሰበካው ጉባኤ ለአፀደ ሕፃናት ማስፋፊያ አለ እና አብነቱን ያለ አብነት አስቀርቶ በተነው» ሲሉ ከአርባ በላይ ተማሪዎች መበተናቸውን መምህር ተመስገን ይናገራሉ። 
መሪ ጌታ በጽሐ የ 26 ዓመት ወጣት እና ጉባኤ ቤቱ ከመፍረሱ በፊት በዚህ ቦታ ይማር የነበረ  ነው። ለ 8 ዓመታት በቋሚነት  በዚሁ ጊቢ የቅኔ ተማሪ ሆኖ እየተማረ የቆየ ሲሆን በቦታው ተፈፅሟል የሚለው « በ 2014 ሚያዢያ አካባቢ ይፍረስ የሚባል ነገር ነበር። እኛም ለምን ይፈርሳል ብለን ሀገረ ስብከት ሄደን አመለከትን። ሀገረ ስብከቱም ማገጃ ሰጥቶን ይዘን መጥተን ሰጠናቸው። ይሁንና ይህንን ተግባራዊ ሳያደርጉ ነሀሴ ላይ እንዲፈርስ አደረጉ» ይላል። መሪ ጌታ በጽሐ ሰበካ ጉባኤው ለምን ወቀሳችሁኝ በሚል ፖሊስ ጣቢያ እንድንቀርብም አስደርጎናል፣  ወደ ቤተ ክርስትያኑም እንዳንደርስ እና እንዳንፀልይ ተደርገናል ይላል። 
ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ምህረት ሞላ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ጉባኤ ቤቱ እንዳይፈርስ በደብዳቤ ፤ በቃልም አሳውቀን የነበረ ቢሆንም እንዲፈርስ ተደርጓል ይላሉ። « ወረዳ ቤተ ክነቱ የፃፍነውን ደብዳቤ ሳያይ እና ሳያስተካክለው ቀርቶ መፍረሱን ሰማን። » ይላሉ። እሳቸውም ሰበካ ጉባኤውን እና ወረዳ ቤተ ክህነቱን ጠርተው መፍትሄ እንዳፈላለጉ እና በአሁኑ ሰዓት የወረዳ ቤተ ክህነት ኃላፊው ከቦታቸው እንደተነሱ ገልፀውልናል።
መልአከ ብሥራት ጸጋ አዲስ ፤ የወረታ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል  ቤተ ክርስትያን አስተዳዳሪ ናቸው። ታሪካዊ እንደሆነ የተገለፀውን ቦታ ማፍረስ ለምን እንዳስፈለገ ጠይቄያቸዋለሁ። እሳቸው ግን አንድም የፈረሰ ጎጆ የለም ይላሉ። « የተሻለ ቦታ ነው ቀይረን የሰጠናቸው። ያ ቦታ የእናቶች መግቢያ በር ስለሆነ እና መንገድ ሊሰራ ስለሆነ የቦታ ቅየራ አድርገን ነው።  12 ሰርቪስ ቆርቆሮ ቤት እና 11 ጎጆ ቤት ሰርተን ነው ያንን ቦታ ያስረከብናቸው።»
የ ቤተ ክርስትያኒቱ አስተዳዳሪ «ምንም ጎጆ አልፈረሰም» ይበሉ እንጂ የቤተክርስትያኒቱ የቅኔ ጉባኤ ቤትን መሠረተ ድንጋይ የሚያሳይ እና ከጎኑ የወዳደቁ እንጨቶች እና የሳር ቤት ክዳኖችን የሚያሳዩ ምስል እና ቪዲዮዎች ከቅሬታ አቅራቢዎቹ አንዱ ከሆኑት ደርሶናል። 
ሌላው የጉባኤ ቤቱን አላስፈረሱም በሚል የአብነት መምህሩ የወር ደሞዝ በሰበካ ጉባኤው አማካኝነት እንዲቆረጥባቸው ተደርጓል የሚለው ወቀሳ ነው። የቤተ ክርስትያኒቱ አስተዳዳሪ  መልአከ ብሥራት ጸጋ ግን የመምህሩ ደሞዝ የተቆረጠው የጉባኤ ቤቱን ስላላስፈረሱ አይደለም ይላሉ።  « ተማሪ እና ተማሪ ተጣልቶ አካል በመጉደሉ ፤ አካል የጎደሉ ተማሪዎች ይውጡ ብንል ለመምህሩ ይህንን ስላልተገበሩ ነው የተቀጡት።» ይላሉ። ከሀገረ ስብከቱ የደረሳቸው ደብዳቤ እንደሌለም መልአከ ብሥራት ጸጋ ይናገራሉ።
መ/ር አየነው ጉዳዩን እንዲያጣሩ ሀገረ ስብከቱ ወክሏቸው ከደብረታቦር ወደ ወረታ በመሄድ በአካል ጉባኤ ቤቱን ያዩ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኛ ናቸው። « ተማሪዎቹን አዲስ በሰሩላቸው የተወሰኑ ጓጆዎች መልሰው መምህሩ እያስተማሩ ባለበት ወቅት ነው እኔ ወደ እዛ የሄድኩት ። አብዛኞቹ ተማሪዎች ተበትነው ነበር።  እኛም  ከሰበካ ጉባኤው ጋር ተወያይተን ቤታቸው እንዲሰፋ፤ የመምህሩ መብት እንዲጠበቅ ፣ የደቀመዛሙርቱ መብት እንዲጠበቅ፤ መግባት የሚፈልግ ተማሪ ገብቶ እንዲማር ሰበካ ጉባኤው ማመቻቸት እንዳለበት ነው መግባባት ላይ የደረስነው» ብለዋል።

ፈረሰ የተባለው የወረታ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የቅኔ ጉባኤ ቤት ምስል Kidus Gebreal Qinee gubae bet
የወረታ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የቅኔ ጉባኤ ቤት ተማሪዎች ጉባኤ ከዚህ ቀደም መምህራቸውን ሲጠይቁና ሲማማሩምስል Kidus Gebreal Qinee gubae bet


ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW