1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ መልዕክት

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 14 2017

በኢትዮጵያም ሆነ በአካባቢው "አለመግባባት በዝቷል፣ ማኩረፍና መቀያየም ሰፍቷል" ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዐቡነ ማትያስ ተናገሩ። ፓትርያርኩ በቤተ ክርስትያኗ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ እና ዓመታዊ ጉባኤ መክፈቻ "ነገር ሁሉ ግራ የሚያጋባ እና የተመሰቃቀለ ሆኖ ይታያል" ሲሉ ተደምጠዋል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዐቡነ ማትያስ
በኢትዮጵያም ሆነ በአካባቢው "አለመግባባት በዝቷል፣ ማኩረፍና መቀያየም ሰፍቷል" ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዐቡነ ማትያስ ተናገሩ።ምስል DW/G. Tedla

የቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ መልዕክት

This browser does not support the audio element.

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያም ሆነ በአካባቢው "አለመግባባት በዝቷል፣ ማኩረፍና መቀያየም ሰፍቷል" ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዐቡነ ማትያስ ተናገሩ። ፓትርያርኩ ትናንት በቤተ ክርስትያኗ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ እና ዓመታዊ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር "ነገር ሁሉ ግራ የሚያጋባ እና የተመሰቃቀለ ሆኖ ይታያል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ቅዱስ ፓትርያርኩ አክለውም ችግሩ ከሕዝብ አልፎ የአምልኮ ፈፃሚዎችና ስፍራዎችን ዒላማ ማድረጉንና ይህም "ለአንድ ሀገር ወይም ሕዝብ የውድቀት ምክንያት ከመሆን በቀር የዕድገት ምልክት ሊሆን አይችልም" ብለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ "በረቀቀ ስልት" ባሉት ሁኔታ አማንያን ላይ የሚፈፀም ግድያ፣ ዕገታ፣ የመብት ተፅእኖ እና አድሎ እንዲቆምም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዐቡነ ማትያስ የጥቅምቱን የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ እና ዓመታዊ ጉባኤ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት ዘመኑ ለፍጥረተ-ሰብ የተመቸ አልሆነም፣ በመላው ዓለምም ይሁን በኢትዮጵያ በተለይ ለኦርቶዶክስ ክርስትያኖች "ከባድ ፈተና" ደቅኗል።

የኢትዮጵያኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የሰላም ጥሪ

"በአሁኑ ጊዜ በሀገራችንም ሆነ በአካባቢያችን አለመግባባት በዝቷል፤ ማኩረፍና መቀያየም ሰፍቷል፤ ነገር ሁሉ ግራ የሚያጋባ እና የተመሰቃቀለ ሆኖ ይታያል"

በንግግራቸው ሕዝብን ማስተማር እና መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት ዐቡነ ማትያስ ምእመኑ በቤተ ክርስትያኗ አባቶችና መሪዎች ዘንድ ይህንን ለማድረግ አቅም፣ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት መኖሩን ማወቅ ይፈልጋል ብለዋል። ሁሉም "ሀገርን እና ሕዝብን ከመጉዳት እንዲቆጠብ" አሳስበዋል።

"በከተማም፣ በጫካም፣ በገጠርም፣ በየትኛውም የምትገኙ ልጆቻችን ምንም ይሁን ምን ሀገርን እና ሕዝብን ከመጉዳት ተቆጠቡ"

የሃይማኖት አስተማሪዎች እሥር

ለመሆኑ የሃይማኖት አባቶች ለዘመናት ያልተቋረጠ የሰላምና የአንድነት ብሎም የግብረ ገብ ሥራ ሰሚ እያጣ ይልቁንም ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጉቶች ለምን ተበራከቱ የሚለውን የጠየቅናቸው ሰው ጉዳዩን ከፖለቲካ አመለካከትና ድርጊቶች ብልሽት ጋር አያይዘውታል።

አቡነ ማትያስ "በከተማም፣ በጫካም፣ በገጠርም፣ በየትኛውም የምትገኙ ልጆቻችን ምንም ይሁን ምን ሀገርን እና ሕዝብን ከመጉዳት ተቆጠቡ" ብለዋል። ምስል Solomon Muchie/DW

የፖለቲካ ድርጅቶች እየተቋቋሙ በየጊዜው ሲፈታተኑት የኖሩት [ሕዝቡን] መሪዎች ናቸው"

ክፉ ድርጊቶች እየተፈፀሙ ያሉት በኢትዮጵያውያን መሆኑ ከሁሉም በላይ የሚያሳዝን ጉዳይ መሆኑን ደግሞ ቅዱስ ፓትርያርኩ ጠቅሰዋል።

"በአማንያን ልጆቻችን ላይ በረቀቀ ስልት ግድያን፣ ዕገታን፣ የመብት ተጽዕኖ እና አድልዎ በማድረግ እንደዚሁም በአስመሳይ ስብከት እና አምልኮ ጣዖት በማለማመድ ሕዝቡ ሳይገባውና ሳይጠነቀቅ ከእግዚአብሔር መንግሥት እንዲወጣ እያደረገ ነው"

የዘመኑ የኢትዮጵያ ትውልድ ተራማጅ ነውን?

የእኔነት ስሜት የፈጠረው መጣበብ ህብረተሰቡን ብርቱ ግራ መጋባት ውስጥ እንደዘፈቀው ደግሞ የትዳር እና የመገናኛ ብዙኃን ጉዳይ አማካሪ የሆኑት አቶ ሀበነዮም ሲሳይ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። "ግራ የተጋባ ማህበረሰብ ነው የሆንነው"

ፓትርያርክ ዐቡነ ማትያስ ለመንግሥት ባለሥልጣናትም መልዕክት አስተላልፈዋል። "ቢሰሙንም ባይሰሙንም ዓለማዊያን ሹማምንትን የማስተማርና የመምከር ኃላፊነት አለብን"

ባለፉት ዓመታት በውስጥ መከፋፈል ለችግር ተጋልጣ የቆየችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በርካታ መእመኖቿ እና አብያተ ክስትያናትም ለተደጋጋሚ ጥቃት ተጋልጠውባት ስትጮህ ከርማለች። ፓትርያርኩ ከዚህ ቀደም "የዘመናችን ትውልድ ከተግባር ይልቅ አስመሳይ ሆኖ መታየትን፣ ከትሕትና ይልቅ ትዕቢትን የተለማመደ፣ ለሃይማኖትም ሆነ ለማህበረ-ሰብ ጤናማ ሕላዌ ያልተመቼ ትውልድ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው" በማለት ተናግረው ነበር።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW